ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እንደ ሐዋርያዊ እረኝነቴ ጦርነትን መደገፍ አልችልም!” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአራት የአፍሪካ አገራት፥ አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ አንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ሲያደርጉ የቆዩትን ሐዋርያው ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ተመልሰዋል። በጉዞአቸው ወቅት ለጋዘጤኞች ባደረጉት ንግግር፥ ተልዕኮአቸው ወንጌልን ለሁሉም ሕዝቦች ማወጅ እንደሆነ ተናግረው፥ በኢራን እና በሊባኖስ በተደረጉ ጦርነቶች የተጎዱ ሕፃናትን በማስታወስ፣ የሞት ቅጣትን በማውገዝ እና ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲከበር አጥብቀው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአፍሪካ አኅጉር የሚያደርጉትን የ11 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ያጠናቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ ተነስተው ወደ ሮም በመመለስ ላይ ሳሉ በጉብኝታቸው ወቅት አብረዋቸው ከተጓዙት ወደ 70 ከሚጠጉ ጋዜጠኞች መካከል ከአምስቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ለጋዜጠኞቹ ምላሽ ከሰጧቸው ጥያቄዎች መካከል ጦርነትን፣ የአሜሪካ እና ኢራን ድርድርን፣ ስደትን፣ የሞት ቅጣትን እና የግብረ ሰዶማውያን ጥንዶች ቡራኬን አስመልክቶ ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል።

በአራት የአፍሪካ አገራት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ተሞክሮን በማስታወስ የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት በአፍሪካ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከሁሉም በላይ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለመገናኘት፣ አብሮ ለመጓዝ እና ለማወቅ የተደረገ ጉብኝት እንደ ነበር አስረድተዋል።

ብዙውን ጊዜ ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስለዚህ ወይም ስለዚያ ጉዳይ ምን ይላሉ? በአንድ ወይም በሌላ አገር መንግሥት ላይ ለምን አይፈርዱም?’ እየተባለ የሚወሩ ነገሮች እንዳሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ሐዋርያዊ ጉዞው ከሁሉም በላይ ወንጌልን የማወጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መልዕክት ማብሰር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበው፥ ይህም ሰዎችን በእምነታቸው፣ በደስታቸው እና በመከራቸው ወቅት የመቅረብ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሰዎች ለሕይወታቸው ኃላፊነትን እንዲወስዱ ማበረታታት እና ሰላማዊ መፍትሄዎችን መፈለግ አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ከአገር መሪዎች ጋር መነጋገር፣ ሃሳብ መለዋወጥ ወይም ስለ ጋራ ጥቅም በማሰብ የበለጠ ዕድል እንዲኖር ማበረታታት እና የአንድ አገር ሃብት ክፍፍልን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ማጤን አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ባደረጓቸው ውይይቶች በሙሉ በሕዝቡ ዘንድ ፍላጎት እንዳለ ማየታቸውን ተናግረዋል።

በጉዞአቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ሕዝብ ጋር መሆን እና አብሮ መጓዝ ከሁሉም በላይ በእምነታችን የምንገልጸው ከዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር የመጋራት ምልክት ነበር ብለዋል።

በካሜሩን-ባሜንዳ የተካሄደውን የሰላም ጉባኤ አስመልክተው በማስመልከት እንደተናገሩት፥ አዲስ አመለካከት እና የሰላም ባሕልን ማበረታታት አለብን ብለው፥ ብዙውን ጊዜ አንዳንድ ሁኔታዎችን ስንገመግም ወደ ዓመፅ፣ ወደ ጦርነት እና ወደ ጥቃት መግባት አለብን የሚል ፈጣን ምላሽ እንዳለ አስታውሰው፥ ይህን በመሰለ ውሳኔ በርካታ ንፁሃን ሰዎች ሲሞቱ ማየታቸውን ገልጸዋል።

በኢራኑ ጥቃት የመጀመሪያ ቀን ልጆቻቸው ከተገደሉባቸው ቤተሰቦች የተላከላቸውን መልዕክት ማየታቸውን ገልጸው፥ ጉዳዩ የሥርዓት ለውጥ ይኖራል ወይስ አይኖርም የሚለው ሳይሆን፥ በርካታ ንፁሃን ሰዎች ሳይሞቱ በፊት ለችግሩ መፍትሄ የሚገኝባቸውን መንገዶች ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢራን ያለው ሁኔታ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በድርድሩ ወቅት ኢራን “አዎ” ስትል አሜሪካ “አይሆንም” እንደምትል ገልጸው፥ በዚህ ሁኔታ ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ አለማወቃቸውን ገልጸዋል። ይህም ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ መዋዠቅ ዋና ምክንያት እንደሆነ ገልጸው፥  ነገር ግን በዚህ ጦርነት ምክንያት በኢራን ውስጥ የሚሰቃዩ ንፁሃን ሰዎች መኖራቸውን ተናግረው፥ “እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ ከሰነዘሩት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጥቃት በኋላ ምን ዓይነት የሥርዓት ለውጥ እንዳለ ግልጽ አይደለም” ብለዋል።

ለሰላም የሚደረገው ውይይት እንዲቀጥል ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለማስፈን፣ የጦርነትን ስጋት ለማስወገድ እና ዓለም አቀፍ ሕግን ለማክበር የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ለማበረታታት እንደሚጥሩ ገልጸው፥ በብዙ ቦታዎች እንዳልታየ ሁሉ ንፁሃን ሰዎች ጥበቃ ማግኘት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሊባኖስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት “ፖፕ ሊዮ እንኳን ደህና መጡ” የሚል ጽሑፍ የያዘ አንድ የሙስሊም ሕጻን ልጅ ፎቶ ይዘው እንደሚጓዙ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ሕጻን በጦርነቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መገደሉን በሐዘን ተናግረው፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን እና እንደ ሐዋርያዊ እረኛ ጦርነትን መደገፍ እንደማይችሉ ገልጸው፥ ሁሉም ሰው ከጥላቻ እና ከመለያየት ይልቅ ከሰላም ባሕል የሚመጡ መልሶችን እንዲፈልግ ለማበረታታት እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

የስደት ጉዳይ እጅግ ውስብስብ እና በርካታ አገራትን የሚነካ ዓለም አቀፍ ክስተት እንደሆነ ተናግረው፥ ሰሜናዊው የዓለማችን ክፍል ደቡባዊውን ክፍል ለመርዳት ምን እያደረገ እንደሚገኝ ጠይቀው፥ ዛሬ ወጣቶች የወደፊት ተስፋን ማግኘት ከማይችሉባቸው አገራት ወደ ሰሜኑ ክፍል የመዛወር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የሰሜኑ ክፍል ለእነዚህ ወጣቶች ዕድሎችን የማመቻቸት አዝማሚያ እንደማያሳይ አስረድተዋል።

“አንድ አገር ድንበሮቹን የመቆጣጠር መብት እንዳለው አምናለሁ” ያሉት ቅዱነታቸው፥ ሁሉም ሰው ያለ ሥርዓት እንዲገባ መፍቀድ አለበት ማለት ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ በመዳረሻ አገሮች ውስጥ ለስደተኞች እንክብካቤ የማይደረግላቸው ከሆነ ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታዎች እንደሚፈጠጥ ተናግረዋል።

በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ምን እየተደረገ እንደሚገኝ የጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ በመንግሥት ዕርዳታም ሆነ በብዙ አገራት ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ሃብታም ኩባንያዎች በጎበኘኋቸው አገራት ውስጥም ቢሆን ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ለምን አንሞርም?” ሲሉ ጠይቀዋል።

“አፍሪካ ብዙውን ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ማዕድናትን ለማውጣት፣ ሃብቷን ለሌሎች አገራት ጥቅም ለማዋል እንደ ምንጭነት ትታያለች” ብለው፥ “ምናልባት በዓለም አቀፍ ደረጃ በእነዚህ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሰዎች ወደ ሌሎች አገራት እንዳይሰደዱ ለማድረግ የበለጠ ፍትህ፣ እኩልነት እና ልማትን ለማስፈን የበለጠ መሥራት አለብን” ብለዋል።

ሰብዓዊ ክብርን በማስመልከት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ብዙውን ጊዜ እንደሚከሰተው ሰዎች ከእንስሳት በከፋ ሁኔታ እንደሚስተናገዱ ገልጸው፥ ለአንዳንድ አገራት ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸው፥ አንድ አገር ከተወሰነ ቁጥር በላይ ስደተችን መቀበል እንደማይችል በግልጽ መንገር እንደሚችል፣ ነገር ግን ስደተኞችን የሚመጡ ከሆነ ሰዎች በመሆናቸው የሚገባቸው ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ሕዝቡን መጎብኘት እና ቅድስት መንበር በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም ቅድስት መንበር አምባገነን መሪዎች ካሏቸው አገራት ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት፥ ከእነዚህ አገራት ጋር በመደበኛ ደረጃ የመነጋገር ዕድል መኖሩን፣ ፍትህን ለማስፈን፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስተዋወቅ፣ የፖለቲካ እስረኞች የሚፈቱበት እና ነፃ የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ብዙ ሥራዎች እንደሚሠሩ አስረድተዋል።

ቅድስት መንበር ገለልተኛነቷን በመጠበቅ እና ከብዙ አገራት ጋር ያላትን አዎንታዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመቀጠል መንገዶችን በመፈለግ እና ወንጌልን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከረች መሆኗን ገልጸዋል። ይህን ጥረቷን ሰዎች በሚፈልጉት መንገድ ቢተረጉሙም ነገር ግን የማንኛውንም አገር ሕዝብ ለመርዳት የምንቻልበት መልካም መንገድ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

የተመሳሳይ ጾታ ጉዳይን በማስመልከት የተነሳውን በማስታወስ በሰጡት ምላሽ፥ በመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ወይም ክፍፍል በጾታዊ ጉዳዮች ላይ መሆን እንደሌለበት ማወቅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ቤተ ክርስቲያኗ ስለ ሥነ-ምግባር ስትናገር ብቸኛው ጉዳይ ወሲባዊ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚታሰብ ተናግረው፥ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ፍትህ፣ እኩልነት፣ የወንዶች እና የሴቶች ነፃነት እና የሃይማኖት ነፃነት የመሳሰሉ ትልቅ እና የበለጠ አስፈላጊ ጉዳዮች ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጥባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉም ሰው ወይም በእርሳቸው ፊርማ ከተፈቀደላቸው ሌላ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ጥንዶች ወይም ግብረ ሰዶማውያን ቡራኬን መስጠት ቅድስት መንበር ፈጽሞ የማትቀበል መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

አንድ ካህን በመስዋዕተ ቅዳሴ ፍጻሜ ላይ ምዕመናኑን በቡራኬ ሲያሰናብት ያ ቡራኬ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት በሙሉ የሚሰጥ እንደሆነ፣ ‘ሁሉም፣ ሁሉም፣ ሁሉም’ የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አባባል የቤተ ክርስቲያኗ እምነት መግለጫ እንደሆነ አስረድተው፥ በዚህም መሠረት “ሁሉም ሰው ኢየሱስን እንዲከተል እና በሕይወቱ ውስጥ ለውጥን እንዲፈልግ ተጋብዟል” ሲሉ በማስረዳት፥ ርዕሡ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም ነገር ግን አንድነትን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በእርሱ ትምህርት ላይ ለመገንባት መንገዶችን መፈለግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የሞት ቅጣትን ጨምሮ ፍትሃዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን በሙሉ እንደሚያወግዙ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ የሞት ቅጣትን በማውገዝ የሰው ሕይወት መከበር እንዳለበት እና ሁሉም ሰው ከተጸነሰበት ጊዜ  አንስቶ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ሕይወቱ መከበር እና ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “አንድ አገዛዝ ወይም አንድ አገር የሌሎች ሰዎችን ሕይወት ያለአግባብ ለማጥፋት ሲወስን ያ በግልጽ ሊወገዝ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

24 Apr 2026, 16:38