ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የስፔን ወጣቶች የአዲስ ሰብዓዊነት ምልክት እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በማድሪድ የዋዜማ ጸሎት ዝግጅት ላይ ለስፔይን ወጣቶች የማበረታቻ እና የተስፋ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ የስፔይን ወጣቶች የአዲስ ሰብዓዊነት ምልክት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበው፥ በዕለቱ ከወጣቶች ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ ታሪክን ወደ ተሻለ ዓለም ለመለወጥ የወንጌል ሚስዮናውያን እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስፔይን የመጀመሪያ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ በማድሪድ ፕላዛ ደ ሊማ የቀረበውን የወጣቶች የጸሎት ዝግጅት መርተዋል። የጸሎት ዝግጅቱን ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በአደባባዩ እና በዙሪያው ባሉት ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሆነው ተሳትፈዋል። በዘመናዊው ዓለም ውስጥ እምነትን፣ የወንጌል ምስክርነትን እና ሕይወትን አስመልክቶ ከወጣቶች ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምልሽ ሰጥተዋል። በቅዱስ ቁርባን ስግደት የተከናወነው የቅዳሜው የዋዜማ ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ቅዱስነታቸው በስፔይን ለሚያደርጉት የአንድ ሳምንት ሐዋርያዊ ጉብኝት ክፍል እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)

የማድሪድ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሆሴ ኮቦ ካኖ የዛሬውን ወጣት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማስመልከት ንግግር ካደረጉ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከወጣቶቹ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ካዳመጡ በኋላ ምላሽ ሰጥዋል። ቅዱስነታቸው እምነታቸውን ያነሳሱን ሰዎችን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ እውነትን ከኅብረት ጋር ያጣመረውን ቅዱስ ዮሐንስ ክሪዞስቶምን በአድናቆት ጠቅሰው፥ በአስቸጋሪ ጊዜያት ቸርነቱን ይበልጥ ያጠናከረውን የቪላኑዌቫ ቶማስን እና ፍትህን በመጠበቅ እና ሕዝብን በማገልገል የሚታወቀውን የሞግሮቬዮ ቱሪቢየስን በመጥቀስ፥ በፔሩ በሚስዮናዊነት ባሳለፏቸው ዓመታት ውስጥ ችግር ካጋጠሟቸው ማኅበረሰቦች ጋር መገናኘት እምነታቸውን እንዳጠናከረው እና በወንጌል እንደለወጠው አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)

ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡ ምላሽ፥ የእግዚአብሔርን ድምጽ በጸሎት እና በጽሞና እንዲፈልጉ፣ ለእውነት ቁርጠኞች እንዲሆኑ እና የክርስትና እና የጋብቻ ሕይወት እውነተኛ ጥሪ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ አበረታተዋል። እውነተኛ የክርስቲያን ምስክርነት በግል ምርጫ እና በትህትና የሚጀምር መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ እያንዳንዱ ሰው አስተማሪ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ደቀ መዝሙር ሆኖ መቀጠል እንዳለበት መምህራንን እና መሪዎችን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይም በፍጆታ እና በራስ ወዳድነት የሚታወቀውን የዘመናዊ ዓለም ጭንቀትን ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ጽሞና ሰዎች የእግዚአብሔርን ድምጽ የሚያዳምጡበት፣ እውነትን ከቅዠት የሚለዩበት እና ዘላቂ ትርጉም የሚያገኙበት እንደሆነ አስረድተዋል።

በዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ በታማኝነት መኖር እንደሚገባ ተናግረው፥ ለዲዮግናጤስ የተጻፈውን ጥንታዊ ደብዳቤ በመጥቀስ፥ ክርስቲያኖች በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ሙሉ በሙሉ መሳተፍ እንዳለባቸው እና ይህም በቄንጥ ወይም በርዕዮተ ዓለምን ሳይማረኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበው፥ ከቁሳዊ ስኬት፣ ደስታ እና ኃይል ይልቅ እምነት እውነተኛ ነፃነትን እና ተስፋን እንደሚሰጥ፥ እንዲሁም ርዕዮተ ዓለም እና ዝንባሌ ቶሎ ብለው ሲጥፉ እውነት ግን ጸንቶ እንደሚቆይ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ከቅዱስነታቸው ጋር ለዋዜማው ጸሎት የተሰበሰቡት ወጣቶች
ከቅዱስነታቸው ጋር ለዋዜማው ጸሎት የተሰበሰቡት ወጣቶች   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ወጣቶች በዲጂታል ዓለም ውስጥ ጨምሮ በኅብረተሰብ ውስጥ የአዎንታዊ ለውጥ ወኪሎች እንዲሆኑ፣ የወንጌልን እሴት እና ውበት ለሌሎች እንዲያስተላልፉ፣ ግዴለሽነትን፣ ዓመፅን እና ሐሰትን በመዋጋት አዲስ የሰብዓዊነት ምልክቶች እንዲሆኑ፣ ፍትህን እንዲፈልጉ እና ሰዎች እንዲያደረጉላቸው የሚፈልጉትን ለሌሎች እንዲያደርጉ አሳስበዋቸዋል።

በመጨረም ወጣቶች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል እውነተኛ ሰው እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበው፥ እምነትን እንደ እምነት ብቻ ሳይሆን በበጎነት የሚገለጽ የአኗኗር ዘይቤ እንዲያደርጉት እና ይህም ታሪክን የመለወጥ ችሎታ ያለው እና ዓለምን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል በጎ ምግባር መሆኑን በመግለጽ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

ቅዱስነታቸው ከዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ቅዱስነታቸው ከዋዜማው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@Vatican Media)
ቅዱስነታቸው የዋዜማውን ጸሎት ከቅዱስነታቸው ጋር ለማድረግ ሲጓዙ
08 Jun 2026, 15:52