ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የዓለም መሪዎች ጦርነት የሚቆምበትን መፍትሄ እንዲያገኙ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ መጋቢት 22/2018 ዓ. ም. ማታ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ቅጥር ግቢ ለተገኙት ጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፥ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዓለም መሪዎች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
“ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቅርቡ ጦርነቱን ለማስቆም እንደሚፈልጉ ተነግሮኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ፕሬዝደንት ትራምፕ ዓመፅን እና ከባድ የጦር መሣሪያ ፍንዳታን ለመቀነስ እንደሚፈልጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች ቦታዎች በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ጥላቻ ለማስወገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይሆናል” ብለዋል።
የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ሊከበር ከተቃረበው የፋሲካ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በግጭት እና በዓመፅ በተጎዳ ዓለም ውስጥ ሰላም እንዲወርድ” በማለት ጥሪያቸውን አድሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መጋቢት 22/2018 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት በኩል ለሁሉም የዓለም መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ መሪዎቹ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ተመልሰው እንዲወያዩ፣ በተለይም በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት ሰላምን በልባችን ውስጥ ለማንገሥ ለችግሮች መፍትሄ እንዲገኝ እና ዓመፅን ለመቀነስ የሚያግዙ መንገዶችን መፈልግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የብርሃነ ትንሳኤው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት
የብርሃነ ትንሳኤ በዓል በዓመቱ ውስጥ እጅግ የተቀደሰ፣ የሰላም እና የአስተንትኖ ጊዜ ነው” ሲሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ሁላችንም እንደምናውቀው በዓለም ላይ በብዙ ቦታዎች ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ሞት እና ንጹሐን ሕጻናትም ጭምር የአደጋው ተጠቂዎች መሆናቸውን እያየን እንገኛለን” ብለዋል።
ለሰላም የማያቋርጥ ጸሎት ብናቀርብም ጥላቻን፣ ዓመፅን እና ጦርነትን ለማበረታታት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ” ብለው፥ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ተሰቅሎ እንደሚገኝ፣ በዓመፅ፣ በጥላቻ እና በጦርነት ምክንያት በሚሰቃዩ ንጹሐን ሰዎች በኩል እየተሰቃየ መሆኑን እያንዳንዱ ሰው በተለይም ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ ጠይቀዋል።
“የጦርነት ሰለባ ለሆኑት ስዎች እንጸልይላቸው፤ እውነተኛ ሰላም እንዲወርድ እንጸልይ” በማለት ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ከሰጡት ምላሽ ጋር በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የስቅለተ ዓርብ የመስቀል መንገድ
ሮም ውስጥ ኮሎሲየም በተባለ ሥፍራ በየዓመቱ በስቅለተ ዓርብ በሚደረገው የመስቀል መንገድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መስቀልን በግል ለመሸከም ያደረጉትን ውሳኔ በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ “በዛሬው ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ መሪ ሆኖ የሚያገለግል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም እየተሰቃየ መሆኑን መግለጽ አስፈላጊ ስለሆነ እኔም እነዚህን ሁሉ መከራዎች በጸሎቴ እሸከማቸዋለሁ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች እና ለምዕመናን በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኅብረት በመሆን ለእኛ ሲል ከተሰቃየው እና አዳኛችን ከሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመጓዝ የሰላም መሣሪያዎች እንድንሆን ጥሪ አቅርበዋል።
በስፔን የሚደረገው ሐዋርያዊ ጉብኝት
በሰኔ ወር በስፔን ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምን እንደሚጠብቁ የተጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ እምነትን፣ ብዙ ፍቅርን፣ እንግዳ ተቀባይነትን እና መልካም አቀባበልን እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ከ40 ዓመታት በላይ ስፔንን ሲጎበኟት እንደቆዩ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ዘወትር ታላቅ እምነት እና በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ማግኘታቸውን ገልጸው፥ አክለውም በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ይህንን ሁሉ ማክበር እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
