ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ መስቀል ተሸክመው የስቅለተ ዓርብ የመስቀል መንገድ ጸሎት መርተዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኮሎሲየም ዓርብ ማታ የቀረበውን የመስቀል መንገድ ጸሎት የመሩት መስቀል ተሸክመው ሲሆን ይህን በማድረግ ሁለተኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል።
በጥንት ዘመን በርካታ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት በተገደሉበት በኮሎሲየም የተዘጋጀውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመሩትን የመስቀል መንገድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ 30,000 በላይ ምዕመናን በሬዲዮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በቴሌቪዥን የተከታተሉት ሲሆን፥ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በተካሄደበት ቦታም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የሻማ ብርሃን ይዘው ተካፋይ ሆነዋል።
ግንባታው በንጉሠ ነገሥት ቬስፓሲያን ተጀምሮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ80 ዓ. ም. በንጉሠ ነገሥት ቲቶ የተጠናቀቀው ይህ ትልቁ እና ጥንታዊው ሥፍራ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራነት ተለውጧል።
በዚህ ሥፍራ በየዓመቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የሮም ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ ሞት እና በሚያስታውሱ በአሥራ አራት የመስቀል መንገድ ምዕራፎች ላይ ለማስተነተን በኮሎሲየም ይሰበሰባሉ።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ1980 ዓ. ም. እስከ 1994 ዓ. ም. ድረስ መስቀል በመሸከም ያቀረቡትን የመስቀል መንገድ ጸሎት ፈለግ በመከተል የዘንድሮውን የመስቀል መንገድ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መርተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መስቀል ተሸክመው ጸሎቱን ሲመሩ ከቅዱስ ወንጌል የተወሰዱ ምንባቦች እና በቅዱስ ፍራንችስኮስ የተጻፉ አጭር ጽሕፎች ጨምሮ የቀድሞው የቅድስት ምድር ተንከባካቢ በነበሩ ፍራንችስኮስዊ ካኅን በአባ ፍራንችስኮስ ፓተን የተዘጋጁ የአስተንትኖ ጽሕፎች ተነበዋል።
አባ ፓተን በአስተንትኖአቸው፥ ክርስቲያኖች የቅዱስ ፍራንችስኮስን ምሳሌ በመከተል በእውነተኛው ዓለም ውስጥ የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅር ሥነ-መለኮታዊ በጎነቶችን እንዴት ማሳየት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
አባ ፓተን በአስተንትኖአቸው አማካይነት “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ውስጥ በተጓዘባቸው ጠባብ መንገዶችች በኩል እስከ ጎልጎታ ድረስ ለመስቀል እና ለመቀበር ይወስደናል” ብለዋል።
“እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን ሁሉ በሁከት፣ ትኩረትን በሚከፋፍል እና ጫጫታ ባለበት አካባቢ፥ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት የምንጋራ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በእርሱ ላይ በሚያፌዙበት እና በሚሰድቡት ሰዎች ተከበን እንጓዛለን” ብለዋል።
“የመስቀሉ መንገድ ፍጹም ቀናተኛ ወይም ረቂቅ በሆነ መልኩ ሕይወትን ለሚመሩ ሰዎች የታሰበ አይደለም” ያሉት አባ ፓተን፥ “ይልቁንስ እምነት፣ ተስፋ እና ቸርነት በእውነተኛው ዓለም ውስጥ መካተት እንዳለባቸው የሚያውቅ ሰው ልምምድ ነው” ብለዋል።
አባ ፓተን በእያንዳንዱ የመስቀል መንገድ ምዕራፍ ላይ የሰው ልጅ ኃይልን ያለ አላግባብ የመጠቀም ፈተናን አውግዘው፥ “ትህትናን ከመፈለግ ይልቅ ክብርን በመፈለግ መስቀሉን የመናቅ ፍላጎታችንን እናያለን” ያሉት አባ ፓተን፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ጊዜ ሲወድቅ የፍቅር ኃይል የሌለን እኛን ወደ አብ እንዲያነሳን በእርሱ መታመን እንዳለብን ያሳስበናል” ብለዋል።
“አምባገነን አገዛዞች፣ ግድየለሽ ሚዲያዎች እና የራሳችን መጥፎን የማወቅ ጉጉታችን ሌሎችን እርቃናቸውን እንዴት እንደሚያሳዩ እና በዚህም የእኛን ሰብዓዊ ክብር እንደሚያዋርዱ ይጠቁማል” ብለዋል።
“እመቤታችን ማርያም የልጇን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በቅርብ ሆና ስትመለከት፥ ሴቶች ሁልጊዜ ከሚሰቃዩት ጋር እንደሚሆኑ ያስታውሰናል” ያሉት አባ ፓተን፥ የለቅሶ እንባችን ሰው ሆነን መኖርን እንደሚያስተምር እንማራለን” ብለዋል።
“ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አብ ዘንድ ተመልሶ ሲሄድ እኛንም ከራሱ ጋር እንደሚወደን እና ዘላለማዊ ሞትን የሚያስከትል ጥፋትን የመስበክ ተልዕኮውን በአደራ ሰጥቶናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስቀል መንገድ ጸሎት ማብቂያ ላይ፥ ክርስቲያኖች “የሕይወት ጉዞአችሁን ጥልቅ በሆነ የጋራ ፍቅር ላይ እንዲሳተፉ” በማለት ቅዱስ ፍራንችስኮስ ያቀረበልንን ግብዣ እንድንቀበል ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
