ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለሰላም መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባርሴሎና የቅዱስ ቤተሰብ ባዚሊካ ከድንጋይ፣ ከቀለም እና ከብርሃን የተሰራ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ምስልን በመጠቀም እንደተናገሩት፣ አማኝ የሆኑ ሰዎች ንጹሐን ሰዎችን መግደል ወይም የሚሰቃዩትን፣ የሚያለቅሱትን፣ ከድህነት የሚሸሹትን መተው እንደማይችሉ አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ሳግራዳ ፋሚሊያ (የቅዱስ ቤተሰብ) ባዚሊካ የሚያደርጉትን ጉብኝት የጀመሩት በመንበረ ታቦት ፊት ለፊት ሆነው በቅዱስ ቁርባን ፊት ለፊት በመጸለይ እና ባዚሊካው በሥነ ሕንፃ፣ በብርሃን፣ በቀለም እና በምልክት አማካኝነት የክርስትና እምነትን ወደ ታላቅ መገለጫ የፈጠረውን የአቶ አንቶኒ ጋውዲ መቃብር በመጎብኘት ነው። የአቶ ጋውዲ ሞት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ግንብ በረከት የሚያከበርበትን ሥርዓተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የወንጌልን የእምነት ጥሪ በማሰላሰል በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ከዓመፅ፣ ግድየለሽነት እና ለሚሰቃዩ ሰዎች ቸልተኝነትን ከማሳየት ጋር የማይጣጣም መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በካታላን እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ባደረጉት ስብከት፣ “እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና፤” (ዩሐ. 8፡24) ከዮሐንስ ወንጌል የተወሰደውን አንድ ጥቅስ አስታውሰዋል፡- እነዚህ ጠንካራ ቃላት መሆናቸውን፣ ነገር ግን የመዳን ግብዣም ጭምር መሆናቸውን አስተውለዋል። በኢየሱስ ማመንና ጦርነት ማድረግ እንደማይቻል አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው በኢየሱስ ማመንና ንጹሐንን መግደል አንችልም። በኢየሱስ ማመንና መከራ የሚደርስባቸውን፣ የሚያለቅሱትንና ከድህነት የሚሸሹትን መተው አንችልም ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ፔድሮ ሳንቼዝ ጋር ለንጉሥ ፌሊፔ ስድስተኛ እና ለንግሥት ሌቲዚያ እንዲሁም ለፖለቲካና ለቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት ሰላምታ ሲያቀርቡ፣ የሳግራዳ ፋሚሊያ ባሲሊካ (የቅዱስ ቤተሰብ) በሮቹን እንደ ተዘረጉ ክንዶች በሮቹ እንደሚከፈቱ፣ ሁሉንም ሰው ወደዚህ መሠዊያ ለመግባት እንዲጋብዝ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያዳምጡ እንደሚጋብዝ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው ይህም በጌታ የተወደድን እና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ባለው ሕይወቱ የሚመገብ ቤተሰብ ያደርገናል ብለዋል።

የሲቪልና ሃይማኖት መሪዎችን ሲያነጋግሩ፣ ባዚሊካው ሰዎችን በእግዚአብሔር ቃልና በቅዱስ ቁርባን ዙሪያ የሚሰበስብ የአንድነት ምልክት እንደሆነ ገልጸዋል። በሥነ ሕንፃው ላይ በመመስረት፣ ቤተክርስቲያኑን ከብዙ ድንጋዮች ከተገነባ ሕያው ሕንፃ ጋር አነጻጽረውታል፣ ክርስቶስም መሠረቷና ግቧ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የባዚሊካው ቀጣይነት ያለው ግንባታ፣ ክርስቲያናዊ ሕይወትን የሚያመለክት በእግዚአብሔር ያለማቋረጥ የሚጠናቀቅ ሥራ እንደሆነ፣ አማኞችም በእቅዱ እንዲተባበሩ እንደሚጋብዝ ተናግሯል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የባዚሊካውን ዲዛይን መንፈሳዊ ትርጉም አጉልተው ገልጸው፣ የፊት ገጽታዎቹ እና አዲሱ የተባረከው የኢየሱስ ክርስቶስ ግንብ መስቀሉን እንደ ቤዛነት፣ የተስፋ እና የመለኮታዊ ፍቅር ምልክት አድርገው እንደሚያመለክቱት አስታውቀዋል። በግንቡ ላይ ያለው ብርሃን ያለው መስቀል ለእምነት የሚታይ ምስክርነት እና ለከተማዋ ምልክት ሆኖ ያገለግላል። ጥበብ እምነትን በመግለጽ ረገድ ልዩ ሚና እንደሚጫወት አፅንዖት ሰጥተው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ጎብኚዎች ክርስቶስን እንዲገናኙ የሚያደርጋቸውን መንፈሳዊ ጉዞ በመፍጠሩ የስነ-ሕንጻውን ንድፍ አውጪ አቶ ጋውዲ አመስግነዋል።

ስብከታቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሳግራዳ ፋሚሊያ (የቅዱስ ቤተሰብ) ባዚሊካ ግንባታ የደገፉትን አመስግነዋል፣ እንዲሁም ባዚሊካውን እንደ የሥነ ሕንፃ ድንቅ ሥራ እና ኃይለኛ የወንጌል አገልግሎት መሣሪያ አድርገው ገልጸውታል። ምእመናን ዓይኖቻቸውን ወደ ክርስቶስ እንዲያነሱ ብቻ ሳይሆን የተገለሉትን እና የሚሰቃዩትንም እንዲያንሱ አሳስበዋል፣ ይህም የባዚሊካ የተስፋ እና የበጎ አድራጎት መልእክት የክርስትናን ሕይወት እና ምስክርነት እንዲመራ ያስችላችኋል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

11 Jun 2026, 14:57