ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14፥ ከሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14፥ ከሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የሲሮ-ማላንካራ ምዕመናን በአውሮፓ የተስፋ መልዕክተኞች እንዲሆኑ አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአውሮፓ የሚኖሩ የሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ቅርስ መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር በምትዘጋጅበት ወቅት የተስፋ መልዕክተኞች እንዲሆኑ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ሰኞ ሰኔ 9/2018 ዓ. ም. በአውሮፓ የሚኖሩ የሕንድ ሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን እንዲሁም ምዕምናንን በቫቲካን ተቀብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፥ የሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መቶኛ ዓመቷን ለማክበር ረጅም መጓዟን አስታውሰው፥ ይህም ዕድገትን በማሳየት ዛሬ ወደ ሙሉ አንድነት የደረሰችበት ጊዜ እንደሆነ አስታውሰዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1932 ዓ. ም. “ክርስቶስ የእረኞች አለቃ” በሚል ርዕሥ ያወጁትን ሐዋርያዊ ደንብ በማስታወስ፥ ቤተ ክኅነቱ እና ምዕመናን ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ጋር እንዲተባበሩ ያደረጉትን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ማር ኢቫኒዮስን እና ማር ቴዎፍሎስን ለምስክርነታቸው አመስግነዋል።

ማር ኢቫኒዮስን “በኢየሱስ ልብ የተመካ እውነተኛ እረኛ” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥የአንድነት እና የኅብረት ምልክት፣ በዓለም ላይ የእርቅ ምንጭ ሆና በምታገለግል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

ከምስክርነት ጋር የሚቀርብ ስብከተ ወንጌል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ማር ኢቫኒዮስ ወጣት ካኅን በነበረበት ጊዜም ከራሱ ማኅበረሰብ አልፎ በሕንድ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተጀመረውን የሚስዮናዊነት ተግባር ማደስ እንደሚያስፈልግ መገንዘቡን ገልጸው፥ የሚስዮናዊነት ሥራ በቃላት ብቻ ሳይሆን በመልካም አኗኗር እና በእውነተኛ በጎነት መከናወን እንዳለበት መገንዘቡንም አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሲሮ-ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ለተቸገሩት ሁለገብ ዕድገትን ለማምጣት የምትጥር የወንጌል ኃይል እና የሐዋርያዊ በጎነት ምልክት መሆኗን ተናገሩ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሲሮ-ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ለተቸገሩት ሁለገብ ዕድገትን ለማምጣት የምትጥር የወንጌል ኃይል እና የሐዋርያዊ በጎነት ምልክት መሆኗን ተናገሩ   (@VATICAN MEDIA)

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም፥ በዚህም የሲሮ-ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ለተቸገሩት ሁለገብ ዕድገትን ለማምጣት የምትጥር የወንጌል ኃይል እና የሐዋርያዊ በጎነት ምልክት መሆኗን ተናግረዋል።

የቀድሞውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛን በመጥቀስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም በፍቅር ኃይል ወደ ራሱ እንደሚጠራ እና ከሁሉም በላይ ወንጌል ሰዎችን በመማረክ የሚሰራጭ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የሚደረግ እንክብካቤ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከሕንድ ውጭ እያደገ የመጣውን የሕንድ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በማስታወስ፥ የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ እና የአምልኮ ቅርስ በዳያስፖራው ማኅበረሰቦች መካከል መጠበቅ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቀ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ፥ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊ ምዕመናንን የሚያገለግል ሐዋርያዊ ሚሲዮን መመሥረታቸውን እና በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚሲዮኑን ሐዋርያዊ እንክብካቤ ወሰን እስከ ካናዳ ማስፋታቸውን አስታውሰዋል።

በውጭ አገራት በርካታ የሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊ ምዕመናን መኖራቸውን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአውሮፓ ለሚኖሩ የሲሮ-ማላንካራ ካቶሊካዊ ምዕመናን ማር ኦስታቲዮስን የመጀመሪያው የሙሉ ጊዜ ሐዋርያዊ ጎብኚ አድርገው መሾማቸውን አስታውሰዋል።

የጳጳሱ ተልዕኮ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሁኔታን በመገምገም ጠንካራ እና ዘላቂ የሆነ መሠረትን ለመትከል እንደሆነ አብራርተው፥ ይህም የወደፊት ትውልዶች ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከልዩ የአምልኮ ሥርዓቶቻቸው ጋር እንዲያጠናክሩ ለማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለእንግዶቹ ንግግር ሲያደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለእንግዶቹ ንግግር ሲያደርጉ   (@VATICAN MEDIA)

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ በቅድስት መንበር ሥር የሚገኘው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ የምሥራቅ ካቶሊካዊ ምዕመናን ወጎቻቸውን እየጠበቁ የሚኖሩባቸውን አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ለማሳደግ የሚችሉበትን ድጋፍ ከላቲን ጳጳሳት እንዲጠይቅ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

በተግባር የሚኖሩት እና የሚጋሩት እምነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ምዕመናኑ የሲሮ-ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን ውድ ማንነትን የበለጠ እንዲያውቁ እና በቤተ ክርስቲያኗ ሕይወት ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ አበረታተዋል።

እንግዶቹ በሙሉ ከሊቀ ጳጳሳቸው እና ከብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጋር አንድ እንዲሆኑ፣ ከአባቶቻቸው የተቀበሏቸውን ቅርሶች እንዲያከብሯቸው እና እንዲንከባከቧቸው አሳስበው፥  በመጨረሻም የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ስም በመጥቀስ፥ በክርስቲያን ማኅበረሰቦች፣ በቤታቸው እና በልባቸው ውስጥ በተለይም በወጣቶች መካከል ጠንካራ እምነት እንዲኖር ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

16 Jun 2026, 11:30