ስደተኛው ኦስማን ከአገሩ ጋምቢያ እስከ ካናሪ ደሴቶች ድረስ ያደረገውን ጉዞ ሂደት ተናገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ኦስማን ወደ ካናሪ ደሴት ቴኔሪፍ ሲመጣ የመጀመሪያው ሲሆን፥ ቴኔሪፍ ከስምንቱ የካናሪ ደሴቶች መካከል አንዱ እና ትልቁ ነው። ከስምንት ቀናትን ከወሰደ አደገኛ የመርከብ ጉዞ በኋላ መሬት የረገጠው ኦስማን “ከጋምቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢወጡም እዚህ አይደርሱም” ሲል ተናግሯል።
በኮምቦ ኖርዝ የባሕር ዳርቻ ከሚገኘው መንደሩ የወጣው ኦስማን ችግርን በሚገባ ያውቃል። ሚስቱን ሳሊን፣ የ8 ዓመቷን ካሪን እና የሁለት ከግማሽ ዓመቱን ዩሱፍን ተሰናብቷል። ነገር ግን በባህር ዳርቻ ሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት በቀን የሚያገኘው 4 ዩሮ በቂው አልነበረም።
ለልጆቹ ሲል የማይፈልገውን ሕይወት መረጠ እንጂ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱ ለምንም ዓይነት ሥራ ብቁ አላደረገውም። ስደት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ስለሚያውቅ በወቅቱ የ13 ዓመቱን ታላቅ ልጁን ላሚንን ብቻ ይዞ መሰደድን መርጧል።
የአትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ መድፈር
በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ አባት እና ልጅ ከ156 ሰዎች ጋር በእንጨት ጀልባ ተሳፈሩ። በጀልባው ላይ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች ነበሩ። ኦስማን ስለ ጉዞው አደገኛነት ሲገልጽ፥ ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዱ መድረሻቸው ከመድረሱ ጥቂት ሰዓታት በፊት ሕይወቱን እንዳጣ ጠቅሷል። በመጨረሻም በሰባተኛው እና በስምንተኛው ቀን መካከል ባለው ምሽት ኦስማን የቴኔሪፍ መብራቶች ሲበሩ እና አውሮፕላኖች ወደ አጎራባች ደሴቶች ሲበሩ አየ።
በተለይ ትላልቅ ድንጋያማ ኮረብታዎችን እና የደሴትነት ባህሪ ያላቸውን ምስሎች ማየት አስገረመው። እርሱ የመጣው መልክዓ ምድሩ ሜዳማ ከሆነበት አገር ነው። “ኮረብታዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት አስገርሞኛል” ይላል። ከእግሩ በታች ያለው ደረቅ መሬት እና ከእርሱ ጋር የተያያዘውን የነፃነት ስሜት አስተዋለ።
ወደ ላስ ፓልማስ እንኳን በደህና መጡ
ነገር ግን ጉዞው በዚያ አላበቃም። መጀመሪያ ወደ ላንዛሮቴ ተዛወረ። እዚያም ለሁለት ወራት ቆዩ። አባት እና ልጅ ክሩዝ ብላንካ ፋውንዴሽን በተሰኘ የስፔን ድርጅት ድጋፍ በላስ ፓልማስ ወደሚገኝ የስደተኞች ማዕከል ተወሰደ።
ማዕከሉ በፍራንችስካውያን ወንድሞች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2004 ዓ. ም. የተመሠረተ ነው። ከመጠለያነት በተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት፣ የሥነ-ልቦና እና የህግ ድጋፍ፣ እንዲሁም የቋንቋ ትምህርት እና የሕጻናት ማቆያ አገልግሎት ይሰጣል። ሕጻናት እና አዳጊ ልጆች በላስ ፓልማስ በሚገኙ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ይማራሉ። ይህም ከስፓኒሽ ማኅበረሰብ ጋር ለመዋሃድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። የላሚን ሕይወት በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ በመሆኑ ኦስማን ተደስቷል።
ለሚፈልጉት መንፈሳዊ ድጋፍም ይደረጋል። “ስደተኞቹ በሥነ-ልቦና እና በመንፈሳዊነት እጅግ የተጎዱ ናቸው” ሲል የክሩዝ ብላንካ ፋውንዴሽን ማዕከላት ዋና አስተባባሪ ወንድም ጃሂር ፋሎን ያስረዳል። “መንፈሳዊነታቸው ብዙ ሕመም እና ስቃይን እንደሚያካትት ገልጾ፥ “ተልዕኳችን እነርሱን ማዳመጥ እና ሙሉ ትኩረት መስጠት ነው” ብሏል።
ትኩረታቸው የእምነታቸውን ልምምድ ማረጋገጥ በመሆኑ ምንም ይሁን ምን ነዋሪዎች በአቅራቢያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን መካፈል ወይም በማዕከሉ ውስጥ ረመዳንን ማክበር እንደሚችሉ ገልጿል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት የመጽናት ምንጭ ነው
ኦስማን ሙስሊም ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን በአርጊኔጉዊን ደሴት ካያቸው በኋላ የተሰማው ደስታ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሮ፥ “እምነታችንም በሰው ልጅ ላይ ተመሳሳይ እምነት አለን” የሚለው ኦስማን “ነጭም ጥቁርም ብንሆንም ጉዳት ሲደርስብን የሚፈሰው የደም ቀለም ተመሳሳይ ነው” ብሏል።
ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለስደተኞች እና ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ ከፍተኛ የአቀባበል እና የመዋሃድ ሂደቶችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ለፍራንችስካውያን ፋውንዴሽን ምስጋና ይግባውና ኦስማን እና ልጁ በትክክለኛው መንገድ ላይ ያሉ ይመስላል። በቀድሞው ሥራው አስተናጋጅ የነበረው ኦስማን በማንኛውም ዘርፍ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እኛ ስደተኞች ወደዚህ የመጣነው ማኅበረሰቡን ለማወክ ሳይሆን አብረን ለማደግ እና ሃገሪቱን የበለጠ ወደ ፊት ለማራመድ መሆኑን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ” ብሏል።
ወደፊት በሚወስደው ረጅም ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት ጊዜ እንደሆነ ቢያውቅም በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች እና ሠራተኞች እንግዳ ተቀባይነት በማስረዳት “ቤተሰብ ሆነናል” ሲል ኦስማን ተናግሯል።
