ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክን በመንበራቸው ተቀበሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ጠዋት የፖላንድ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ዶናልድ ተስክን በቫቲካን ተቀብለው ተነጋግረዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ሚያዝያ 29/2018 ዓ. ም. ረፋድ ላይ ከፖላንድ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ተስክ በመቀጠልም ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እና በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጋርም ተገናኝተዋል።
እንደ ቅድስት መንበር መግለጫ መሠረት፥ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የተደረጉት ውይይቶች ገንቢ እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያረጋግጡ እንደ ነበር ታውቋል።
መግለጫው አክሎም፥ “ውይይቶቹ በፖላንድ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሁም በፖላንድ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ባለው ግንኙነት፥ በተለይም በትምህርት መስክ እና በሥነ-ምግባር ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሰጡ ነበር” ብሏል።
መግለጫው በመጨረሻም፥ በአሁኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ላይ የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን ገልጾ በተለይም በዩክሬን ስላለው ግጭት፣ እንዲሁም ፖላንድ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ባላት ሚና ላይ ውይይት የተደረገበት እንደ ነበር አስታውቋል።
07 May 2026, 14:00
