ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ አዲስ የሾሟቸው የሮም ጳጳሳት የሰላምና የአንድነት ምሳሌዎች እንዲሆኑ አሳሰቡ

የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቅዳሜ ሚያዝያ 24/2018 ዓ. ም. አራት የሮም ሀገረ ስብከት ካኅናትን ረዳት ጳጳሳት አድርገው ሾመዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ጳጳሳቱ ከሁሉም ጋር ለማግኘት ዝግጁዎች እንዲሆኑ፥ የእግዚአብሔርን ቅርብነት እንዲያውጁ እና ተስፋን እንደገና እንዲያነቃቁ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይህ የሕዝበ እግዚአብሔር በዓል ነው” በማለት ቅዳሜ ሚያዝያ 24/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት መጀመሪያ ላይ አስታውቀዋል።

ቅዱስነታቸው በዕለቱ አራት የሮም ሀገረ ስብከት ካኅናትን ረዳት ጳጳሳት አድርገው የሾሟቸው ሲሆን፥ እነሱም እስቴፋኖ ስፓራፓኒ፣ አሌሳንድሮ ዜኖቢ፣ አንድሪያ ካርሌቫሌ እና ማርኮ ቫሌንቲ ሲሆኑ ከሳቢና ካንታሉፖ ከመጡት ማርኮ ቫሌንቲ በስተቀር ሁሉም በሮም የተወለዱ መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቃለ-ምዕዳናቸው፥ አዲሶቹን ረዳት ጳጳሳት “ውድ ወንድሞቼ” ብለው ጠርተው፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ረዳት ካርዲናል ጋር በመሆን የሮም ጳጳስ ለሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናን የመልካም እረኛ ምስል እንዲሆኑ እና በመላው ዓለም ተስፋፍቶ የሚገኘውን የእግዚአብሔር ሕዝብ ቸርነት ለመጠበቅ እንደሚረዱት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አዲሶቹ ጳጳሳት አገልግሎታቸውን እንዴት ማከናወን እንደሚገባ ሲያስረዱ፥ “የሰላም እና የአንድነት ሰዎች እንዲሆኑ፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ያለውን ሰፊ ሕዝብ በጸጋና በምሕረት የሚሰበስቡ፣ ልዩነቶችን የሚያስተሳስሩ፣ የሚቀበሉ፣ የሚያዳምጡ፣ ይቅር የሚሉ እና በአገልግሎታችሁ ውስጥ ነቢያት የሚሆኑ” በማለት ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ አዲስ የሾሟቸው የሮም ጳጳሳት የሰላምና የአንድነት ምሳሌዎች እንዲሆኑ አሳሰቡ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ አዲስ የሾሟቸው የሮም ጳጳሳት የሰላምና የአንድነት ምሳሌዎች እንዲሆኑ አሳሰቡ   (@Vatican Media)

ለሁሉም ሰው ተስፋን የሚያውጁ እና የሚያመጡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 8/2025 ዓ. ም. ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፥ “መሣሪያን ያልታጠቀ እና ትጥቅን የሚያስፈታ ሰላም” ያሉትን በመድገም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች መካከል መሣሪያን ያልታጠቀ እና ትጥቅን የሚያስፈታ ነቢይ ሆኖ መኖሩን አስታውሰዋል።

ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን ቃል በማስታወስ፥ ከኢኮኖሚያዊ ድህነት ባሻገር ጥልቅ መለያየት፣ መከራ፣ ብቸኝነት ወይም ትርጉም ማጣት ያጋጠማቸውን ሰዎች በልባችን ውስጥ በመያዝ፥ በቤተ ክርስቲያን እና በሰው ልጆች መካከል ባለው ወንድማማችነት ውስጥ ማንም ሰው ንቁ አካል ከመሆን ያልተገለለ መሆኑን ማወጅ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሀገረ ስብከታቸው አዳዲስ ረዳት ጳጳሳት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ይህንን ጥሪ እንደ ካህናት ተቀብላችሁ ከቁምስና ማኅበረሰቦች ጋር አብራችሁ የተጓዛችሁ፥ አሁን በመጣላችሁ አዲስ ተጨማሪ እና ተመሳሳይ ጥሪ መሠረት፥ ማንም ራሱን በእግዚአብሔር እንደተጣለ አድርጎ መቁጠር የለበትም በሚለው በቅዱስ ወንጌል እምብርት የሆነው የምሥራች ቃል ሰባኪዎች ትሆናላችሁ” ብለዋል።

ከሁሉም ጋር መቀራረብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጳጳሳቱ ለሁሉም ሰው ማለትም ለምዕመናን፣ ለገዳማውያን ወይም ለቀሳውስት ቅርብ የመሆን አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተው፥ ሰዎች እናንተን ከመፈልግ ይልቅ እናንተ ወደ ሰዎች ቅርብ መሆን ይገባችኋል” ሲሉ አሳስበዋል።

“ካኅናት፣ ዲያቆናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም በሐዋርያዊ ሥራ ላይ የተሰማሩ ምዕመናን ብቸኝነት የማይሰማቸው መሆኑ አረጋግጡ” ሲሉ አሳስበው፥ “በተለያዩ አገልግሎቶቻቸው ተስፋን እንደገና እንዲያቀጣጥሉ እና የአንድ እና ተመሳሳይ ተልዕኮ አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው እርዷቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

“በሮም ውስጥ የሚኖሩ ድሆች፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ከዓለም ዙሪያ ወደ ሮም የሚመጡ ጎብኚዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ በተቋሞች እና በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኗ እውነተኛ ገጽታ የሆነውን እናታዊ እንክብካቤ እንዳይለያቸው በማሳሰብ፥ የእኛ ታማኝ እና የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁልጊዜ በመንገዳችን ትመራን እና ትጠብቀን” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

አራት የሮም ሀገረ ስብከት ካኅናትን ረዳት ጳጳሳት ሆነው የተሾሙበት ሥነ-ሥርዓት
04 May 2026, 17:02