ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በእናቶች ቀን እናቶችን በጸሎታቸው አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር ሁለተኛ እሑድ የሚከበር የእናቶች ቀን በዓለም ዙሪያ ከ40 በላይ አገራት የሚከበር ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ሁሉንም እናቶች በልዩ ትኩረት በማስታወስ መልካምን ተመኝተውላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ግንቦት 2/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ካደረሱ በኋላ ባሰሙት ንግግር፥“እያንዳንዷ እናት በተለይም እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ እናቶችን በፍቅር እና በምስጋና በማስታወስ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የእኛ እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንለምን” ብለዋል።
የኮፕቲ እና የካቶሊክ እምነቶች የወዳጅነት ቀን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በየዓመቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 10 የሚከበረውን የኮፕት እና ካቶሊክ እምነቶች የወዳጅነት ቀን ምክንያት በማድረግ በግብጽ ለኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ የወንድማማችነት ሰላምታ መለዕክት ልከዋል።
“ለብፁዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ወንድማዊ ሰላምታዬን ሳቀርብ፥ ይህ የወዳጅነት ጉዞአችን ‘ወዳጆች’ ብሎ በጠራን በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ፍጹም አንድነት እንደሚመራን ተስፋ በማድረግ፥ መላዋን የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት እንደማስታውሳት አረጋግጣለሁ” ሲሉ አክለዋል።
ለካናሪ ደሴቶች ነዋሪዎች ቀረበ ምስጋና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የካናሪ ደሴቶች ሕዝብ የሚገልጸውን የመልካም አቀባበል መንፈስን በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
የካናሪ ደሴቶች የተላላፊ ቫይረስ ታማሚዎችን የያዘ የሆንዲየስ መርከብ ወደ ክልሉ እንዲገቡ መፍቀዳቸውን በመጥቀስ፥ በሚቀጥለው ወር በደሴቶቹ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ስለሚያገኟቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 5/2018 ዓ. ም. ድረስ በስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ሲታወቅ፥ በጉብኝታቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በቴኔሪፍ እና የካናሪያ ደሴቶች በኩል በማለፍ ከስደተኞች እና ስደተኞችን በመርዳት ላይ ከሚገኙ የተወሰኑ ድርጅቶች አባላት ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።
