ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ "የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ በጦርነት ወቅት የሰላም መልዕክት ነበር" ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 21/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በሳምንታዊው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ ወቅት፥ ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአራት የአፍሪካ አገራት ማለትም በአልጄሪያ፣ በካሜሩን፣ በአንጎላ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ “የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት የሰላም መልዕክት እንደ ነበር አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያደረጉት ንግግር ሙሉ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት ለዕለቱ የተመርጠውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል እናነብላችኋለን፥

“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ አንዳንዶች ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛ። ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28: 16-20)

ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ለምዕመናኑ ያሰሙትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ እንደምን አደራችሁ! እንኳን ደህና መጣችሁ! በዛሬው ዕለት ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአራት የአፍሪካ አገራት ማለትም በአልጄሪያ፣ በካሜሩን፣ በአንጎላ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ያደረግሁትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት መናገር እወዳለሁ።

ከርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናዬ መጀመሪያ አንስቶ በአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ስለማድረግ አስብ ነበረ። እንደ ሐዋርያዊ እረኛ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመገናኘት እና ለማበረታታት ዕድል ስለሰጠኝ፣ እንዲሁም ጦርነት እና በዓለም አቀፍ ሕግም ከባድ እና ተደጋጋሚ ጥሰት እየተፈጸመ ባለበት በዚህ ጊዜ የሰላም መልዕክት በማስተላለፍ የሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎቴን እንድለማመድ ስላደረገኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በሄድኩባቸው አገራት ሁሉ በክብር ለተቀበሉኝ ብጹዓን ጳጳሳት እና የሲቪል ባለሥልጣናት እንዲሁም ጉብኝቴን በስኬት እንድፈጽም ላገዙኝ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

እግዚአብሔር ቢፈቅድ በዚህ ጉብኝቴ የመጀመሪያ መዳረሻዬ እንዲሆን የተመኘሁት፥ በአልጄሪያ ውስጥ ቅዱስ አጎስጢኖስ የኖረባቸውን ቦታዎች ማየት ነበር። ስለዚህ በአንድ በኩል የመንፈሳዊ ማንነቴ መሠረቶችን እንደገና መጎብኘት፥ በሌላ በኩል ለመላው ዓለም እና ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ድልድዮችን መሻገር እና ማጠናከር ነበር። ይህ ድልድይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በፍሬያማ ዘመን ከእስልምናው ዓለም እና ከአፍሪካ አኅጉር ጋር ለመገናኘት ብለው የገነቡት ድልድይ ነው።

በአልጄሪያ የተደረገልኝ አቀባበል አክብሮት የተሞላበት ብቻ ሳይሆን ደማቅም ነበር። እንደ አንድ መሐሪ አባት ልጆች፣ እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች አብረው መኖር እንደሚችሉ ለዓለም ለማሳየት ችለናል። ከዚህም በላይ የቅዱስ አጎስጢኖስ ምሳሌን ለመማር ወቅታዊ አጋጣሚ ነበር። ቅዱስ አጎስጢኖስ በሕይወት ልምዱ፣ በጽሑፎቹ እና በመንፈሳዊነቱ እግዚአብሔርን እና እውነትን በመፈለግ ረገድ ዋና ሰው ነው። ይህ ምስክርነት ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለክርስቲያኖች እና ለእያንዳንዱ ሰው አስፈላጊ የሆነ ምስክርነት ነው።

በጎበኘኋቸው ሌሎች ሦስት የአፍሪካ አገሮች ሕዝቡ በአብዛኛው ክርስቲያን ነው። ስለዚህም በእምነት እና በደማቅ የአቀባበል ድባብ ውስጥ ራሴን ያገኘሁበት ነው። ይህም በአፍሪካውያን ባሕል በመታገዝ ጎልቶ የታየ ደማቅ አቀባበል ነበር። ልክ እንደ ቀድሞዎቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እኔም ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ከነበሩት ሰዎች ጋር በነበረ ጊዜ የደረሰበት ነገር አጋጥሞኛል። ፍትህን ሲጠሙ እና ሲራቡ ባያቸው ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ ‘ድሆች ብፁዓን ናቸው፤ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ሰላም ፈጣሪዎች ብፁዓን ናቸው’ አላቸው። እምነታቸውንም በመገንዘብ፥ ‘እናንተ የምድሪቱ ጨውና የዓለም ብርሃን ናችሁ’ (ማቴ 5፡1-16) አለ።

በካሜሩን ያደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለእርቅ እና ለሰላም አብረን ለመሥራት የማቀርበውን ጥሪዬን ለማጠናከር አስችሎኛል። ምክንያቱም ያች ሀገርም በሚያሳዝን ሁኔታ በውጥረት እና በዓመፅ ትታወቃለች። የአንግሊፎን ክልል ወደ ሆነው ባሜንዳ በመጓዜ ደስ ብሎኛል። እዚያም ሰዎች ለሰላም አብረው እንዲሠሩ አበረታታሁ። ካሜሮን ‘ትንሿ አፍሪካ’ በመባል ትታወቃለች። ይህም የተፈጥሮ አካባቢዋን እና ሃብቷን፣ ብዝሃነቷን እና ብልጽግናዋን ያመለክታል። በዚህ አገላለጽ በካሜሩን ውስጥ የመላው አፍሪካ አኅጉር ፍላጎቶች ይገኛሉ ማለት ነው። ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አስፈላጊነት፣ ለወጣቶች ትኩረት መስጠት፣ ሥር የሰደደውን ችግር ማሸነፍ፣ ይህም ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን ማራመድ፣ የተለያዩ የአዲስ ቅኝ አገዛዝ ዓይነቶችን በአርቆ አሳቢነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር መቃወም እንደሚያስፈልግ ያሳስባል። በካሜሩን ውስጥ ያለችውን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና መላውን የካሜሩን ሕዝብ አመሰግናለሁ። በጉብኝቴ ወቅት የታየው የአንድነት መንፈስ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል እና የወደፊት ምርጫዎችን እና ድርጊቶችን እንዲመራ እጸልያለሁ።

የሐዋርያዊ ጉብኝቴ ሦስተኛው ምዕራፍ ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ጋር የተያያዘች፣ ለብዙ መቶ ዘመናት የቆየ የክርስትና ባሕል ያላት አንጎላ የተባለች ትልቅ አገር ነበረች። ልክ እንደ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ነፃነቷን ካገኘች በኋላ አንጎላ በርካታ ችግሮችን አሳልፋለች። አንጎላ ውስጥ ረጅም እና ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዷል። በዚህ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር የአልጎላን ቤተ ክርስቲያን መርቷታል፣ አጽድቷታልም። በወንጌል ምስክርነት፣ የሰው ልጅ ዕድገትን በማስፋፋት፣ እርቅን እና ሰላም በማገልገል ረገድ እንድታድግ እና እንድትለወጥ አድርጓታል። ለነፃ ሕዝብ ነፃ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋል! ማማ ሙክሲማ የእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ ትርጉሙም “የልብ እናት” ማለት ነው። የአንጎላ ሕዝብ የሚመታ ልብ እንዳለው ተሰማኝ። በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን በማየቴ ተደስቻለሁ። ይህም የመንግሥተ ሰማያት ትንቢት በሕዝባቸው መካከል መናገራቸውን ይገልጻል። ሙሉ በሙሉ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የቆሙ የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎችን አይቻለሁ። በድካምና በመከራ የተሸነፉ ነገር ግን በወንጌል ደስታ የሚያበሩ በርካታ አረጋውያንን አይቻለሁ። በርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰባቸው ባዶ ተስፋዎችን የሚሰጡ ሃያላንን ለመቋቋም የሚዘምሩ እና ለትንሳኤው ጌታ የምስጋና ዜማዎችን የሚያቀርቡ ወንድ እና ሴት መዘምራንን አይቻለሁ።

ይህ ተስፋ ተጨባጭ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል በምስክርነት እና በድፍረት በማወጅ ለሁሉም ሰው መብቶች እውቅናን የመስጠት እና ትክክለኛ ክብራቸውን የማሳደግ ኃላፊነት አለባት። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከአንጎላ የሲቪል ባለስልጣናት ጋር እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ከፍትኛ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር በተለይም በጤና አጠባበቅ እና በትምህርት ዘርፎች የምታበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኗን ማረጋገጥ ችያለሁ።

ከ170 ዓመታት በፊት ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበከባት እና የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ የመጨረሻዋ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ነበረች። የኢኳቶሪያል ጊኒ ሕዝብ በባህላዊ ጥበብ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን በመታገዝ የታሪካቸውን ውጣ ውረዶች ተቋቁሟል። በቅርብ ቀናት ውስጥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፊት በተስፋ ወደፊት አብረው ለመጓዝ ያላቸውን ቁርጠኝነት በታላቅ ጉጉት አድሰዋል።

በኢኳቶሪያል ጊኒ ባታ ከተማ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ የተከሰተውን ነገር አልረሳውም። ታራሚዎቹ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ ለእግዚአብሔር እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የምስጋና መዝሙር ዘምረዋል። ለሰሩት ኃጢአት እና ለነጻነታቸው እንዲጸልዩ ጠይቀዋል። እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። በዝናብ ውስጥ ‘አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር!’ ጸሎትን ከእኔ ጋር ጸልየዋል። ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት እውነተኛ ምልክት ነው! አሁንም በዝናብ ውስጥ ከወጣቶች ጋር የተደረገ ታላቅ ስብሰባ በባታ ስታዲየም ውስጥ ተጀመረ። በወንጌል ውስጥ ወደ ነጻ እና ኃላፊነት ወደሚሰማው ዕድገት የሚያመራውን መንገድ ያገኙ ወጣቶችን የሚያነቃቁ ምስክርነቶች የቀረቡበት እና ክርስቲያናዊ ደስታ የተገለጠበት በዓል ነበር። ይህ በማግሥቱ በቀረበው የቅዱስ ቁርባን ስግደት የተጠናቀቀው ዝግጅት የኢኳቶሪያል ጊኒ እና የሌሎች ሦስት አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝቴ በበጎነት እንዲጠናቀቅ አድርጎታል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐዋርያዊ ጉብኝት የአፍሪካ ሕዝቦች ድምፃቸውን ለማሰማት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በመሆን የሚገኘውን ደስታ ለመካፈል፣ የተሻለ የወደፊት ተስፋን ለማግኘት፣ ለእያንዳንዱ ሰው ክብርን ለመግለጽ ዕድል የሰጠ ነው። ይህንን ዕድል በመስጠቴ ደስተኛ ነኝ። እንደዚሁም እነርሱም የሰጡኝ ነገር በሙሉ ለልቤ እና ለሐዋርያዊ አገልግሎቴ የማይገመት ሃብት በመሆኑ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።”

29 Apr 2026, 16:46