ለእኩለ ቀን የእሑድ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡ ምዕመናን ለእኩለ ቀን የእሑድ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡ ምዕመናን  (@VATICAN MEDIA )

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዓመፅ እና በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ጋዜጠኞችን አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 3 የሚከበረውን ዓመታዊ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በማስታወስ፥ በጦርነት እና በዓመፅ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ በርካታ ጋዜጠኞችን እና ዘጋቢዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ ግንቦት 3 (እአአ) በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት “ዩኔስኮ” የተደገፈ ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን እንደ ሆነ ገልጸዋል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የፕሬስ ነፃነት እንደሚጣስ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንድ ጊዜ በግልጽ በሌሎች ጊዜያት በድብቅ መንገዶች እንደሚጣስ ገልጸው፥ “የጦርነቶች እና የዓመፅ ሰለባ የሆኑ በርካታ ጋዜጠኞችን እና ዘጋቢዎችን በጸሎታችን እናስታውስ” ብለዋል።

አስተማማኝ መረጃን ማድረስ፣ ተጠያቂነት መኖር፣ ውይይት እና እምነት፣ የፕሬስ ነፃነትን እና የገለልተኛ ጋዜጠኝነት ተደራሽነትን ማሳደግ ለሰላም፣ ለኢኮኖሚ ማገገም፣ ለዘላቂ ልማት እና ለሰብዓዊ መብቶች ቁልፍ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት “ዩኔስኮ” ይገልጻል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዚሁም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2022–2025 ዓ. ም. ድረስ ያደረገውን ጥናት መሠረት በማድረግ ባወጣው ሪፖርቱ፥ የፕሬስ ነፃነት እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ ከ2012 ዓ. ም. ወዲህ ከፍተኛ ውድቀት እንዳጋጠመው ገልጾ፥ ይህም በ20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ያልተረጋጋ እና በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች እና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከታየው ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደሆነ አስረድቷል።

የመረጃ ማጭበርበር እና በተንኮል አዘል ተዋናዮች የሚደረግ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም እምነትን እና ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቆ፥ በተመሳሳይም እነዚህ ጉዳዮች ሊነገሩ እንደሚችሉ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. የፕሬስ ነፃነት አስፈላጊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጊዜ መሆኑን የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት “ዩኔስኮ” ተናግሯል።

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ጉባኤ “የሰላምን የወደፊት ሁኔታ መቅረጽ” በሚል መሪ ጭብጥ፥ ሰኞ ሚያዝያ 26/2018 ዓ. ም. በዛምቢያ መዲና ሉሳካ እንደሚካሄድ እና ይህም በበይነ መረብ በኩል የሚቀርቡ በርካታ ዝግጅቶችን እንደሚያካትት ታውቋል።

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የፕሬስ ነፃነትን ለማስታወስ የሚረዱ መሠረታዊ መርሆዎችን በማቅረብ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታን ለመገምገም፣ የሚዲያ ነፃነትን ለመከላከል እና በሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ላጡ ጋዜጠኞች ክብር ለመስጠት ዕድልን እንደሚሰጥ ታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት “ዩኔስኮ” በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በባህል እና በመረጃ ዘርፎች ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የተቋቋመ ልዩ ኤጀንሲ እንደሆነ ይታወቃል።

ለ “ሚተር” ማኅበር የቀረበ ሰላምታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ሚያዝያ 25/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት  ምዕመናን  ቡራኬያቸው የሰጡ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ለሰላሳ ዓመታት ሕጻናትን ከጥቃት ሲከላከል የቆየ “ሚተር” የተሰኘ ማኅበር አባላት እንደሚገኙ ታውቋል። አባላቱ ቤተ ክርስቲያን እና ሲቪል ማኅበረሰብ በትምህርት ዘርፍ ተጎጂዎችን በመርዳት እና በመከላከል ጥረቶች ላይ ለማሳተፍ ሲሠራ ​​የቆዩ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለዚህ ሥራቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ያለፈው ዓርብ የገባው ግንቦት ወር የእመቤታችን ወር መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በተለይም የመቁጠሪያ ጸሎትን በኅብረት ማቅረብ መላው ቤተ ክርስቲያን በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በመሰብሰብ የሚያገኙት ደስታ የሚታደስበት ጊዜ እንደሆነም አስረድተዋል። “በኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት እና በመንፈስ ቅዱስ መውረድ መካከል ያሉት ቀናት ደቀ መዛሙርቱ በኅብረት ሆነው መንፈስ ቅዱስን ለመለመን መሰብሰባቸውን ያስታውሱናል” ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመካከላቸው ሆና በልቧም የሁሉንም ጸሎት የሚያነቃቃውን እሳት ትጠብቅ እንደ ነበር ገልጸው፥ “በተለይም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ኅብረት እና በዓለም ላይ ሰላም እንዲኖር ያለኝን ፍላጎት በአደራ እሰጣችኋለሁ” ብለዋል።

 

04 May 2026, 16:49