ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በሳህል ክልል አገራት የሰላም እና የልማት ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሐድ ግንቦት 2/2018 ዓ. ም. ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በሰሜን አፍሪካ የሳህል ክልል አገራት ውስጥ ያለው የሰላም እና የልማት ሁኔታ ያሰጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሳህል ክልል በተለይም በቻድ እና በማሊ ውስጥ የሽብር ጥቃቶች መከሰታቸውን የሰሙት፥ ከሳህል ክልል አገራት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን ተወካዮች ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት እንደ ነበር ታውቋል።
በሽብር ጥቃት የተጎዱትን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፥ በአካባቢው ለሚሰቃዩት በሙሉ ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ፥ ሰላምን ለማስፈን ቀጣይነት ያለው ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
“ሁሉም ዓይነት ዓመፅ እንደሚቆም ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው፥ “በዚያ ተወዳጅ ምድር ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ አበረታታለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሥነ-ምህዳራዊ እና ደረቃማ የአየር ንብረት ሁኔታ በተጨማሪ ክልሉ በውስጣዊ አለመረጋጋት እና በውጫዊ ተጽዕኖ የተጎዳ ጂኦ-ፖለቲካዊ አካባቢ እንደ ሆነ ይታወቃል።
በተደጋጋሚ የሚከሰተው የአየር ንብረት ቀውስ፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት እንዲሁም ሙስና፥ ለመፈንቅለ መንግሥት፣ ለአመጽ እና ለሽብርተኝነት ምክንያት መሆኑ ታውቋል።
አለመረጋጋት፣ ሽብርተኝነት እና ሰብዓዊ ቀውስ
አመጽ ፈጣሪ አክራሪ ቡድኖች በሳህል ዙሪያ ባሉት አገራት ውስጥ ያላቸውን ቦታ እያሰፉ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የሰብዓዊ ቀውስ አደጋ እያባባሰው እና በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን ሰፊ ያለመረጋጋት ስጋት እያሳደገው እንደሚገኝ ታውቋል።
ከሴኔጋል እስከ ኤርትራ ድረስ ያለው የሳህል አገራት ክልል ለአሥርተ ዓመታት በተደራረቡ የደህንነት፣ የፖለቲካ እና የአየር ንብረት ጫናዎች ሲገጥመው መቆየቱ ይታወቃል።
እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ደካማ የመንግሥት ተቋማት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እና እየተባባሰ የመጣው የአካባቢ ውጥረት በየጊዜው ድንበሮችን አቋርጦ የሚሄድ የግጭት ዑደቶችን ማባባሱ ታውቋል።
በመካከለኛ ማሊ ውስጥ ሐሙስ ሚያዝያ 29/2018 ዓ. ም. በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ጥቃቶቹ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በገዢው ጁንታ ላይ የተፈጸሙ የተቀናጁ ጥቃቶችን ተከትሎ፥ ከአልቃይዳ አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ከተባለው “JNIM” የተፈጸሙ መሆናቸው ታውቋል።
በምዕራብ አፍሪካ የሳህል ክልል አገራት ደህንነት የሚከታተል የጋዜጠኞች መረብ “WAMAPS” በመጀመሪያ ቆጠራው ከ50 በላይ የመንደሩ ነዋሪዎች መሞታቸውን እና ያሉበት እስካሁን የማይታወቅ ሌሎች ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ የጸረ-ሽብር ተልዕኮ መቀነሱ እና በክልሉ ያለው ትብብር መዳከሙ በገጠር አካባቢዎች በሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ በሚደረግ ቁጥጥር ክፍተት መፍጠሩ ታውቋል።
የሳህል ክልል አገራት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ወደ ሰሜን አፍሪካ እና ወደ አውሮፓ ለሚጓዙ ስደተኞች ዋና መተላለፊያ መንገድ ሆኖ ቀጥሏል።
እየሰፋ የመጣው አዲስ ዓመፅ መፈናቀልን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል እና በባሕር ዳርቻ ባሉት አገራት እና በአውሮፓ መዳረሻዎች ላይ ጫናን ሊፈጥር እንደሚችል ተንታኞች አስጠንቅቀዋል።
