ፈልግ

ርሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ ርሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ልግስና የእግዚአብሔርን ቸርነት እንደሚያሳይ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ከተውጣጡ ልዑካን ቡድን ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ንግግር አድርገውላቸውል። ቅዱስነታቸው ለል ዑካን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ብዙዎችን ለመርዳት ያደረጉት የበጎ አድራጎት ሥራ እንቅስቃሴን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ወደ ሮም ንግደት ያደረጉ በአሜሪካ የሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት አስተባባሪ አባላት ጋር ቅዳሜ ሚያዝያ 24/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ በፔሩ ለሚገኘው የቀድሞው የቺክላዮ ሀገረ ስብከታቸው ፋውንዴሽኑ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፥ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪ ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አገልግሎት ለመርዳት ላደረጉት ተልዕኮ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፋውንዴሽኑ ውስጥ የአባላት ቁጥር በየዓመቱ እጨመረ መምጣቱን እና የሚሰጠውን ድጋፍ ለማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ የአገልግሎት መንገዶችን ለማመቻቸት ፍላጎት እንዳለው በማወቃቸው የተሰማቸውን ደስታ ለአባላቱ ገልጸዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን እና ተተኪዎቻቸውን እንዲሁም ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ያዘዘ ቢሆንም እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ምዕመን ቅዱስ ወንጌልን በቃል እና በበጎ አድራጎት የማወጅ ተልዕኮ ተሰጥቶታል” ብለዋል።

ቅዱስ ያዕቆብ ለጥንት የክርስቲያን ማኅበረሰብ የጻፈውን በማስታወስ፥ “እምነት ያለ ሥራ የሞተ እና የማዳን ኃይልም የለውም” ሲሉ ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ድሃ እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ፍላጎቶችን እንዲያረኩ መጠየቁን ወንጌላት ያስተምሩናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በዓለም ዙሪያ በቤተ ክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ ለሚሳተፉ ሰዎች ዕርዳታን እንደሚያደርግ እና ነጻ የትምህርት ዕድል እንደሚሰጥ አስታውቀው፥ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወደፊት መሪዎች ለመሆን የላቀ ትምህርት ማግኘት የሚችሉ ካህናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን እንደሚያካትት ታውቋል።

“ልግስናችሁ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ደግነት በተጨባጭ መንገድ እንዲለማመዱ አስችሏቸዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ከደግነታቸው ተጠቃሚ ለሆኑት ሁሉ ላሳዩት ልግስና የፋውንዴሽኑን አባላት አመስግነዋል።

ከለጋሽ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት መሆኑን በማስታወስ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰላምታ በመጠቆም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰላም መሣሪያዎች እንዲሆኑ ያቀረበላቸውን ግብዣ ደግመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፥ “ልማት አዲሱ የሰላም ስም ነው” ማለታቸውን በማስታወስ፥ ይህን ሲሉ እውነተኛ ስምምነት የግጭት አለመኖር ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የሰው ልጅ ልማትን በንቃት ከማበረታታት የመጣ ነው” ማለታቸውን አክለው ገልጸዋል።

“ፋውንዴሽኑ የሚያደርጋቸው ዓይነት ተጨባጭ ተነሳሽነቶች እውነተኛ ዕድገትን በማሳደግ በማኅበረሰቦች እና በግለሰቦች መካከል ስምምነትን ለማበረታታት ትክክለኛ መንገዶች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ወደ ሮም ላደረጉት መንፈሳዊ ጉዞ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን እና የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ሥራን በመደገፋቸው የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላትን በድጋሚ አመስግነዋል።

“የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደመሆኔ መጠን ለሐዋርያዊ አገልግሎቴ እና ለቤተ ክርስቲያኗ ፍላጎቶች የምታቀርቡትን ጸሎት በዘላቂነት እንድትቀጥሉ እጠይቃለሁ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

02 May 2026, 15:44