ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኔፕልስ ከተማ የሰላም መወያያ መድረክ ልትሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሐዋርያዊ መንበር ሥልጣናቸው የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያን ባከበሩበት ሚያዝያ 30/2018 ዓ. ም. በሁለቱ የጣሊያን ከተሞች፥ ፖምፔይ እና ኔፕልስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ መንበራቸው ተመልሰዋል። ጉብኝታቸውን ባጠናቀቁባት ኔፕልስ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በፍትህ፣ በአንድነት እና በማኅበራዊ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያን ባከበሩበት ዓርብ ዕለት ወደ ፖምፔይ እና በአቅራቢያው ወደሚገኘው ኔፕልስ ከተማ በመጓዝ በማዕከላዊ ኔፕልስ ከተማ በሚገኝ የፕሌቢሺቶ አደባባይ ከተሰበሰቡት በግምት ወደ 50,000 ከሚደርሱ ሰዎች ጋር ተገናኝተው ሰላምታቸውን በማቅረብ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ አደባባዩ ሲደርሱ ለሲቪል ባለስልጣናት፣ ለከተማዋ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ዶሜኒኮ ባታግሊያ እና ለምእመናን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በንግግራቸውም በፍትህ ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ ለውጥ፣ አንድነት እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኔፕልስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሲገናኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኔፕልስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

በውበት እና በቁስል የተመሰለች ከተማ

ስለ ኤማውስ ደቀ መዛሙርት በሚናገረው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማሰላሰል ባሰሙት ንግግርም፥ ኔፕልስ በሚያስደንቅ ውበት እና በጥልቅ ቁስሎች የምትታወቅ ከተማ እንደሆነች ገልጸው፥ ከከተማው የሚወጡ የውበት፣ የድህነት፣ የፍርሃት እና የመገለል ስሜት ድምጾችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመንገድ ላይ ካገኙት ከደከሙ እና ተስፋ ከቆረጡ ደቀ መዛሙርት ጋር አነጻጽረዋል።

ብዙውን ጊዜ በድካም፣ በግዴለሽነት እና በማኅበራዊ መከፋፈል አውድ ውስጥ የሚገኝ የኔፕልስ ከተማ እንደገና ትርጉም  እንዲያገኙ ዜጎችን ጋብዘው፥ ኔፕልስን ያጋጠመው እና እያደገ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ ከኑሮ አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ወደ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ያልተለወጥ መሆኑን አስታውሰዋል።

ሥራ አጥነት፣ ትምህርት ማቋረጥ፣ የአገልግሎት እጥረት እና የተደራጀ ወንጀል ተጽዕኖ ከተማውን ከሚነኩ ችግር ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሆኑ ጠቁመው፥ በዚህ አውድ ውስጥ፣ እምነትን፣ ደህንነትን እና የተለያዩ መልካም ዕድሎችን ወደነበሩበት ለመመለስ የመንግሥት ተቋማት መኖር አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ጠንካራ የዕለት ተዕለት ሠራተኞች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለፍትህ፣ ለእውነት እና ለክብር በጸጥታ የሚሰሩትን የኔፕልስ ከተማ በርካታ ጠንካራ ሰራተኞችን ወንዶች እና ሴቶችን አወድሰው፥ ጥረታቸው አንድ ላይ ሆኖ መላውን ማኅበራዊ መዋቅር የሚያጠናክር መልካም የጋራ ትስስር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ በከተማው ውስጥ የኅብረት ትስስር መሆኗን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በተለይም የሲቪል ተቋማትን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና የሲቪል ማኅበረሰብን በሚያካትት የትምህርት ስምምነት ላይ ያላትን ከፍተኛ ሚና አጉልተው በመግለጽ፥ ይህ ትብብር ለከተማዋ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የጋራ ተልዕኮ በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት አጥብቀው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በከተማው አደባባይ ለተገኙት ንግግር ሲያደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በከተማው አደባባይ ለተገኙት ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

የሰላም መወያያ መድረክ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የንግግራቸው ማዕከላዊ ጭብጥ የሆነውን ሰላም በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኔፕልስ ውበቷን በፎቶግራፍ የምታሳይ ከተማ ብቻ ሳትሆን ነገር ግን የሰላም መወያያ መድረክ እንድትሆን መጠራቷን ገልጸው፥ እርቅ በዕለት ተዕለት ግንኙነቶች፣ በተጨባጭ የፍትህ እና የትምህርት ተግባራት የሚገነባ መሆኑን በማስረዳት፥ ፍትህ ያለ ሰላም እና ያለ በጎ አድራጎትም የተሟላ ሊሆን እንደማይችል አረጋግጠዋል።

በተጨባጭ የሚገለጹ የተስፋ ምልክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ቅዱስነታቸው፥ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት እና ለተቸገሩት ሰዎች የሚዘጋጅ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ጨምሮ ለእንክብካቤ እና ለአዲስ ሕይወት ጅምር የሚያግዙ ቦታዎች የሰላም ሕያው መግለጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተሃድሶ ምልክቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንዲሁም ኔፕልስን በባህል እና በሃይማኖት መካከል ለሚደረግ ውይይት ዋና መድረክ ለማድረግ የተደረገውን ጥረት አድንቀው፥ የከተማዋን ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የመቀበል ረጅም ባሕል አስታውሰው፥ ይህም ድንገተኛ ምላሽ ሳይሆን የእርስ በርስ ግንኙነት እና የጋራ መበልጸጊያ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ወጣቶችን ሚና በማስመልከት በተደጋጋሚ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወጣቶች ለኅብረተሰቡ ሸክም ከመሆን ይልቅ የተሃድሶ ሂደት ዋና ተዋናይ መሆናቸውን ተናግረው፥ ከባሕላዊ ውጥኖች እስከ ቁምስና ተነሳሽነቶች እና የበጎ አድራጎት አገልግሎቶች ድረስ የኔፕልስ ከተማ ወጣቶች የታደሰች ከተማ እና የታደሰች ቤተ ክርስቲያን ምልክቶች እንደሆኑ ተናግረዋል።

በጉብኝታቸው ማጠቃለያም፥ የኔፕልስን ከተማ ሕዝብ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የከተማዋ ተወዳጅ ጠባቂ ለሆነው ቅዱስ ጄናሮ አማላጅነት በማቅረብ፥ ሕዝቡ በድፍረት እና በተስፋ አብሮ እንዲጓዝ ብርታትን ተመኝተውለታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሕዝቡ ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሕዝቡ ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ   (@Vatican Media)

 

09 May 2026, 11:31