ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ሉዋንዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ሉዋንዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሦስተኛ አገር አንጎላ ደርሰዋል

ቅዱስነታቸው የአሥር ቀናት የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በመቀጥል ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ወደ አንጎላ መዲና ሉዋንዳ ደርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካሜሩን ካሳለፏቸው አራት ቀናት በኋላ ወደ አንጎላ የተጓዙት ቅዱስነታቸው፥ በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ለዘጠኝ ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች እንደቀሩ ወደ ሉዋንዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደርሰዋል።

ቀጣዮቹን ሦስት ቀናት በአንጎላ የሚቆዩ ሲሆን፥ ከዚያም የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አራተኛ እና የመጨረሻ መዳረሻቸው  ወደ ሆነች ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚጓዙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ሉዋንዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮአኦ ማኑዌል ጎንሳልቨስ ሎሬንሶ ለቅዱስነታቸው አበባን ካቀረቡላቸው ሁለት ሕጻናት ጋር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እሁድ ሚያዝያ 11/2018 ዓ. ም. ወደ ማክሲማ ቤተ መቅደስ ከመጓዛቸው በፊት በኪላምባ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚመሩ ታውቋል።

በማክሲማ ቤተ መቅደስ የሚዘጋጀውን የመቁጠሪያ ጸሎት በመምራት ከምእመናን ጋር እንደሚጸልዩ እና ሰኞ ሚያዝያ 12/2018 ዓ. ም. ወደ ሳውሪሞ በመጓዝ መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ አረጋውያንን ከጎበኙ በኋላ ወደ ሉዋንዳ በመመለስ የአንጎላ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደሚያጠናቅቁ የጉብኝታቸው መርሃ-ግብር አመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2018 ዓ. ም. ጠዋት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር ወደ ሆነች ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚጓዙ መርሃ-ግብሩ ያመለክታል።

 

18 Apr 2026, 17:31