ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት   (@Vatican Media)

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል። ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ይፋ በሆነው መርሃ ግብር መሠረት ቅዱስነታቸው ማድሪድን፣ ባርሴሎናን እና የካናሪ ደሴቶችን እንደሚጎበኙ እና በዓለም ረጅሙ የተባለለትን “የሳግራዳ ፋሚሊያ” የቅድስት ቤተሰብ ባዚሊካን እንደሚባርኩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ረቡዕ ሚያዝያ 28/2018 ዓ. ም. የቅዱስነታቸውን የስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር አረጋግጦ፥ በጉብኝታቸው ወቅትም አሥራ ሁለት ንግግሮችን እንደሚያደርጉ፣ አራት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን እንደሚመሩ እና ከፖለቲካ፣ ከቤተ ክርስቲያን እና ከሲቪክ መሪዎች ጋር፥ በጠቅላላው አሥር ስብሰባዎችን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ስፔን መዲና ማድሪድ የሚደርሱት ግንቦት 29/2018 ዓ. ም. እንደሚሆን ያስታወቀው መግለጫው፥ ወደ ማድሪድ ሲደርሱ ንጉሥ ፌሊፔ 6ኛ በንጉሣዊ ቤተ መንግሥት አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው እና ከዚያም ቅዱስነታቸው ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲ አባላት ጋር ከተገናኙ በኋላ በዚያው ምሽት በማዕከላዊ ማድሪድ በሚገኘው ፕላዛ ዴ ሊማ ከወጣቶች ጋር ሆነው የጸሎት ሥነ-ሥርዓትን እንደሚመሩ መግለጫው አስታውቋል።

በማግሥቱም በቅዱስ ቁርባን “ኮርፐስ ክሪስቲ” ቡራኬ ላይ ከተገኙ በኋላ በታዋቂው ፕላዛ ደ ሲቤሌስ የሚዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ይመራሉ። ከቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባላት ጋር በግል ከተገናኙ በኋላ በማድሪድ ሞቪስታር አሬና በሚቀርበው ዝግጅት ከባህል፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከንግድ እና ከስፖርት ተወካዮች ጋር የሚደረገውን ስብሰባ ይካፈላሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሰኔ 1/2018 ዓ. ም. ጠዋት ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። ከዚያም በተወካዮች ኮንግረስ ላይ ለፓርላማ አባላት ንግግር እንደሚያደርጉ፣ በስፔን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር እንደሚገናኙ እና ምሽት ላይ በበርናቤው ስታዲየም ከሀገረ ስብከቱ ምዕመናን ጋር እንደሚገናኙ መርሃ ግብሩ አመልክቷል።

የሳግራዳ ቤተሰብ ባዚሊካ ምረቃ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኔ 2/2018 ዓ. ም. በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማዕከላዊ ሥፍራ በሚሰጠው የባርሴሎና ጉብኝታቸው የቅዱስ ቤተሰብ “ሳግራዳ ፋሚሊያ” ባዚሊካ አካል በሆነው ረጅሙ ሰገነት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው እንደሚባርኩት ይጠበቃል።

ይህ ረጅሙ የባዚሊካው ሰገነት ሥራ ከ16 ዓመታት በፊት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ተባርኮ የተጀመረ ታሪካዊ እና የባዚሊካው ዋና ምልክት እንደሆነ ታውቋል። ብዙውን ጊዜ “በድንጋይ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ” እየተባለ የሚጠራው ባዚሊካ ቅርጽ የተነደፈባው በታዋቂው የካታላን አርክቴክት አንቶኒ ጋውዲ ሲሆን፥ ሕይወቱ ያለፈበት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ዘንድሮ እየተከበረ እንደሚገኝ ታውቋል።

ስደት እና የካናሪ ደሴቶች

ቅዱስነታቸው ከሚሳተፉባቸው አምልኮአዊ በዓላት እና ይፋዊ ዝግጅቶች ጎን ለጎን በማኅበረሱ ለተገለሉት ሰዎች ያላቸውን አሳቢነት በድጋሚ እንደሚገልጹ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በማድሪድ ቤት የሌላቸው ሰዎች መጠለያን እና በባርሴሎና የሚገኘውን የማረሚያ ቤት ተቋም እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መጨረሻ ላይ “ስደት” የሚለው ርዕሥ ማዕከላዊ ሥፍራን እንደሚይዝ ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰኔ 4/2018 ወደ ካናሪ ደሴቶች፥ በሰሜን ምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ወደሚገኙ የእሳተ ገሞራ ደሴቶች እንደሚጓዙ መርሃ ግብሩ አመልክቷል። ደሴቶቹ ወደ አውሮፓ ለሚጓዙ ስደተኞች ዋና የባሕር በር ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በሁለቱ ደሴቶች፥ በላስ ፓልማስ ደ ግራን ካናሪያ እና በሳንታ ክሩዝ ደ ቴነሪፍ ደሴቶች መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ በስደተኞች መቀበያ እና ዕርዳታ መስጫ ማዕከላት የሚሰሩትን እንደሚያበረታቷቸው ታውቋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ወደ ሥፍራው ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ የስፔን ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን በጉጉት እንደሚጠብቃቸው ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታወጅ፥ የስፔን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊስ አርጉኤሎ የጳጳሳቱን ደስታ በቪዲዮ መልዕክታቸው ገልጸው፥ ምእመናኑም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመቀበል ጆሮአቸውን እና ልባቸውን እንዲከፍቱ መጋበዛቸው ይታወሳል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችን እና እህቶችን ለማፅናት የታሰበ እንዲሁም በማኅበረሰቦቻችን ተጨባጭ ሕይወት ውስጥ ተስፋ እና ቸርነት የሚሆን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

07 May 2026, 12:02