ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ድሆችን መንከባከብ ከባድ ቢሆንም የክርስትናችን ዋና አካል ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰኞ ሚያዝያ 26/2018 ዓ. ም. የቤተ ክርስቲያኗ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ” አካል ከሆነው የአሜሪካ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።
ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ ድሆችን እና እጅግ የተቸገሩትን በመንከባከብ ወንጌልን ለማወጅ ለሚፈልጉ ሰዎች የግል እና ተቋማዊ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው ተገንዝበዋል።
ከችግሮቹ መካከል በቂ የዕርዳታ አቅም አለማግኘት፥ ይህ ዓይነቱ አገልግሎት እውነተኛ የክርስትና ሕይወት ዋና አካል መሆኑን ለሌሎች ማሳየት እና በተለይም በምንፈልገው መንገድ ልንረዳቸው የማንችላቸውን ሰዎች ስናገኝ ተስፋ መቁረጥን እንደሚያካትት አስረድተዋል።
የአሜሪካ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ከእነዚህ ተግዳሮቶች በምንም መልኩ ነፃ እንዳልሆኑ ተናግረው፥ “ሆኖም፣ እንደዚህ ዓይነት እንቅፋቶች ሲያጋጥሙን ‘ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ!’ የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ድምፅ እንደገና መስማት መማር አለብን” ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የአሜሪካ መንግሥት በማያሚ ሊቀ ጳጳስ ለሚተዳደረው የዕርዳታ ፕሮግራም የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ መቀነሱ ሲታወስ፥ የዕርዳታ ፕሮግራሙ ለአሥርተ ዓመታት ብቻቸውን ለቀሩት ታዳጊ ሕጻናት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ እንደ ነበር ታውቋል።
ኦፕሬሽን “ፔድሮ ፓን” የተሰኘ የስደተኞች ማቋቋሚያ ጽ/ቤት፥ ልጆችን በማደጎ ውስጥ በመንከባከብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1960 ዓ. ም. ጀምሮ ከቤተሰብ አባላት ጋር እንዲገናኙ ሲረዳቸው ቆይቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የአሜሪካ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተገቢ ጥረት በማድረግ የእግዚአብሔርን የአገልግሎት ጥሪ በተለይም ለተቸገሩት እና ለተናቁት የሚሰጠውን የርህራሄ አገልግሎት እንዲቀጥል አበረታተዋል።
ይህን ሲያደርጉ ኢ-ሰብዓዊ ለሆኑ ሁኔታዎች መፍትሄ ለማግኘት፣ የግለሰቦችን እና የቤተሰብን ስቃይ ለማቃለል፣ ችግር እና ግጭት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መከራን ለማቃለል እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ “በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በዕለት ተዕለት ሥራችሁ የሚያስገድዳችሁ የክርስቶስ ቸርነት መሆን አለበት” ብለዋል።
የአሜሪካ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከ170 በላይ የሀገረ ስብከት ኤጀንሲዎችን ያካተተ ሲሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የማኅበራዊ አገልግሎት ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለጎረቤት ያለው ፍቅር ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ያለውን እውነተኛ ፍቅር የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ መሆኑን አስታውሰዋል።
ቅዱስነታቸው እንዳሉት፥ የካቶሊክ የበጎ አድራጎት ሠራተኞች በኢየሱስ ልብ ፍቅር ለሌሎች ቁሳዊ ዕርዳታ የማቅረብ ፍላጎት ስላላቸው እውነተኛ ዕረፍት በማግኘት ሰብዓዊ ክብራቸውም ይከበራል” ብለዋል።
“የካቶሊክ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተጨባጭ ዕርዳታ አማካኝነት ዕድለ ቢስ የሆኑትን ሲረዱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ጋር ይገናኛሉ” ብለው፥ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የክርስቶስ ትንሣኤ ሁሉንም ነገር አዲስ እንደሚያደርግ እና የድርጅቱን ሥራ በብርሃነ ትንሳኤው ተስፋ እንዲመራ የዳይሬክተሮች ቦርድን አበረታተዋል።
በመጨረሻም፥ “ለተከበረ ተልዕኮአችሁ መልካም ምኞትን አቀርባለሁ፤ እናንተን እና ባልደረቦቻችሁን በሙሉ በጸሎቴ እንደማስታውሳችሁ አረጋግጣለሁ” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
