ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ እግዚአብሔር ጥላቻን እንዲያረግብ እና የዓለም መሪዎች ልብ እንዲከፍት ጸለዩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጣሊያን ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ለማድረግ የደቡብ ጣሊያን ከተማ ወደ ሆነች ፖምፔይ ተጉዘዋል። ቅዱስነታቸው በፖምፔይ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፥ በአገራት ውስጥ ከባድ ጥፋት እያስከተሉ ያሉ በርካታ ጦርነቶች መኖራቸውን አስታውሰው፥ “የእግዚአብሔር ምሕረት ልባችንን እና ዓለማችንን በሰላም ይሙላው” ሲሉ ጸሎታቸውን አድርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓርብ ሚያዝያ 30/2018 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተሞችን ፖምፔይ እና ኔፕልስ በመጎብኘት የሐዋርያዊ መንበር ሥልጣናቸውን የመጀመሪያ ዓመት አክብረዋል። በፖምፔይ በሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ላይ መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ ከአንድ ዓመት በፊት የፖምፔይ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ለሐርያዊ መንበር መመረጣቸውን አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ሐዋርያዊ አገልግሎቴን በቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ ሥር ለማድረግ ወደዚህ ሥፍራ መምጣት ነበረብኝ” ሲሉ  ተናግረው፥ “ከዚህም በላይ ሊዮ የሚለው ስማቸው ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ጥቅም ሰፊ አስተምህሮዎችን ያዘጋጁት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ፈለግ እንድከተል ያደርገኛል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ79 ዓ. ም. በቬሱቪየስ ተራራ ላይ የሚገኘውን የቅዱስ ባርቶሎ ሎንጎ እና የባለቤታቸው ማርያና ፋርናራሮ ደ ፉስኮን ውርስ አስታውሰው፥ ይህ ውርስ በቬሱቪየስ ተራራ ላይ የተከሰተ ፍንዳታ ታላቅ ሥልጣኔ የታየበት እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2003 ዓ. ም. በተከበረው የመቁጠሪያ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ ቤተ መቅደሱ የመጡት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቃላትን በማስታወስ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ዛሬ ልክ እንደ ጥንታዊው ፖምፔይ ዘመን ከክርስቲያናዊ እሴቶች ለሚርቅ እና ትዝታውንም ለሚያጣ ማኅበረሰብ ክርስቶስን መስበክ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ወደ ብስራተ ገብርኤል ጸሎት የተመለሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ጸሎት የደስታ ግብዣ እንደሆነ ተናግረው፥ የመልአኩ ቃላት የእግዚአብሔር ምሕረት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በኃጢአት ወደ ቆሰለው ዓለማችን መምጣቱን አስታውሰው፥ እንዲሁም ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሱስን ለመቀበል በሚወስደው መንገድ ላይ ቤተ ክርስቲያንን እንደምትመራ እና ኢየሱስንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን የወለደች እርሷ እንደሆነች አስረድተዋል።

“የመቁጠሪያ ጸሎትን ስናቀርብ ለእመቤታችን የምናደርጋቸው የፍቅር ተግባራት ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመለስ እና የክርስትና ሕይወት ምንጭ እና ጫፍ ወደሆነው ወደ ቅዱስ ቁርባን የሚያመጣን በመሆኑ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እናድሳለን” ብለዋል።

“የመቁጠሪያ ጸሎት የእመቤታችን ማርያም መልክ ቢኖረውም ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ቁርባን ልብ አለው” ሲሉ አስረድተው፥ በርካታ ክርስቲያኖች በመቁጠሪያ ጸሎት መባረካቸውን አስታውሰው፥ አክለውም የመቁጠሪያ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የክርስቲያን ሥነ-መለኮት የያዘ እና ምስጢራዊ ከፍታዎችን መድረስ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።

በድንግል እናቱ ርህራሄ ከሚነገረው ቅዱስ ስሙ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ምንድን ነው?” በማለት ጠይቀው፥ መዳን የምንችለው በሌላ በማንም ሳይሆን በስሙ እንደሆነ በማስረዳት፥ የመቁጠሪያ ጸሎት ልባችንን ዓለምን ለሚያስፈልጉት ነገሮች በተለይም የቤተሰብን  እና የሰላምን አስፈላጊነት እንደሚያመለክተው ተናግረዋል።

በዓለማችን ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ በርካታ ጦርነቶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህን ጦርነቶች ለማስቆም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ የሆኑ አዲስ ቁርጠኝነቶች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰላም በልባችን ውስጥ እንደሚወለድ ገልጸው፥ “በየቀኑ የሚደርሰንን የሞት ምስሎችን ችላ ማለት ስለማይቻል፥ ሁሉም ሰው ለሰላም የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያቀርብ በመጋበዝ፥ “በዚህም የእግዚአብሔር መለኮታዊ የፍቅር ኃይል ዓለምን ሊያድን ይችላል” ብለዋል።

“በእመቤታችን ማርያም አማላጅነት ከሰላም አምላክ የሚፈስ ምሕረት ልብን የሚነካ፣ ቂምን እና ጣልቻን የሚያስወግድ እና የወንድማማችነት ጥላቻ የሚሸከም ይሁን” ብለዋል።

 

08 May 2026, 18:25