ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የኢየሱስ ፍቅር በውስጣችን ፍቅር እንዲወለድ ያደርጋል” ሲሉ ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸውን አንዳንድ ቃላትን እንሰማለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እንጀራውን እና ወይኑን ወደ ሕያው የፍቅሩ መገለጫነት ሲለውጠው እንዲህ አለ፥ ‘የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ’ (ዮሐ. 14፡15)። ይህ አባባል ‘እግዚአብሔር እኛን የሚወደን ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅ ነው’ ከሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ ነፃ ያደርገናል። ጽድቃችን ለእግዚአብሔር ፍቅር ቅድመ ሁኔታ ሊሆን አይችልም። በተቃራኒው የእግዚአብሔር ፍቅር የጽድቃችን መሠረት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለዓለም እንደገለጠው ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የእርሱን ትእዛዛት የምንጠብቀው እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ስንገነዘብ ነው። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት የማስፈራሪያ ቀነ ገደብ ሳይሆኑ፥ እኛ ወደ እርስ በርስ ግንኙነት እንድንገባ የቀረቡልን ግብዣዎች ናቸው።
እግዚአብሔር እኛን እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ የሚያዝዘን ለዚህ ነው (ዮሐ. 13፡34)። በውስጣችን ፍቅር እንዲወለድ የሚያደርግ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ታማኝ፣ ንፁህ እና ቅድመ ሁኔታን የማያስቀምጥ የእውነተኛ ፍቅር መለኪያ ነው። ‘ነገር ግን’ ወይም ‘ምናልባት’ የሚሉ ቃላትን የማያውቅ፣ ከእኛ ምንም የማይፈልግ፣ በምላሹ ምንም የማይጠብቅ፣ ሕይወትንም ጭምር አሳልፎ የሚሰጥ ፍቅር ያለው ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደወደደን ሁሉ እኛም ሌሎችን ልንወድ እንችላለን። እግዚአብሔርን በእውነት ስንወድ እርስ በርሳችን በእውነት እንዋደዳለን። ልክ እንደ ሕይወት ነው፥ ሕይወትን የተቀበሉት ብቻ በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ ሁሉ፥ ሊወዱ የሚችሉት የተወደዱት ብቻ ናቸው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ትእዛዛት ከሐሰተኛ ፍቅር የሚፈውሱን የሕይወት መንገዶች ናቸው። ወደ ድነት የሚያደርሱን የመንፈሳዊ አኗኗር ዘይቤዎች ናቸው።
በሕይወት ፈተናዎች ውስጥ ብቻችንን የማይተወን እግዚአብሔር ስለሆነ ነው። ‘ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚሆን አጽናኝ የእውነት መንፈስ እሰጣችኋለ’ ብሎ ቃል ገብቶልናል (ዮሐ. 14:17)። ይህ ስጦታ በክፉ መንገድ መጓዝ፣ ድሆችን መጨቆን፣ አቅመ ደካሞችን ማግለል እና ንጹሐንን መግደል እስከቀጠለ ድረስ ዓለም ሊቀበለው አይችልም። በሌላ በኩል ኢየሱስ ሁሉንም ማፍቀሩን የሚቀበሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ፈጽሞ የማይወድቅ አጋርነትን ያገኛሉ። ‘እርሱ በእናንተ ዘንድ ስለሚኖር፤ በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላችሁ’ (ዮሐ. 14:17)። ስለዚህ ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እና በሁሉ ሥፍራ መመስከር እንችላለን። ፍቅር የሰው ልጅ የአእምሮ ሃሳብ ሳይሆን ሁሉም ነገር ከምንም የተፈጠረበት እና ከሞት የተዋጀበት የመለኮታዊ ሕይወት እውነታ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ እና ዘላለማዊ ፍቅሩን ለእኛ በመስጠት የተወደደ የአብ ልጅ ማንነቱን ከእኛ ጋር ይካፈላል። “እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ” (ዮሐ. 14:20)። ይህ ሁሉን የሚያቅፍ የሕይወት አንድነት ተከላካያችንን የሚቃወም የጠላት መንፈስ ይክዳል። እንደ እውነቱ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ የእውነት ኃይል ቢሆንም ከሳሹ መንፈስ ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ እና ሰዎችን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚጥር የሐሰት አባት ነው’ (ዮሐ. 8:44)። በተቃራኒው ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከክፉ ነገር በማዳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች አንድ ያደርገናል።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ለዚህ ስጦታ በምስጋና በመሞላት፣ መለኮታዊ የፍቅር እናት ለሆነችው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እራሳችንን እናቅርብ።” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።
