ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የዘወትር መተማመኛችሁ ፈጽሞ የማይተወን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ያሳሰቡት ዓርብ ሚያዝያ 30/2018 ዓ. ም. የፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የበጎ አድራጎት ድርጅትን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን ይህም ለሐዋርያዊ መንበር በተመረጡበት የመጀመሪያ ዓመት ወደ ፖምፔይ ከዚያም ወደ ኔፕልስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት እንደ ሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የድርጅቱ በጎ ፈቃደኞችን ለልግስናቸው እና ለእምነታቸው ምስጋናን በማቅረብ፥ ይህን ሐዋርያዊ ጉብኝት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ቅድስናውን ባወጁት የባርቶሎ ሎንጎ ፈለግ በመከተል መሆኑ እጅግ እንዳስደሰታቸው አስረድተው፥ “የመቁጠሪያ እመቤታችን እና ቅዱስ ባርቶሎ በሁሉም የዕድሜ ክልል እና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ወደ ሰላም እና ወደ ስምምነት የሚመራ አንድ የፍቅር ምንጭ ሥር የሚሰበስቡበት ይህ ሥፍራ የጸጋ ሥፍራ ነው” ሲሉ ጠርተውታል
የኢየሱስ ትንሣኤ ኃይል በየቀኑ የሚለማመዱት ነው
ቅዱስ ባርቶሎ ሎንጎ “የፖምፔይ ሸለቆን ልብን የሚያሞቅ የፍቅር፣ የእምነት እና የልግስና ድል” ብሎት እንደሚጠራው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ እውነታው አሁንም ሕያው እና የሚታይ መሆኑን ተናግረው፥ “የቤተ መቅደሱ በጎ አድራጎት ሥራዎች የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል በየቀኑ የሚለማመዱበት፣ ልብን በፍቅር ወደ ወንጌል ሕይወት የሚመልስ ነው” ብለው፥ “የበጎ አድራጎት ቤተ መቅደስ እና የእምነት ቤተ መቅደስ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው” ሲሉ በማስረዳት፥ ጸሎት ሰዎችን በእንግድነት መቀበልን፣ ማፍቀርን፣ ማገልገልን እና ለጋስ መሆንን እንደሚያበለጽግ ተናግረው፥ ፍቅር ከእያንዳንዱ ጥረት እና ግምት በላይ የሚሄዱ ተአምራትን ሊያከናውን እንደሚችል ገልጸዋል።
የክርስቶስን ፊት በሁሉም ሰው ውስጥ ማየት
ቅዱስ ባርቶሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፖምፔይ ሸለቆ ሲደርስ በታላቅ ድህነት የተጠቃች ምድር ማግኘቱን ለቤተ መቅደሱ የበጎ አድራጎት ድርጅት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጥቂት ድሃ ገበሬዎች ብቻ በሚኖሩበት፣ በወባ በሽታ እና በወንበዴዎች በሚሰቃዩበት ቦታ እንኳን ቅዱስ ባርቶሎ ሎንጎ በሁሉም ሰው ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ማየት እንደቻለ ተናግረው፥ በቅዱስ ባርቶሎ ርህራሄ ምክንያት የእግዚአብሔርን ልብ ለአዋቂዎችም ሆነ ለልጆች በተለይም ወላጅ ለሌላቸው ልጆች እና ለእስረኞች መገለጡን አስታውሰዋል።
ጸሎት የሁሉም ነገር መሠረት ነው
ይህ ቦታ ለክርስቲያናዊ አምልኮ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርን የሚሰጡበት የክርስትና ሕይወት ማዕከል ሆኖ መቀጠሉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ጸሎት የሁሉ ነገር መሠረት እንደሆነ እና በተለይም የመቁጠሪያ ጸሎት ሌላውን ነገር በሙሉ እንዲቻል የሚያደርግ የተደበቀ ኃይል ነው” ብለዋል።
ይህን ጥንታዊ እና ውብ የሆነውን አምልኮ ሕያው ማድረግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምዕመናን በሙሉ ይህንን ጥንታዊ እና ውብ የሆነውን መንፈሳዊ አምልኮ ሕያው በማድረግ ወደ ሌሎች ሥፍራዎችም እንዲያሰራጩት አሳስበው፥ “የኢየሱስ ክርስቶስን ምስጢራዊ ሕይወት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቀላል እና እናታዊ ዓይኖች ማሰላሰል እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያከናወናቸው ነገሮች ልብን ዘልቀው በመግባት ሕይወትን ይለውጣል” ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሕይወት ዕቅድ ትኩረት በመስጠት ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ብርሃን ግልጽ እና ትሑት የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ፥ በቃላቸው እና በድርጊታቸው ቅዱስ ባርቶሎ ያበራውን የፍቅር ነበልባል በስፋት እንዲያበሩ፣ በአገልግሎት፣ በውይይት እና በእምነት ሕይወት ለዚህ አስደናቂ ወጣት ትውልድ ተዓማኒ ሞዴሎች እና ጥበበኛ መሪዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል።
እምነትን በኢየሱስ ላይ ማድረግ
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ለሕፃናት፣ ለታዳጊዎች እና ለወጣቶች በሰጡት የማበረታቻ ቃላት፥ እድገታቸውን በፍቅር ለሚንከባከቡት ሰዎች እምነት እንዲኖራቸው፥ በሕይወት ዘመናቸው እምነታቸውን በተሰቀለው፣ ከሞት በተነሣው፣ በሚያድናቸው ነፃ በሚያወጣቸው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያደርጉ ተማጽነው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የማይተወን ወይም የማይጥለን ወዳጃችን፣ የሚረዳን እና ሁልጊዜም ከጎናችን የሚሆን ወንድማችን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ከእርሱ እና ከጸጋው ጋር መሆን
“በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል የሰውን ዘር ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንክብካቤ እንደምናቀርብ፥ ከእርሱ ጋር በመሆን በጸጋው ስንታገዝ መልካም ነገርን ከማድረግ ሊያግደን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እና የሰላም ተስፋ እዚህም ሆነ በየትኛውም ቦታ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን” ሲሉ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ የበጎ አድራጎት ሠራተኞን በጸሎታቸው በማስታወስ ቡራኬያቸውን እንደሚሰጧቸው በማረጋገጥ፥ “የፖምፔይ ቅዱስ መቁጠሪያ ንግሥት እና ቅዱስ ባርቶሎ ሆይ! ስለ እኛ ጸልዩልን! በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።
