ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚያጎሳቁሉ ነገሮችን የመቃወም ተልዕኮ አላት” ሲሉ ተናገሩ
ክቡራት እና ክቡራን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያደረጉት ንግግር ሙሉ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት ለዕለቱ የተመርጠው የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ፥ “የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከመከራውም ሁሉ አወጣው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው” (ሐዋ. ሥራ 7: 9-10) ይላል።
ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ለምዕመናኑ ያሰሙትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ወንድሞችና እህቶች ሆይ! ዛሬ ስለ ቤተ ክርስቲያን በሚናገረው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ምክር ቤት ደንብ ሰባተኛ ምዕራፍ ላይ እናተኩራለን። ይህ ደንብ ከሚገልጻቸው ባህሪያት መካከል አንዱ በሆነው እና በዘመን ፍጻሜ የሰው ልጅ፣ የዓለም እና የታሪክ ዕጣ ፈንታ ገጽታ ሥነ-መለኮታዊ ጥናት ላይ እናሰላስላለን። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድራዊ ታሪክ ውስጥ ዘወትር ወደ መጨረሻ መድረሻዋ ማለትም ወደ ሰማያዊው ቤቷ ትጓዛለች። ነገር ግን ይህ ብዙውን ጊዜ ችላ የምንለው ወይም አሳንሰን የምንመለከተ አስፈላጊ ገጽታ ነው። ምክንያቱም ወዲያውኑ በሚታየው ነገር እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ይበልጥ ስለምናተኩር ነው።
ቤተ ክርስቲያን ማለት የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን መንግሥት የእርምጃዎቿ ሁሉ ዓላማ አድርጋው የምትጓዝበት መንገድ ነው። ‘Lumen Gentium’ (የአሕዛብ ብርሃን ቁ.9)። በትክክል ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረታት ይህንን የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥት በማወጅ ነው (የአሕዛብ ብርሃን ቁ.5)። ስለዚህ እኛ በክርስቶስ አማካይነት ለድነት የተጠራውን ማኅበረሰብ እና ጠፈር እንድናጤን፣ ዓይኖቻችንን ወደዚህ የመጨረሻ ግብ እንድናዞር እና እንዲሁም ሁሉንም ነገር ከዚህ አንፃር እንድንመለከት እና እንድንገመግም ተጠርተናል።
ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ውስጥ የምትኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ዓለም መምጣት ለማወጅ ነው። ይህን የተስፋ ቃል ለሁሉም ሰው ዘወትር ታውጃለች። ይህን ቃል ኪዳን የምትቀበለው ቅዱሳት ምስጢራትን በተለይም የቅዱስ ቁርባን ምስጢር በምታከብርበት ወቅት ነው። የዚህን አመክንዮ ተግባራዊ በማድረግ በፍቅር እና በአገልግሎት ግንኙነቶች ውስጥ ትለማመደዋለች። ከዚህም በላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በቅርበት አንድነት የሚከናወንበት ቦታ እና መንገድ እርሷ መሆኗን ታውቃለች (የአሕዛብ ብርሃን ቁ.48)። እንደዚሁም መዳን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኩል ሊሰጥ እንደሚችል ትገነዘባለች።
ይህን በተመለከተ ‘የአሕዛብ ብርሃን’ (Lumen gentium) የሚለው ሐዋርያዊ ደንብ አንድ አስፈላጊ መግለጫን ይሰጣል። ‘ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የመዳን ምስጢር ናት’ (የአሕዛብ ብርሃን 48) ይላል። ማለትም በእግዚአብሔር የተደገፈው የሕይወት እና የሰላም ሙላት ምልክት እና መሣሪያ መሆኗን ይገልጻል። ይህ ማለት ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር ፍጹም በሆነ መልኩ ትታወቃለች ማለት ሳይሆን ነገር ግን ፍሬው እና ጅማሬው በመሆን፥ ፍፃሜውም ለሰው ልጅ እና ለጠፈር የሚሰጠው በመጨረሻው ጊዜ ብቻ ነው። ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በዚህ ምድራዊ ታሪክ ውስጥ ያልፋሉ። በመልካም ብስለት ግን በፍትሕ መጓደል እና በመከራዎችም ጭምር ሳይታለሉ ወይም ተስፋ ሳይቆርጡ፥ ‘እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ’ (ራዕ. 21:5) ከሚለው አምላክ በተቀበሉት ተስፋ እየተመሩ ይኖራሉ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ ቀድሞውኑ በኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠው የእግዚአብሔር መንግሥት መጀመሪያ እና ገና ባልተገለጠው መካከል ያለ መሆኑን ትገነዘባለች። ለመንገዷ ብርሃን የሚሆናት ተስፋ ጠባቂ እንደመሆኗ መጠን ሕይወትን የሚያበላሹ እና ዕድገቱን የሚከለክሉ ነገሮችን ሁሉ ውድቅ የማድረግ፥ ድሆችን፣ የተበደሉትን፣ የዓመፅ እና የጦርነት ሰለባዎችን እና በአካልም ሆነ በመንፈስ ለሚሰቃዩ ሁሉ አቋም ይዛ በግልጽ የመናገር ተልዕኮ አላት። (የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ማጠቃለያ ቁ. 159)።
ቤተ ክርስቲያን እንደ መንግሥተ ሰማይ ምልክት እና ቅዱስ ምስጢር፥ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ነጋዲያን ሕዝብ ስትሆን፥ በመጨረሻው የተስፋ ቃል በመነሳሳት፣ የታሪክን ተለዋዋጭነት በቅዱስ ወንጌል በኩል የምታነብ እና የምትተረጉም፣ ክፋትን በሁሉም መልኩ የምታወግዝ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የፍትህ፣ የፍቅር እና የሰላም መንግሥት ሊያመጣ የሚፈልገውን መዳን በቃልም ሆነ በተግባር የምታውጅ ናት። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እራሷን ለሌልች የምታውጅ ሳትሆን በውስጧ የሚገኝ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚድን ልታመለክት ይገባል።
ከዚህ አንፃር ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር መንግሥት አገልግሎት ውስጥ ብትገኝም የዚህን ዓለም ጊዜያዊ ምስል የያዙ የራሷን ተቋማት፣ የሰው ልጅ ድክመት እና ጊዜያዊነት በትህትና እንድትገነዘብ ተጠርታለች (የአሕዛብ ብርሃን ቁ.48)። ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ተቋም ፍጹም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። በእርግጥም፣ በታሪክና በጊዜ ውስጥ ስለሚኖሩ፣ ተልዕኮአቸውን በትክክል እንዲፈጽሙ ቀጣይነት ያለውን ለውጥ እንዲያደርጉ፣ ቅርጾቻቸውን ለማደስ፣ መዋቅሮቻቸውን ለማሻሻል እና ግንኙነቶችን በማደስ ቀጣይነት ላለው ለዳግም መወለድ ተጠርተዋል።
በእግዚአብሔር መንግሥት አድማስ ውስጥ ዛሬ ተልዕኳቸውን እያከናወኑ ባሉት ክርስቲያኖች እና ምድራዊ ሕይወታቸውን ጨርሰው በመንጻት ወይም በብፁዕና ውስጥ ባሉ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ግንኙነት መረዳት አለብን። “የአሕዛብ ብርሃን” የሚለው ሐዋርያዊ ደንብ እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ሁሉም ክርስቲያኖች አንድ ቤተ ክርስቲያን እንደሚመሠርቱ ያረጋግጣል። ሁሉም ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባላቸው አንድነት ላይ የተመሠረተ የመንፈሳዊ ሃብት ኅብረት እና መጋራት እንዳለ፣ በምድራዊት ቤተ ክርስቲያን እና በሰማያዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ወንድማማችነት በተለይም በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ የሚለማመዱት የቅዱሳን ኅብረት መኖሩን ያረጋግጣል (የአሕዛብ ብርሃን ቁ. 49-51)። ለሞቱት በመጸለይ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው የኖሩትን ሰዎች ፈለግ በመከተል እኛም በጉዞአችን ላይ እንጸናለን፤ ለእግዚአብሔር ያለንን አምልኮ እናጠናክራለን። በአንድ መንፈስ ቅዱስ ምልክት የተደረገበት እና በአንድ ሥርዓተ አምልኮ አንድ ሆነን፣ ከእኛ በፊት ከነበሩት ጋር ሆነን ቅድስት ሥላሴን እናመሰግናለን፤ ክብርንም እንሰጣለን።
ይህን እጅግ አስፈላጊ እና ውብ የሆነውን የክርስቲያንነት ገጽታ ያስታወሱንን የጉባኤው አባቶች እናመሰግናለን፤ በሕይወታችን ውስጥም ለማዳበር እንጥራለን” ሲሉ አስተምህሮአቸውን ደምድመዋል።
