ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወደ መለኮታዊ ፍትህ ከመቅረባቸው በፊት ንስሐ እንዲገቡ ጠየቁ

በስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በካናሪ ደሴት ቴኔሪፍ ከሚገኙ ስደተኞች እና የመጠለያ ማዕከላት ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው የጋራ ኃላፊነት ያለው ማኅበራዊ ውህደት ሰብዓዊ ክብርን እና አባልነት መልሶ ለመገንባት እንደሚያግዝ ተናግረው፥ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መለኮታዊ ፍትህን ከመጋፈጣቸው በፊት ንስሐ እንዲገቡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ስደተኞች ከሚኖሩበት አካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እንዲዋሄዱ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በድጋሚ ጥሪ አቅርበው፥ ይህም ከሚደረግላቸው አቀባበል ባሻገር ሰብዓዊ ክብርን፣ አባልነትን እና ዕድልን የሚያስገኝ ሂደት መሆን አለበት” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ዓርብ ሰኔ 5/2018 ዓ. ም. በሳን ክሪስቶባል ዴ ላ ላጉና ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን፣ የበጎ አድራጎት እና የሲቪል ድርጅቶች ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ የካናሪ ደሴቶች ስደተኞች ወደ አውሮፓ ከሚገቡባቸው ዋና የስደት መንገዶች መካከል አንዱ ሆነው መቀጠላቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በካናሪ ደሴት ቴኔሪፍ ውስጥ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ድርጅቶች ሥራን አድንቀው፥ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍርሃት እና ከግድየለሽነት እንዲላቀቅ አሳስበዋል።

“የልዩነት ግድግዳ የሌለባት ከተማ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው መጀመሪያ፥ የድንበር አጥር ስለ ሌለባት ላ ላጉና ከተማ የሰሙትን ጠቅሰው፥ ምስሉ ከፍተኛ ጥረትን እንደሚጠቁም ተናግረው፥ “ለማፍረስ እጅግ የሚያስቸግሩ እንቅፋቶች ሁልጊዜ ከድንጋይ የተሠሩ አይደሉም” ሲሉ አስረድተው፥ ይልቁንም አንዳንድ ጊዜ በአመለካከታችን፣ በፍርሃታችን ወይም በግዴለሽነታችን ውስጥ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የካናሪ ደሴቶች በቅርብ ዓመታት ውስጥ ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት የሚጓዙ በርካታ ስደተኞች ከሚመጡባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ጠቅሰው፥ ከሰሜናዊ ምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት እነዚህ ደሴቶች ብዙውን ጊዜ ከሴኔጋል፣ ከማውሪታኒያ፣ ከማሊ እና ከጋምቢያ ካሉ አገራት የሚመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚደርሱባቸው የመጀመሪያው የአውሮፓ ግዛት እንደሆነ ታውቋል።

የአትላንቲክ ውቅያኖስ መስመር በዓለም ላይ ካሉት በጣም አደገኛ የስደት ኮሪደሮች አንዱ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ በተጨናነቁ እና ብዙውን ጊዜ ባሕርን ለማቋረጥ በማይመቹ ጀልባዎች ይሞክራሉ። ብዙዎቹ ለቀናት ወይም ለሳምንታት በባህር ውስጥ ሲዘዋወሩ ደክሟቸው ይደርሳሉ፣ ሌሎች ደግሞ ጉዞአቸውን አያጠናቅቁም።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከስደተኞች እና ደጋፊ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ሲሰብሰቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከስደተኞች እና ደጋፊ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ሲሰብሰቡ   (@Vatican Media)

በተለየ መንገድ ማየትን መማር

“ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር መዋሄድ የተለየ የአመለካከት መንገድን ይፈልጋል” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሃሳብ፥ ሰዎች የስደተኞችን ሕይወት በሚገባ ለማወቅ የስታቲስቲክ ወይም የአስተዳደር ምድቦች መረጃን ከማንበብ ይልቅ እርስ በርስ መገናኘትን መማር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“አትኩረው ቢመለከቱም መለየት የማይችሉ ዓይኖች አሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “እነዚህ ዓይኖች የስደተኞችን ቁጥር እና ታሪክ ብቻ ይመለከታሉ” ብለው፥ ነገር ግን በምትኩ ወንጌል በትዕግስት፣ በእንክብካቤ እና በተጨባጭ ተግባር ላይ የተመሠረተ የማየት መንገድን ያስተምራል” ብለዋል።

ከበጎ አድራጎት ሥራ ባሻገር

አንድነት ወደ በጎ አድራጎት ወይም አልፎ አልፎ ወደ ልግስና ተግባራት ሊወርድ እንደማይችል አፅንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በእንግድነት መቀበል በርን እንደሚከፍት፣ ማኅበራዊ ውህደት ገደቦችን ለማለፍ እንደሚረዳ ገልጸው፥ ዕርዳታን ማድረግ ለችግሮች መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል እና ማኅበራዊ ውህደትም የወደፊት ሕይወት እንደገና ለመገንባት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ስደተኞች ማንነታቸውን እንዲተዉ ወይም ብቻቸውን እንዲኖሩ የሚያበረታቱ የማኅበረሰብ አቀራረቦችን ውድቅ አድርገው፥ ይልቁንም ውህደት የጋራ ጉዞ መሆኑን በማብራራት፥ አዲስ መጤዎች የአዲሱ መኖሪያ አካባቢ ቋንቋ፣ ሕጎግ እና ልማድ ሲማሩ፥ የሚቀበሏቸው ደግሞ ማንነታቸውን ሳያጡ አድማሳቸውን ማስፋት እንደሚማሩ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለስደተኞች በቀጥታ ሲናገሩ፥ እያንዳንዱ ስደተኛ በአዲሱ ማኅበረሰባቸው ሕይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍ እና ተሰጥኦዎቻቸውን እና ልምዶቻቸውን ለጋራ ጥቅም እንዲያውሉ አበረታተዋል።

መሸከም ከሚችሉት በላይ የሆነ ችግር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስደትን ወደ ፖለቲካዊ ወይም አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ደረጃ የሚያወርዱ አመለካከቶችን ተቃውመው፥ “ከሕጋዊ ዘርፎች ወይም መሸከም ከምንችለው በላይ ከሆኑ ችግሮች ይልቅ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል ከተፈጠሩ ሰዎች ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ሁለት ስደተኞች በሰጡት ምስክርነቶች ላይ ያሰላሰሉት ወደ ደሴቶቹ የሚመጡ ብዙ ሰዎች ደህንነትን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን የመገንባት ዕድልንም እየፈለጉ እንደሆነ ተናግረው፥ እነዚህ ስደተኞች በቃላት ሳይሆን በድርጊት የሚገልጽ ሰውን እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ “ሕይወታችሁ ከንቱ አይደለም፤ ስቃያችሁ የተሰወረ አይደለም፤ ክብራችሁ ተሻግራችሁ በመጣችሁበት ውሃ አልታጠበም” ካሉ በኋላ ስደተኞች በቋሚነት እንደ ተጋላጭ የሚገለጹ ሳይሆን በሥራ ለመሳተፍ ዕድሎችን የሚፈልጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስብሰባው ወቅት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስብሰባው ወቅት   (@Vatican Media)

በድጋሚ የሚያጋጥም የመርከብ አደጋን መከላከል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስደተኞች ወዳለሙት ቦታ በሰላም ከደረሱ በኋላ ሊከሰት የሚችለውን “ዝምተኛ የመርከብ አደጋን” አስታውሰው፥ ብዙዎች ስደተኞች ባሕሩን ለመሻገር ሲሞክሩ ቢሞቱም ሌሎች ደግሞ ወደ መድረሻቸው ከደረሱ በኋላ መገለል፣ ብዝበዛ እና ብቸኝነት እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል።

“ከማኅበረሰብ ጋር መዋሃድ ማለት በድጋሚ የሚያጋጥም የመርከብ አደጋን መከላከል ማለት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ከአስቸኳይ የዕርዳታ አቅርቦት በላይ ስደተኞችን በመደገፍ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያግዙ የሀገረ ስብከት የዕርዳታ ድርጅት ካሪታስን፣ የስደተኞች ጽ/ቤቶችን፣ ቁምስናዎችን እና የአገር ውስጥ ድርጅቶችን አወድሰዋል።

ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስደት እና በሰዎች ስቃይ ለሚተርፉ ሰዎች ባቀረቡት ጥሪ፥ በተጋላጭ ሰዎች እንቅስቃሴ እና እንግልት ውስጥ የተሳተፉ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች፣ በዝባዦች እና የወንጀል መረቦች አስተባባሪዎች ከዚህ ድርጊቶቻቸው ተመልሰው ንስሐ እንዲገቡ አሳስበዋል። “ለእያንዳንዱ የጠፋው ሕይወት፣ ለተጭበረበረ ቤተሰብ፣ መከራ እና ስቃይ ለተፈራረቀባት ሴት፣ ለተበዘበዘ ሠራተኛ በመለኮታዊ ፍትህ ፊት መቅረብ አለባቸው” ብለዋል።

አደገኛ የስደት ጉዞን የሚያስተባብሩ፣ ሠራተኞችን የሚበዘብዙ፣ ሴቶችን የሚያስፈራሩ እና ተስፋን ከመቁረጥ የሚተርፉ ሰዎችን በማውገዝ፥ “የእነዚህ ወንድሞች እና እህቶች እንባ እና ደም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ከድሆች የተዘረፈው ገንዘብ ሰላምን፣ ክብርን፣ የወደፊት ሕይወትን አይገነባም” በማለት ወንጀለኞቹ የሚበዘብዟቸውን ሰዎች እንዲፈቱ፣ የወሰዱባቸውን እንዲመልሱ እና ጊዜው ከማለፉ በፊት እርቅን እንዲፈልጉ አሳስበዋል።

ክርስቲያናዊ ምላሽ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ ውህደቱ እንደ ማኅበራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሊወሰድ እንደማይችል አሳስበው፥ እንደ መኖሪያ ቤት፣ የቋንቋ ትምህርት፣ ሥራ፣ የሕግ ጥበቃ፣ ጓደኝነትን እና ምስክርነትን የመሳሰሉ ተጭባጭ ድጋፎችን ማቅረብ የሚችሉ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ማግኘት እንደሚገባ አሳስበው፥ “ስደተኞችን የምትቀበል ቤተ ክርስቲያን ወንጌልንም የምትሰብክ ናት” ብለው፥ ወንጌልን ዘወትር የህሊናን ነፃነት በማክበር መሰራጨት እንዳለበት አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ቅዱስ ቤተሰብ ወደ ግብፅ ያደረገው ስደት በታሪክ ውስጥ ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች ዘላቂ ምልክት መሆኑን አመልክተው፥ “የናዝሬት ቅዱስ ቤተሰብ ለእያንዳንዱ ስደተኛ ቤተሰብ እና አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ለተገደዱት ሰዎች በሙሉ ምሳሌ እና መሸሸጊያ ሆነው ይቆያሉ” ሲል ተናግረዋል።

 

13 Jun 2026, 16:45