ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “እውነተኛና ፍጹም ደስታን የሚጠን የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እውነተኛ እና ፍጹም ደስታ ሊሰጠን የሚችል የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ መሆኑን በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት በሚገኝ የፍራንችስካውያን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለወጣቶች በተዘጋጀው ዓመታዊ የበጋ ወቅት ጉባኤ ተሳታፊዎች በላኩት የቪዲዮ መልዕክት ላይ ገልጸዋል።
ውስጣዊ ሰላም የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው
በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ሆነው 50ኛውን የበጋ ወቅት ጉባኤውን ለሚካፈሉት ወጣቶች በሙሉ ሰላምታቸውን በማቅረብ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፥ ዓመቱ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዕረፍት ስምንት መቶኛ ዓመት የሚከበርበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ጉባኤው የተዘጋጀው በፍራንችስካውያን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሆኑን በማስታወስ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በተለይም ዛሬ እውነተኛ ሰላም እና ፍጹም ደስታን በማስመልከት ለወጣቶች ሊያስተላልፍ በሚችለው መልዕክት ላይ ማሰላሰል ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።
በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በአሲሲ ጎዳናዎች ላይ ቅዱስ ፍራንችስኮስ አንድን ሰው ቢያገኝ በተረጋጋ እና ፍቅር በተመላበት ፈገግታ “ሰላም እና መልካም ላንተ ይሁን!” ሊል እንደሚችል ተናግረው፥ “ለምናገኛቸው ሰዎች እውነተኛ ሰላም እንመኝላቸዋለን ወይ?” በማለት ወጣቶችን ራሳቸውን እንዲጠይቁ ጋብዘዋል።
ይህ ዘወትር ቀላል እንዳልሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሰላምን መዝራት የቻለው በራሱ ጥንካሬ ሳይሆን የእውነተኛ ሰላም ምንጭ በእርሱ ውስጥ በመኖሩ መሆኑን ወጣቶች እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።
የእግዚአብሔር የሰላም መሣሪያዎች ለመሆን ተጠርተዋል
“ሰላም እግዚአብሔርን ወደ ልባችን ስንቀበል ከእርሱ የሚላክልን ስጦታ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ስለዚህ ምዕምናን የሰላም መሣሪያዎች በመሆን ይህን ሰላም ለቤተሰቦች፣ ለማኅበረሰቦች፣ ለአገር እና ለመላው ዓለም እንዲያስተላልፉ የተጠሩ ናቸው” ብለዋል።
ወጣቶች በጉባኤው ወቅት የጽሞና ጊዜያትን ተጠቅመው የክርስቶስን ሰላም እንዲያገኙ ጋብዘው፥ ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የገባላቸው ቃል መሆኑን አስታውሰዋል (ዮሐ. 14:27)።
እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ደስታን ማግኘት በእርግጥ ይቻል እንደሆነ የተጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ሕይወታችን ሰላም ሊያገኝ የሚችለው አፍቃሪ አባት ከሆነው እግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ሲመሠረት ብቻ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
እውነተኛ ያልሆነ እርካታን አለመፈለግ
“ቅዱስ ፍራንችስኮስ የተናገረው ደስታ፥ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች፣ ስልካችን ላይ ለሰዓታት በመቆየት ወይም ሳያቋርጡ በየቀኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሆኑ ሊገኝ አይችልም” ብለው፥ እንዲህ ያሉ ልምዶች ብዙውን ጊዜ ለጸሎት፣ ለእውነተኛ ጓደኝነት፣ ለቤተሰብ ሕይወት፣ ለሃይማኖት ትምህርት፣ ለጥናት ወይም ለስፖርት ሊውሉ የሚችሉ ጠቃሚ ጊዜዎችን እንደሚያባክኑ አስጠንቅቀዋል።
እንዲሁም ደስታ ዕፅን በመውሰድ፣ አልኮልን ያለአግባብ በመጠቀም፣ በዝሙት፣ በውጫዊ ግንኙነቶች፣ ለማይጠቅሙ ምስሎች ከመጠን በላይ በመጨነቅ ወይም በማንኛውም ዓይነት ጎጂ ባሕሪ በኩል መፈለግ የለበትም” ብለው በተጨማሪም ሁሉ ቀሪ በመሆኑ ደስታ በሃብት ብዛት፣ በውበት፣ በዝና ወይም ጤናን በመሳሰሉ ቁሳዊ ነገሮች ውስጥ ሊገኝ እንደማይችል አክለዋል።
እግዚአብሔር ያለ ቅድመ ሁኔታ ወዶናል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ የሰውን ልብ በእውነተኛ ደስታ ሊሞላ እንደሚችል አረጋግጠው፥ እግዚአብሔር እንደ ውድ ልጆቹ የሚያስብልን መሆኑን በሚገባ የምናምን ከሆነ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ አንደነግጥም ወይም ተስፋን አንቆርጥም” ብለዋል።
“ከትንሽነታችሁ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር እንደሚወዳችሁ ሰምታችኋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ያለ ቅድመ ሁኔታ በእርሱ የተወደዳችሁ እና በፊቱ ውድ ናችሁ” (ኢሳ. 43:4) ሲሉ ተናግረው፥ ወጣቶች ይህን እውነት በእርግጥ እንዲያምኑ አደራ ብለዋል።
በሚለውጠን ኃይል ማመን
“በዘወትር ጸሎት እና በቅዱስ ቁርባን ከእግዚአብሔር ጋር አስተማማኝ ግንኙነትን ካዳበራችሁ እና ራሳችሁን ለእርሱ ከሰጣችሁ” ጭንቀት፣ ሐዘን እና ብቸኝነት ተወግዶ በጸጋው ተሞልታችሁ ፍቅሩ ልባችሁን ሲያቃጥል ታያላችሁ” ብለዋል።
“ፈታኝ ሁኔታዎችን በደስታ የመጋፈጥ ምስጢር ይህ ነው” ብለው፥ ወጣቶች ለዚህ እውነታ ልባቸውን እንዲከፍቱ፣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያስገዙ እና ሊለውጣቸው በሚችል ኃይሉ እንዲታመኑ አሳስበው፥ “ለእግዚአብሔር ለጋስ ስጦታዎች እና ታላቅ ፍቅር ልንሰጥ የምንችለው ምላሽ ምንድር ነው?” ብለው የጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ ራሳችንን ለእርሱ ከመስጠት ሌላ ምንም ምላሽ የለም!” ብለዋል።
የእግዚአብሔርን እቅድ መቀበል
እግዚአብሔር እርሱን ወደማያውቁት ሰዎች ዘንድ ቃሉን የሚያሰራጩ መልዕከተኞች፣ ቅዱሳን ምዕመናን፣ ካቶሊካዊ ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ የምስጢራት አገልጋዮች፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የመንግሥቱ እውነተኛ ደስታ ምስክሮች እንደሚያስፈልጉት ለተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
“እግዚአብሔር ከእነዚህ ጥሪዎች መካከል ወደ አንዱ እየጠራችሁ መሆኑ ከተሰማችሁ ራሳችሁን ሳትደብቁ ወይም ሳትፈሩ ነገር ግን አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዳችሁ ጌታን እነሆኝ ወደምትፈልገው ቦታ ላከኝ! በሉት” (ኢሳ 6፡8) ሲሉ አበረታትተው፥ እንደዚሁም ስለ ጥሪያቸው ለመነጋገር መፍራት እንዳይዛቸው አደራ ብለው፥ በተለይም ከሚታመን ጓደኛ፣ ከካኅን ወይም ከደናግል ጋር መነጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስዳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ፍሬያማ ጊዜን በመመኘት በእነዚህ ቀናት በክርስቶስ ፍቅር እንዲሞሉ፣ ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ለመስጠት የሚፈልጉ ሌሎች ወጣቶችን እንዲያገኙ እና ይህን በማድረግ እውነተኛ ደስታን እንዲያገኙ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
