ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወጣቶች ታሪክን በፍቅር እንዲለውጡት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን በማድረግ ላይ ባሉት አራተኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ካላቸው አባላት ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመልዕክታቸው የሲቪል እና የሃይማኖት መሪዎች የተለያዩ ትረካዎችን ወደ ጎን በመተው ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን እንዲንከባከቡ እና የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር በትክክል እንዲመለከቱ አሳስበው፥ ወጣቶች እውነተኛ ስብዕናን በመያዝ ታሪክን በፍቅር እንዲለውጡ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ስፔይን ሲደርሱ፥ የመዲናዋ ማድሪድ ጎዳናዎች እርሳቸውን ሊቀበሉ ተስፋ ባደረጉ በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ የአገር ጎብኚዎች እና መንገደኞች መሞላቷ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንጉሥ ፌሊፔ 6ኛ እና በንግሥት ሌቲሲያ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንጉሥ ፌሊፔ 6ኛ እና በንግሥት ሌቲሲያ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።   (@Vatican Media)

ቅዱስነታቸው በስፔይን በሚያደርጉት የስድስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ ቀን ንጉሣዊ ቤተ መንግሥትን በጎበኙበት ወቅት በንጉሥ ፌሊፔ 6ኛ፣ በንግሥት ሌቲሲያ እና በሴት ልጆቻቸው አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንጉሡም ሆኑ ቅዱስነታቸው በስፔይን ሁለት ሺህ ዓመታት የዘልቀውን ረጅም ካቶሊካዊ ባሕል አስታውሰው፥ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ሕዝቡ በማኅበረሰቡ እውነታ እና ታሪክ ውስጥ መከፋፈል እና ልዩነት የሚያመጡ ትረካዎችን ወደ ጎን በማድረግ ውስብስብነትን ፍሬያማ እና ንፁህ በሆኑ መንገዶች እንዲያሸንፍ ጥሪ አቅርበዋል።

መከፋፈል በተስፋፋበት እና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በቀነሰበት በዚህ ወቅት እነዚህን ነገሮች ማለፍ እንደሚገባ አሳስበው፥ “ለእውነት ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሰዎች ኅሊና ውስጥ ፍትህ እና ሰላም እስኪሰርጽ ድረስ ከቦታ ቦታ እንዲንከራተቱ ተደርገዋል” ብለዋል።

ማንም ብቻውን ሊሆን አይችልም

የሰብዓዊ ክብር ጥበቃን እና ለተጋላጭ ሰዎች የሚደረገውን እንክብካቤ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በማድሪድ ሀገረ ስብከት ውስጥ ዕርዳታ በማድረግ ላይ የሚገኘውን “ሴዲያ 24 ሆራስ” የተሰኘ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማኅበራዊ ፕሮጀክት ጠቅሰው፥ ይህ ፕሮጄክት በማድሪድ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከማድሪድ የመጣ በመሆኑ ለሁሉም ሰው መልካም አቀባበል የሚያደርግ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@Vatican Media)

“በዚህ የዕርዳታ መስጫ ማዕከል ውስጥ ማንም ብቸኛ አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሆኖም ምጽዋት መስጠት ከበጎ አድራጎት ጋር ተመሳሳይነት እንደሌለው ገልጸው፥ የግል ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ በማሳሰብ፥ የነፍስሔር ፍራንችስኮስ አስተምህሮ በማስታወስ፥ ሰዎች በእውነት የሚያገለግሏቸውን ሰዎች ዓይን ይመለከቱ እንደሆነ እና ክብራቸውንም ይገነዘቡ እንደሆነ ጠይቀዋል።

ፍርሃት አይዛችሁ!

ቅዱስነታቸው በጉብኝታቸው ቀን ማጠቃለያ ለማድሪድ ወጣቶች በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከከተማው ወጣቶች ጋር ለመገናኘት ወደ ፕላዛ ደ ሊማ የተጓዙ ሲሆን፥ ከሙዚቃ ዝግጅት በኋላ ከጥቂት የወጣት ቡድን አባላት ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር፥ በዛሬው ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ያነሳሱ ቅዱሳንን በማስመልከት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ቅዱስ ዮሐንስ ክሪዞስተም ሕይወት በመመለስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ወጣቶችባደረጉት ንግግር፥ ወጣቶች ለክህነት አገልግሎት፣ ለምንኩስና ሕይወት ወይም ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ለሚቀርብላቸው ጥሪ መፍራት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው ከጥያቄ እና መልስ በኋላ ከአንድ ወጣት በቀረበላቸው መስቀል ላይ ፊርማቸውን ሲያስቀምጡ
ቅዱስነታቸው ከጥያቄ እና መልስ በኋላ ከአንድ ወጣት በቀረበላቸው መስቀል ላይ ፊርማቸውን ሲያስቀምጡ   (@Vatican Media)

ለሌላኛው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፥ ወጣቶች የእግዚአብሔርን ድምፅ ለማወቅ የጽሞና ጊዜ እንዲኖራቸው በማበረታታት፥ “በዚያ የጽሞና ጊዜ ርዕዮተ ዓለም የሚያልፍ መሆኑን እውነት ግን ዘወትር የሚኖር መሆኑን እንረዳለን” ብለዋል።

የጽሞና እና የእውነት ፍለጋ አንድ ሰው ብቻውን የሚያደርገው እንዳልሆነ ተናግረው፥ “ማንም ሰው በኢየሱስ ብቻ እንደማያምን ማስታወስ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል። ወጣቶች በዚህ የዓመፅ፣ የጦርነት እና የግዴለሽነት ጉዞ መካከል አዲስ የሰብዓዊነት ምልክት እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወጣቶች በተልዕኮ ላይ እውነተኛ እንዲሆኑ፣ ከመልክ ይልቅ ሥጋ እና ደም ያላቸው እንዲሆኑ በማሳሰብ፥ የካቶሊክ እምነት በበጎ አድራጎት የተሟላ ሕይወት መሆኑን እና ወጣቶች በሙሉ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የወንጌል ልኡካን እንዲሆኑ አደራ ብለው፥ በመጨረሻም ይህ በጎነት ታሪክን ከማንኛውም ነገር በላይ የሚቀይር መሆኑን በመናገር ወጣቶችም ታሪክን መለወጥ እንደሚችሉ እና በፍቅር እንዲያደርጉት በማሳሰብ መል ዕክታቸውን ደምድመዋል።

ቅዱስነታቸው በቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ቅዱስነታቸው በቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)
08 Jun 2026, 15:37