ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የሰማዩን ቤት በምድር ማግኘት ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሚያዝያ 25 /2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ካደረሱ በኋላ ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል።ቅዱስነታቸው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በመሩበት ወቅት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “የሰማዩን ቤት በምድር መጠበቅ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። እምነት ልባችንን ሁሉን ማግኘት ከሚል እና ከስግብግብነት ስሜት ነጻ ያደርጋል” ሲሉ አስረድተው፥ ክርስቲያኖች ወንድማማችነትን ማሳደግ እና ሰላምን መፍጠር ጥሪያቸው መሆኑን በተግባር እንዲያሳዩ አደራ ብለዋል።
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አርፍዳችኋል! መልካም ዕለተ ሰንበትን እመኝላችኋለሁ! በዚህ በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት ልክ እንደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሕማማቱ ሙሉ ትርጉም የሚሰጡ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት እንመለከታለን። እነዚህም የፍቅሩን፣ የሞቱን እና የትንሣኤው ብርሃን ሙሉ ትርጉም የሚገልጹ ናቸው። በአንድ ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ የራቁ ወይም ያስጨንቃቸው የነበረው ነገር አሁን ወደ አእምሮአቸው ተመልሶ ልባቸውን በደስታ እና በተስፋ ይሞላል።
በዚህ እሁድ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገውን ውይይት ያስታውሰናል። በተለይም ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ በብርሃነ ትንሣኤው ምስጢር ውስጥ እኛን የሚያሳትፍ ቃል እንሰማለን። ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ ‘ሄጄም ሥፍራ ሳዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትኖሩ ዳግመኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ’ (ዮሐ. 14፡3)። ስለዚህ ሐዋርያት እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው ቦታ እንዳለው ደርሰውበታል። ከእነርሱ መካከል ሁለቱ ይህንን ቀደም ሲል ከኢየሱስ ጋር በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነት ወቅት ተረድተዋል። ኢየሱስም እንዲከተሉት እና ከሰዓት በኋላም የሚኖርበትን ቦታ እንዲጎበኙ ጋበዛቸው (ዮሐ. 1፡39)። ኢየሱስ ሞትን እየተጋፈጠ ቢገኝም አሁንም ስለ ቤት ይናገራል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ የተናገራቸው ቤት ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ ያለው ትልቁ ቤት የአባቱ እና የአባታችን ቤት ነው። ክፍሎችን ለሌሎች ሰዎች እንደሚያዘጋጅ አገልጋይ ወልድ ራሱን ይገልጻል። ስለዚህም እያንዳንዱ ሰው ወደ ቦታው ሲደርስ የራሱ ክፍል ዝግጁ ሆኖ እንደሚያገኝ እና ዘወትር ሲናፍቀው የነበረውን እንዳገኘ እንዲሰማው ያደርጋል።
ውድ ወዳጆቼ ሆይ! አሁን በምንኖርበት በዚህ አሮጌው ዓለም ውስጥ ትኩረታችንን የሚስቡት ለየት ያሉ ቦታዎች ለጥቂቶች ብቻ የተዘጋጁ ነገር ግን ሌሎች ሊገቡባቸው የማይችሏቸው ቦታዎች ናቸው። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶ ወደሚመራን አዲስ ዓለም ውስጥ የመግባት መብት በሁሉም ሰው እጅ ውስጥ ነው። ይህ ለሁሉም ሰው ክፍት የሆነው ቦታ ደስታን የሚሰጥ ነው። ምስጋና የፉክክር ቦታን ይወስዳል፤ ሌላውን በእንግድነት መቀበል መገለልን ያሸንፋል፤ የሃብት መብዛት ከእንግዲህ ወዲህ ለኑሮ አለመመጣጠን ዋና መለኪያ አይሆንም። ከሁሉም በላይ ማንም ሰው እርስ በርስ ይተዋወቃል። ማንም ከማንም አይሰወርም። ሞት የአንድን ሰው ስም እና ትውስታ ሊያጠፋ ይችል ይሆናል ነገር ግን በእግዚአብሔር ሁሉም ሰው ሙሉ በሙሉ የራሱን ማንነት ይይዛል። በእውነት ይህ በሕይወታችን በሙሉ የምንፈልገው ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ትኩረት እና እውቅና ለማግኘት ስንል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች ነን።
ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ‘ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ’ ይለናል (ዮሐ. 14:1)። እንግዲህ ሚስጢሩም ይህ ነው! ሁሉ ነገር ከማግኘት እና ከስግብግብነት፣ በሁሉም ዘንድ ትኩረትን ለማግኘት ስንል የክብር ቦታን መፈለግ አለብን ከሚለው ጭንቀት ልባችንን ነጻ የሚያደርገው ይህ እምነት ነው። በእውነተኛነት እያንዳንዱ ሰው አስቀድሞ በእግዚአብሔር ምሥጢር ውስጥ ማለቂያ የሌለው ዋጋ አለው። ኢየሱስ እንደወደደን እርስ በርሳችን በመዋደድ ይህን ግንዛቤ እርስ በርሳችን እንጋራለን። አዲሱ ትእዛዝ ይህ ነው። በዚህ መንገድ የሰማዩን ቤታችንን በምድራችን ውስጥ በማግኘት ወንድማማችነት ማሳደግ እና ሰላምን መፍጠር የሁላችን ጥሪ መሆኑን ለሁሉም እንገልጻለን። በእርግጥም በፍቅር አማካይነት በበርካታ ወንድሞች እና እህቶች መካከል እያንዳንዱ ሰው በልዩ ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን ይገነዘባል።
እንግዲህ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ለሁሉም ክፍት እና ለሰው ልጅ በሙሉ ትኩረት የሚሰጥ እንዲሆን እጅግ ቅድስት እና የቤተ ክርስቲያን እናት ወደ ሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታችንን እናቅርብ።”
