ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሴራ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሴራ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ  (@VATICAN MEDIA) ርዕሰ አንቀጽ

“ወንጌልን ማስፋፋት እና ስደተኞችን መርዳት የቅዱስነታቸው የስፔይን ጉብኝት ዋና ማዕከል ነው”

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አንድሬያ ቶርኔሊ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 5/2018 ዓ. ም. ድረስ በስፔይን ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና ካናሪ ደሴቶች ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እና እንድሁም የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል “ሳግራዳ ፋሚሊያ” አርክቴክት በሆነው አንቶኒ ጋውዲ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ መገኘታቸውን በማስመልከት ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን በሚያደርጉት የሰባት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ዋና ከተማ ማድሪድ፣ ከዚያም ባርሴሎና እና በመጨረሻም ወደ ካናሪ ደሴቶች እንደሚጓዙ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በአውሮፓ የሚያደርጉት ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የአኅጉሪቱ ቤተ ክርስቲያንን የሚያጋጥሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን የሚዳስሱ  ሦስት ደረጃዎች ያሉት ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በቱርኪዬ እና በሊባኖስ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች ተከትሎ ሲሆን፥ እነዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በሁለቱም አገራት ሕዝቦች ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው እና ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጽመችው የቦምብ ጥቃት ለተጎዱት ሰላምን ለማረጋገጥ የተደረጉ ጉብኝቶች  ናቸው።

በተጨማሪም በሞናኮ ያደረጉትን የአንድ ቀን ጉብኝት እና በአፍሪካ የመጀመሪያው የሚስዮናዊነት ንግደት እንዲሆን ፈልገው በአራት የአፍሪካ አገራት ያደረጉትን የአሥራ አንድ ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተከትሎ ሲሆን፥ “የስፔይን ጉብኝታቸው እጅግ ከተከፋፈለ የአውሮፓ ማኅበረሰብ ጋር የሚገኙበት ነው” ተብሏል።

ቅዱስነታቸው በስፔይን ጉብኝታቸው መጀመሪያ ላይ በማድሪድ ከፓርላማ አባላት ጋር የሚሰበሰቡ ሲሆን፥ ይህም ቤተ ክርስቲያን ለፖለቲካ ያላትን አመለካከት እና ለጋራ ጥቅም ያላትን ቁርጠኝነት የምትገልጽበት መልካም አጋጣሚ ይሆናል።

ዛሬ የክርስትና እምነት ወደ ግል እና ውስጣዊ ተሞክሮ ደረጃ ወርዶ በፖለቲካ አሰላለፍ እና በርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከት ምክንያት ከማንኛውም ሙከራ የራቀ ነው። ምክንያቱም በስልጣን መመካት የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮን የሚያደበዝዝ በመሆኑ ወንጌልን በታማኝነት ማወጅ አትችልም። ክርስቲያኖች ማኅበረሰቡን የበለጠ ሰብዓዊ እና ፍትሃዊ ለማድረግ እንዲሁም ለተገለሉት ትኩረት በመስጠት ወንጌልን በተጨባጭ እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል።

በተከፋፈለ እና ግጭት በበዛበት ዘመን አንድነትን እንድትመሰክር የተጠራችው የስፔይን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ ያለፈው ክፍለ ዘመን የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን አሳዛኝ ሁኔታ ከሕዝቦቿ ጋር ሆና መቋቋም ብትችልም አንዳንድ ቁስሎችዋ ዛሬም ሙሉ በሙሉ አልተፈወሱም።

ማንነቱ በታላቅ ክርስቲያናዊ ትውፊት በተቀረጸው ማኅበረሰብ ውስጥ ወንጌልን እንዴት መስበክ ይቻላል? የሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14 ሐዋርያዊ ጉብኝት ውስጥ ቀዳሚ ቦታን ይዟል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባርሴሎና የታነጸውን አስደናቂ የቅድስት ቤተሰብ ባዚሊካን ሲባርኩ በውስጡ የሚገኘው ረጅሙ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ ውበት ባለው ቋንቋ መልስ ሊሰጥ ይችላል።

ቤተ ክርስቲያን ለሁሉ ሰው ዘወትር በሥነ-ጥበብ እና በተለይም በምስሎች ተናግራለች። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የእምነት ትምህርቶች በምስሎች እና በቅርጻ ቅርጾች ሲተላለፉ ቆይተዋል።

የቅድስት ቤተሰብ “ሳግራዳ ፋሚሊያ” ከመቶ ዓመት በፊት የሞተው እና የቅድስና ጥናት በሂደት ላይ የሚገኘው የካታላን አርኪቴክት አንቶኒ ጋውዲ የእምነት እና የጥበብ ፍሬ ለ​​ውብ ቋንቋ ጥሩ ምሳሌ ሲሆን፥ በባዚሊካው ፊት የሚቆም ማንኛውም ሰው በክርስትና እምነት ምንነት ላይ ይጓዛል። ስለዚህ የአንቶኒ ጋውዲ ትምህርት ዛሬ በተለይም የእምነት ስርጭት በተቋረጠበት ዘመናችን፣ በአውሮፓ እና በቤተሰብ ውስጥ ለወንጌል ስርጭት እጅግ ጠቃሚ እና ቀላል የማይባልለት ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፣ በካናሪያ እና ተነሪፍ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ስደተኞችን የሚያጋጥሙ መከራዎችን በቀጥታ እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል። ከባሕር ላይ የሞት አደጋ የተረፉት ወደ አውሮፓ ቢደርሱም አኅጉሪቱ ብዙውን ጊዜ በተቀናጀ እና በተደራጀ መንገድ ለችግሩ ምላሽ መስጠት አልቻለችም። ስፔይን አንዷ ነች።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካናሪ ደሴቶችን ለመጎብኘት ፍላጎት እንደነበራቸው ቢታወቅም እርሳቸውን የተኳቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አሁን እውን አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጀመሩት ሥራ ፍሬ የሆነውን “Dilexi te” ወይም “እኔ ወድጄሃለሁ” በሚል ርዕሥ የተጻፈ ሐዋርያዊ መልዕክት ባለፈው ጥቅምት ማሳተማቸው ይታወሳል። ሐዋርያዊ መልዕክቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እና እኛ ከድሆች፣ ከተናቁት እና በመከራ ውስጥ ከሚገኙት ጋር ባለን ቅርበት መካከል ያለውን ግንኙነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ፥ ዓለምን በኃያላን ሳይሆን በሚሰቃዩት ሰዎች ዓይን፣ ታሪክን በኃያላን ሳይሆን በዝቅተኞች ዓይን፤ እንድንመለከት፣ የታሪክ ክስተቶችን ከብቸኛ እናት፣ ከወላጅ አልባ ሕጻናት፣ ከመጻተኛ፣ ከቁስለኛ፣ ከስደት እና ከሽሽት እይታ አንጻር በመተርጎም ዓለምን ከታች ወደ ላይ መመልከት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ስለዚህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካናሪ ደሴቶች ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ በመካከላችን በሚገኙ ዝቅተኛ ሰዎች ሕያው የስቃይ እውነታ ውስጥ ገብቶ ክርስቲያኖች የወንጌል ምስክርነት እንዲሰጡ እና ሁሉም ሰው ሰው ሆኖ የመቆየት ኃላፊነት እንዲኖረው ጥሪ ያቀርባል።

 

06 Jun 2026, 15:58