ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለጋራ ጥቅም የቆሙ መሪዎችን እንዲያዘጋጁ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካሜሩን ለማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ዩኒቨርሲቲው ለራሳቸው ማኅበረሰብ እና ለዓለም የጋራ ጥቅም ለመሥራት ኃላፊነት የሚወስዱ መሪዎችን እና ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ያለውን ሚና አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከማዕከላዊ አፍሪካ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ አባላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ፥ የአካዳሚው ባለስልጣናት ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል እና ለትምህርት አገልግሎት ላላቸው የማያቋረጥ ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1989 ዓ. ም. በማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (ACERAC) የተመሠረተው ተቋሙ፥ “ለቤተ ክርስቲያን እና ለአፍሪካ አኅጉር እውነትን በመፈለግ እንዲሁም ፍትህን እና አንድነትን በማስተዋወቅ ረገድ ብርሃን ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እውነተኛ የሕይወት እና የምርምር ማዕከል በመሆን ተማሪዎችን እና ፕሮፌሰሮችን በእውቀት ላይ ከተመሠረተ ወንድማማችነት ጋር ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው በዩኒቨርሲቲው ያደረጉት ጉብኝት መታሰቢያ
ቅዱስነታቸው በዩኒቨርሲቲው ያደረጉት ጉብኝት መታሰቢያ   (@Vatican Media)

“የወንጌል እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች ለዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ንቃተ ህሊና ዕድገት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ አዎንታዊ ኃይሎች ጋር በመተባበር የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን ለማበረታታት የታሰበ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እውነትን ቀዳሚ የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ማድረግ

ዩኒቨርሲቲዎች በዛሬው ዓለም ውስጥ ጠቃሚ እና ማዕከላዊ ሚና አላቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ብዙዎች መንፈሳዊ እና ሥነ-ምግባራዊ እሴቶቻቸውን እያጡ ባሉበት በዚህ ዘመን፥ እራሳቸውን በግለኝነት እና በግብዝነት መደዳ እያገኙ ባሉበት ሁኔታ ዩኒቨርሲቲዎች ልዩ የወዳጅነት፣ የትብብር እና የውስጥ አስተንትኖ ቦታዎች ሆነው ጎልተው ይታያሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ከገንዘብ ወይም ከተፈጠሮ ሃብት በላይ ነው

ቅዱስነታቸው፥ “አፍሪካ ተስፋ ለማድረግ የሚታገል የሰው ልጅ ከመጠን በላይ ጠባብ አድማስ ለማስፋት መሠረታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለች” ሲሉ አስረድተው፥ ከዚህም በላይ ዛሬ በዘመናዊ ባህላዊ አውዶች እና ፈተናዎች ውስጥ ስለ እምነት ማሰላሰል አስቸኳይ ፍላጎት መኖሩን፥ በዚህ መንገድ የእምነት ውበት እና ተዓማኒነት በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ፥ በተለይም በፍትሕ መጓደል፣ በእኩልነት ማጣት እና በዓመፅ በተጎዱ አውዶች ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው ከዩኒቨርሲቲው ቻንስሌር ጋር ሲገናኙ
ቅዱስነታቸው ከዩኒቨርሲቲው ቻንስሌር ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

“የአንድ አገር ሃብት በተፈጥሮ ሃብቶች ብዛት ወይም በቁሳዊ ሃብት ብቻ መመዘን የለበትም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በእውነት ውስጥ በተመሠረተ ቅን ሕሊና ላይ ካልሆነ በስተቀር የትኛውም ማህበረሰብ ሊያድግ እንደማይችል ገልጸው፥ በዚህ መንገድ “ለእውነት እና ለፍትህ አገልግሎት” የሚለው የመካከለኛው አፍሪካ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ጭብጥ፥ “የሰው ልጅ ሕሊና የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ፍትሃዊ እና የተረጋጋ መሠረት የሚጣልበት መሬት መሆኑን የሚያስታውስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

አዳዲስ ነገሮችን መፍራት አይገባም

በዓለማችን ዙሪያ በአንድ ወቅት የማኅበረሰብ ሕይወት መሪ የነበሩ የሞራል እሴቶች እየጠፉ መምጣታቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በዚህም ምክንያት ተቀባይነት የሌላቸው ተደርገው ይታዩ የነበሩ አንዳንድ ልምዶችን ማጽደቅ የተለመደ እየሆነ መጥቷል” ብለው፥ ለዚህ ለውጥ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እንዲሁም የፖለቲካ ኃይሎች አስተዋጽኦ አድርገዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በተለይም የአፍሪካ ካቶሊካዊ ወጣቶች ከፊታቸው የሚመጡ አዳዲስ ክስተቶችን መፍራት እንደሌለባቸው በማሳሰብ፥ ዩኒቨርሲቲው በዲጂታል አብዮት አውድ ውስጥ አዲስ ሰብዓዊነትን መፍጠር እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ብዙዎች የማያቋርጥ ፍለጋ በማድረግ የአፍሪካን ማራኪ የተፈጥሮ ሃብት ለማየት ፊታቸውን ወደ አህጉሪቱ በማዞር የሚያደርሱትን አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ውድመቶችን ግልጽ በማድረግ፥ ይህም ለእውነት እና ለመላው የሰው ልጅ አገልግሎት በመሆኑ የአኅጉሪቱ ነዋሪዎች የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ከቅርምት እንዲያተርፉ አሳስበው፥ “ይህ ጠንካራ ትምህርታዊ ጥረት ካለመኖር የተነሳ ልዩ ልዩ የብዝበዛ መንገዶችን መላመድ እንደ ብቃት ማነስ እና የዕድገት ነፃነት ማጣት ተደርጎ ይወሰዳል” ብለዋል።

በባዶነት ከመኖር መቆጠቡ

ይህ ማስጠንቀቂያ በዛሬው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ዓለም ውስጥ የበለጠ ተዛማጅነት ያለው ዕለታዊ የአእምሯዊ እና ማኅበራዊ ቦታዎቻች አካል ይሆናል” ብለው፥ ከቴክኒክ ብቃት በተጨማሪ በምጣኔ ሃብታዊ ጥናት ውስጥ በተካተቱ አድልዎች እና ስለ እውነታው ያለንን ግንዛቤ የሚቀርጹ የኃይል ዓይነቶች በስተጀርባ ያለውን አመክንዮ በግልጽ የሚያሳይ ሰብዓዊነት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ግንኙነቶችን ወደ ተግባራዊ መስተጋብሮች ሊለውጣቸው ይችላል” ብለው፥ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እውነተኛ ስብዕና ያለው መሆኑን በማስታወስ፥ “በልዩ ሰዎች መመራት ሲጀምሩ ባዶነት ይሰማል፤ ግጭት፣ ፍርሃት እና ዓመፅ የሚስፋፉበት መንገድም ይህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ
የማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ   (@Vatican Media)

“ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ሰዎች ለከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠሩበት፣ እውቀትን ከመስጠት በላይ ማስተዋል የሚችሉ፣ ለፍቅር እና ለአገልግሎት የተዘጋጁ የወደፊት መሪዎች እና ባለሙያዎች የሚወጡበት ቦታዎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከቤተ ክርስቲያን ልብ የተገኙ ናቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የዩኒቨርሲቲዎች ዓላማ በማብራራት ለካሜሩን ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ የስደት ዝንባሌን እንዲቋቋሙት አሳስበው፥ ይልቁንም ከአገራቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያገኙትን እውቀት ዜጎቻቸውን ለመርዳት እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “ከቤተ ክርስቲያን ልብ የተወለደ ነው” ማለታቸውን በመጥቀስ፥ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2017 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት “የእውነት ደስታ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነዳቸው፥ “ፕሮፌሰሮችም ሆኑ ተማሪዎችም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የክርስቶስን ወንጌል ለሁሉም የማወጅ ተልዕኮ ተሳታፊ ናቸው” ያሉትንም ጠቅሰዋል።

በዘመኑ ተግዳሮቶች አኳያ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ልዩ እና የማይተካ ቦታ እንዳለው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “የሰው ልጅ ጠቅላላ ዕድገት የዩኒቨርሲቲው ማዕከላዊ ሚና እንደሆነ እና ይህም መንፈሳዊ ምሥረታንም ያካትታል” ሲሉ አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የማዕከላዊ አፍሪካ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት

 

18 Apr 2026, 15:59