ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሁሉም ሰው የዕለት እንጀራ እንዲያገኝ መጸለይ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ጸልዩ” በሚለው ወርሃዊ ዓለም አቀፍ የጸሎት ማስተባበሪያ የቪዲዮ መልዕክታቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞች እና እህቶች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን በሐዘን አስታውሰው፥ ሁሉም ሰው ምግብ እንዲያገኝ በግንቦት ወር ካቶሊካዊያን በሙሉ በጸሎት እንዲተባበሯቸው አደራ ብለዋል።
በማዕዶቻችን ላይ ብዙ ምግብ እየተበሸ ይገኛል” በማለት በሐዘን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “አዲስ ግንዛቤ በልባችን ውስጥ እንዲፈጠር፣ በየዕለቱ ለምናገኘው ምግብ ምስጋናን እንድናቀርብ፣ ከሌሎች ጋር በደስታ መጋራትን እና ከአንተ ዘንድ የተላከልን ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ የምድርን ፍሬዎች ለመንከባከብ አግዘን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
“ኢየሱስ ሆይ! በማኅበረሰቦቻችን ውስጥ የሚታየው የራስ ወዳድነት አመክንዮን ወደ አንድነት ባሕል መለወጥ እንድንችል አግዘን” ሲሉ ጸልየው፥ ይህም ግንዛቤዎቻችንን፣ የምግብ ማከማቻዎቻችንን፣ ጨዋነት የተሞላበትን እና ኃላፊነት የሚሰማው የአኗኗር ዘይቤን እንደሚያካትት አስረድተዋል።
“የምትወደውን ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቆረሰውን ዳቦ ለዓለም የላክልን እግዚአብሔር ሆይ! ለፍትህ የተራበ እና ለወንድማማችነት የተጠማ አዲስ ልብን ስጠን፤ ማንም ሰው ከጋራ ማዕድ እንዳይገለል፣ መንፈስህ የዕለት ጉርስን እንደ ፍጆታ ሳይሆን እንደ ኅብረት እና እንክብካቤ ምልክት እንድንመለከተው ያስተምረን” ሲሉ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
የምግብ ቀውስ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ነው
በዓለም የምግብ ፕሮግራም የ2026 (እአአ) እይታ መሠረት፥ በዚህ ዓመት 318 ሚሊዮን ሰዎችን የምግብ ቀውስ ወይም ከዚያ የከፋ ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው ገልጾ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ግጭት ከዚህ ዓመት አጋማሽ በፊት ተጨማሪ 45 ሚሊዮን ሰዎችን ለከባድ ረሃብ ሊዳርግ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ ዳይሬክተር የሆኑት አባ ክሪስቶባል ፎኔስ ከቪዲዮ ቅንብር ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፥ የጸሎት ዓላማው እጅግ ግልጽ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ልብ የመነጨ መሆኑን ተናግረው፥ በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ምግብን የመሰለ አስፈላጊ እና ሰብዓዊ ነገርን ማግኘት አለመቻላቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሁሉም ሰው ለችግሩ ግድየለሽ ሆኖ እንዳይቀጥል ነገር ግን በቅድሚያ በጸሎት ከዚያም በተጨባጭ የርኅራሄ ምልክቶች ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁትም ለዚህ ነው” ሲሉ አባ ክሪስቶባል ተናግረዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር በኅብረት የሚደረግ ጸሎት
በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ፥ አንድ አምላክ አሜን።
የፍጥረት ጌታ ሆይ! የፍቅርህ እና የልግስናህ ምልክት እንዲሆን ለም ከሆነች ምድር ጋር የዕለት እንጀራን ሰጥተኸናል።
ዛሬ ብዙ ምግብ እየባከነ ባለበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን እናያለን።
ለእያንዳንዱ የዕለት ምግባችን ማመስገንን፣ ከሌላቸው ጋር በደስታ መካፈልን እና ከአንተ ዘንድ የተሰጠን የምድር ፍሬ ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉ ሰው መሆኑን አውቀን እንድንከባከብ በልባችን ውስጥ አዲስ ግንዛቤ አሳድርልን።
እግዚአብሔር አባት ሆይ! ራስ ወዳድነታችንን ወደ መረዳዳት ባሕል የመቀየር ችሎታ ስጠን።
ማኅበረሰባችን ግንዛቤ ማስጨበጫ ጥረቶችን እንዲያደርግ፣ ምግብን ሳያበላሽ የሚያቆይበትን እና ኃላፊነት በሚሰማው የአኗኗር ዘይቤ ተጨባጭ የርኅራሄ ምልክቶችን እንዲያሳድግ አግዝ።
ለዓለም የሕይወት እንጀራ እንዲሆን ብየምትወደውን ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶን የላክልን እግዚአብሔር ሆይ! ለፍትህ የሚራብ እና ለወንድማማችነት የሚጠማ አዲስ ልብ ስጠን።
ማንም ሰው ከጋራ ማዕድ እንዳይገለል፣ እንጀራን ፍጆታ ሳይሆን የአንድነት እና የመረዳዳት ምልክት አድርገን እንድንመለከተው መንፈስ ቅዱስህ ያስተምረን። አሜን።
