ፈልግ

2025.09.14 Commemorazione dei martiri e testimoni della fede del XXI secolo 2025.09.14 Commemorazione dei martiri e testimoni della fede del XXI secolo  (@Vatican Media)

እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር በእውነተኛው ዓለም ውስጥ በተጨባጭ መገለጽ እንዳለባቸው ተነገረ

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ ዓርብ መጋቢት 25/2018 ዓ. ም. የሚቀርብ የስቅለተ ዓርብ ጸሎት አስተንትኖን ይፋ አድርጓል። በሮም ኮሎሲየም በተባለ ሥፍራ በሚቀርብ የመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ ያስተነተኑት አባ ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያኖች በእውነተኛው ዓለም ውስጥ የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅርን ሥነ-መለኮታዊ በጎነቶችን መገለጽ የሚችሉበትን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ምሳሌ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሮም ውስጥ ኮሎሲየም በተባለ ሥፍራ ለተሰበሰቡት እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ዓርብ መጋቢት 25/2018 ዓ. ም. ምሽት የመሩት የመስቀል መንገድ ጸሎት የቀድሞው የቅድስት ምድር ተንከባካቢ አባ ፍራንቸስኮስ ፓተን ባዘጋጁት አስተንትኖ ተፈጽሟል።

ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ፍራንችስኮስን ዕረፍት 800ኛ ዓመት እያከበረች ባለችበት ወቅት ፍራንችስኮስዊው ካኅን አባ ፍራንችስኮስ ፓተን፥ በአሥራ አራቱ የመስቀል መንገድ ማረፊያዎች ላይ የቀረቡት የቅዱስ ወንጌል ንባባት እና የቅዱስ ፍራንችስኮስ ጽሑፎች መሠረት በማድረግ የክርስትና ሕይወት ገጽታዎችን ዳስሰዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዓርብ ዕለት ይፋ ያደረገው የአባ ፓተን አስተንትኖ፥ በኢየሩሳሌም ጠባብ መንገዶች በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሰቀል እና ለመቀበር እስከ ጎልጎታ ድረስ ያደረገውን ጉዞ ያስታውሰናል።

አባ ፓተን በአስተንትኖአቸው መግቢያ፥ “ይህ መንገድ ጸጥ ያለ ቦታን ለጸሎት ለሚፈልጉ ምእመናን ብቻ የተወሰነ አይደለም” ብለው፥ “ይልቁን ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን በተዘበራረቀ፣ ትኩረትን በሚከፋፍል እና ጫጫታ ባለበት አካባቢ ለምንጓዝ እና በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት ለሚጋሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእርሱ ለሚያፌዙ ወይም ለሚሰድቡት ሰዎችም ጭምር እንደሆነ አስገንዝበው፥ “የዕለት ተዕለት ሕይወታችን እውነታ ይህ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“የመስቀሉ መንገድ ፍጹም ሃይማኖተኛ እና ረቂቅ የሆነ ሕይወት ለሚመሩ ሰዎች ብቻ የታሰበ አይደለም” ይላሉ አባ ፓተን፥ “ይልቁንም እምነት፣ ተስፋ እና በጎነት በእውነተኛው ዓለም ውስጥ መገለጥ እንዳለባቸው የሚያውቅ ሰው ልምምድ ነው” ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው የመስቀል መንገድ ማረፊያ ላይ ሞት ሲፈረድበት፥ ምንም እንኳን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ቢሆንም የሰው ልጅ ኃይልን እና ስልጣንን አላግባብ የመጠቀም ፈተና ውስጥ ሲወድቅ እንመለከታለን” ብለዋል።

“የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ‘ሥልጣን ላይ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ጦርነትን ሲጀምር ወይም ሲያቆም፣ በፍርድ ወንበር ላይ ሲቀመጥ፣ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፍ፣ የሰውን ክብር ሲያበረታታ ወይም ሲያጠፋ፣ ኃይሉን በሚጠቀምበት መንገድ ለእግዚአብሔር መልስ መስጠት አለበት’ ሲል የተናገረውን ያስታውሰናል” ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለተኛው ማረፊያ የሚሰቀልበትን መስቀል ሲቀበል፥ ከማንኛውም ዓይነት ህመም ወይም ውርደት ለመሸሽ የምንገፋፋበት እና የምንፈልግበት ስሜት ይሰማናል” ያሉት አባ ፓተን፥ “ኢየሱስ ሆይ ከመስቀል ፍርሃት ነፃ አውጣን፣ የተራመድክበትን መንገድ እንድንከተል እና ከመስቀልህ የሚገኘውን ክብርን እንድንፈልግ ጸጋ ስጠን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ማረፊያ ላይ ሲወድቅ፣ የእርሱ ሕይወት የማያቋርጥ ውርደት እና ትሕትና እንደ ነበረ እናስታውሳለን” ያሉት አባ ፓተን፥ ሰው ለመሆን የራሱን ክብር አሳልፎ መስጠቱን አስታውሰው፥

ይህ ውድቀት የበለጠ ጥልቅ እና ራሱን እጅግ ዝቅተኛ ያደረገበት ውድቀት መሆኑን አባ ፓተን አስታውሰው፥ “ወደ ሙታን መውረድ እና በሞት መሸነፍ በዚህ ምድራዊ ሕይወት መጨረሻ ላይ እያንዳንዳችንን የሚጠብቀን ውድቀት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአራተኛው ማረፊያ ከእናቱ ማርያም ጋር ሲገናኝ፥ በህመም፣ በአደጋ፣ በዓመፅ እና በተስፋ መቁረጥ ምክንያት የልጆቻቸውን ሞት የሚታገሱ እናቶችን እንደሚያስታውሰን እና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የማይታሰብ ሥቃይ እንደሚያጋጥመን ያሳየናል ብለው፥ “የሌሎችን ሥቃይ እንድንረዳ እና እንድንካፈል፣ በዚህም ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ በትክክል መማር እንድንችል የእናትነት ልብ ስጠን” ሲሉ አባ ፓተን ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአምስተኛው ማረፊያ ቀሬናዊው ስምዖን መስቀሉን በመሸከም እንደረዳው ያስታወሱት አባ ፓተን፥ “ስምዖን ኢየሱስን ለመርዳት ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ከእርሱ ጋር ያሉት እርምጃዎቹ ሕይወቱን ለዘላለም እንደለወጡት እና የራሱን ልጆች ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክሩ እንዲያስተምር ማድረጉን እንረዳለን” ብለዋል።

“ዛሬም ቢሆን በዓለም ዙሪያ ለሌሎች ሰዎች መልካም ለማድረግ የሚመርጡ ብዙ ሰዎች አሉ” ያሉት አባ ፓተን፥ “ብዙ ሰዎች በአንተ ባያምኑም ነገር ግን ሳያውቁ መስቀሉን እንድትሸከም ይረዱሃል” ብለዋል።

በስድስተኛው ማረፊያ ቬሮኒካ የኢየሱስን ፊት ስትጠርግ፥ ቀላል ቢሆንም ነገር ግን ጥልቅ የበጎ አድራጎት ተግባሯን እናያለን” ብለው፥ ለተቸገረ የምታዝን ሰው እንደመሆኗ መጠን የእሱን ምስል ጠብቃለች” ብለዋል።

“ዛሬ በደም የተበላሸ ፊትህን የምንጠርግበት ችሎታ ስጠን” በማለት ጸሎታቸውን ያቀረቡት አባ ፓተን፥ “አሁንም በአቧራ እና በደም የተሸፍነ እና የሰው ልጅ ክብር የሚረገጥበት ሁኔታ አለ” ብለዋል።

“ኢየሱስ በሰባተኛው ማረፊያ ለሁለተኛ ጊዜ ሲወድቅ ፍቅር ከሞት የበለጠ ጠንካራ መሆኑን እናያለን” ያሉት አባ ፓተን፥ ይህም ፍቅር ወደ እግዚአብሔር ሕይወት እንደሚስበን ያሳያል” ብለዋል።

“በምትወድቁበት ጊዜ በግፍ፣ በሐሰት፣ በተለያዩ ብዝበዛዎች እና ዓመፅ እንዲሁም ከጋራ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን የሚፈልግ ኢኮኖሚያዊ ስቃይ መሬት ላይ የወደቁትን ለማንሳት ይረዳል” ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በስምንተኛው ማረፊያ የኢየሩሳሌምን ሴቶች ሲያገኝ፥ መከራ ባለበት ቦታ ዘወትር ሴቶች መኖራቸውን እናስታውሳለን” ብለው፥ “እነዚህ ሴቶች ኢየሱስ ለዕርዳታ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብለዋል” ብለዋል።

“ህሊናችን ወደ ግድየለሽነት እንዳይለወጥ እና ሙሉ በሙሉ ሰው መሆን እንዳናቆም” እርዳን ሲሉ አባ ፓተን ጸልየዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዘጠነኛው ማረፊያ ለሦስተኛ ጊዜ ሲወድቅ፥ ስንቴ ብንወድቅም ምንም ለውጥ የማናመጣ መሆናችንን እንረዳለን” ያሉት አባ ፓተን፥ “በእርግጥ አስፈላጊው ነገር ኢየሱስ በምሕረቱ እንደገና ሊያነሳን መቻሉ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“አንተ ትፈልገናለህ” ይላሉ አባ ፓተን፣ “እያንዳንዳችን ከጎንህ ሆነን ወደ አብ እንድንደርስ እና ማንም እና ማንም ሊነጥቀን የማይችለውን እውነተኛ እና ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ ትፈልጋለህ” ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአሥረኛው ማረፊያ ልብሱን ሲገፈፍ፥ አምባገነን አገዛዞች፣ የሚዲያ ግድየለሽነት እና መጥፎን የማወቅ ጉጉታችን፥ እነዚያ ጥሰቶች ዛሬም መደገማቸውን እና የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር መጋፋታቸውን እናስታውሳለን” ብለዋል።

“ጌታ ሆይ፣ የሌሎችን ክብር ሳናውቅ በቀረን ቁጥር የራሳችን ክብር የሚቀንስ መሆኑን አስታውሰን” ሲሉ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአሥራ አንደኛው ማረፊያ በመስቀል ላይ ሲሰቀል፣ እውነተኛ ኃይል ጉልበት ወይም ዓመፅ እንዳልሆነ ነገር ግን የሰውን ልጅ ክፋት በይቅርታ ማሸነፍ የሚችል የፍቅር ኃይል ነው” ብለዋል።

“አንተ ከመስቀል ላይ ሆነህ የምትገዛ ንጉሥ ነህ” ያሉት አባ ፓተን፥ “የሠራዊትን ኃይል ሳትጠቀም ነገር ግን በመስቀል ለመቸንከር የሚፈቅድ ግልጽ የፍቅር ማጣትን ትጠቀማለህ” ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአሥራ ሁለተኛው ማረፊያ በመስቀል ላይ ሲሞት፣ ወደ አብ ሲመለስ እና ከራሱ ጋር ወደ አብ ሲያመጣን ተልዕኮው መጠናቀቁን እንመሰክራለን” ብለው፥ “የሥጋዌን ምስጢር ለማሳካት፣ የሕይወታችንን ጥልቅ ትርጉም ለማሳካት መንገድ እንዲከፍትልን፣ የእግዚአብሔር ልጆች እና የእርሱ ድንቅ ሥራ እንድንሆን በእርሱ ፊት ቆመናል” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአሥራ ሦስተኛው ማረፊያ ከመስቀል ሲወርድ፥ ሞቱ የመጀመሪያውን ፍሬ ማፍራት የጀመረው በአርማትያስ ዮሴፍ እና በኒቆዲሞስ ድፍረት ሲሆን፥ ጲላጦስን ለመቅረብ እና የኢየሱስን አስከሬን በክብር ለማሳረፍ በነበራቸው ድፍረት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“በሞተ ጊዜም ቢሆን የሰው አካል ክብሩን እንደሚጠብቅ የገለጹት አባ ፓተን፥ የሰው አካል ሊረክስ፣ ሊደበቅ፣ ሊጠፋ እና ተገቢው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሊከለከል እንደማይገባ አሳስበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአሥራ አራተኛው ማረፊያ ሲቀበር፥ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ቤታቸውን የመንከባከብ ስጦታ እና ኃላፊነት ወደ ተቀበሉበት ወደ ኤደን ገነት እንመለሳለን” ብለው፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ባለመታመናቸው ምክንያት ይህን ኃላፊነት አጥተዋል” ብለዋል።

አባ ፓተን በአስተንትኖአቸው መደምደሚያ፥ መግደላዊት ማርያም ሞት ድል እንደተደረገ የማወጅ ተልዕኮዋን እንደተቀበለች፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን፣ እርሱ ጌታ፣ ሕያው እና ከእንግዲህ የማይሞት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስቀል መንገድ ጸሎት መደምደሚያ ላይ፥ “ክርስቲያኖች በሕይወታቸው አብን፣ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን አንድ በሚያደርግ በጥልቅ የፍቅር አንድነት ውስጥ እንዲሳተፉ እና የቅዱስ ፍራንችስኮስን ግብዣ እንዲቀበሉ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

04 Apr 2026, 16:35