ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጀርመን ከኮሎኝ ሀገረ ስብከት ከመጡት ልዑካን ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጀርመን ከኮሎኝ ሀገረ ስብከት ከመጡት ልዑካን ጋር   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በበጎ አድራጎት ሥራዋ እውነትን እንድትመሰክር አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጀርመን ከኮሎኝ ሀገረ ስብከት ከመጡት ልዑካን ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ለልዑካኑ ባደረጉት ንግግር፥ በሁሉም አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ሀገረ ስብከቶች የጋራ ድጋፍ በመስጠት እውነትን በበጎ አድራጎት ሥራ እንድትመሰክር አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ሚያዚያ 22/2018 ዓ. ም. በኮሎኝ ሀገረ ስብከት የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን እና ውይይት ጽሕፈት ቤት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ከሚያከብሩ የሀገረ ስብከቱ ልዑካን ጋር በቫቲካን ተገናኝተው፥ መታሰቢያ በዓሉ የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊነት እና በውይይት አስፈላጊነት ላይ ለማሰላሰል ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

“ቤተ ክርስቲያን በብርሃነ ትንሣኤው በመታገዝ ራሷን ለሁሉም ሕዝቦች የተላከች መሆኗን የምትገነዝብ፥ ይህን የምታደርገው እራሷን በማስገደድ ሳይሆን በበጎ አድራጎት ሥራ እውነትን በመመስከር ነው” ብለው፥ “ውይይት ኅብረትን በማጠናከር የመግባቢያ መንገዶችን እንደሚከፍት እና የሰላምን ዓላማ ያገለግላል” ሲሉ አስረድተዋል።

በመወያየት እና በኅብረት ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የዓለም አንድነት እና የተስፋ ምልክት በማድረግ ሁሉንም ወደ ራሱ ይጠራል” ሲሉ አስረተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኮሎኝ ሀገረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ገጽታ ትንቢታዊ ግልጽነትን በማሳየቱ አመስግነው፥ ይህም “እርስ በርስ ለመገናኘት፣ ሃሳብ ለመለዋወጥ እና ለውይይት ባለው ፍላጎት ይገለጻል” ብለዋል።

ሀገረ ስብከቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1954 ዓ. ም. ከቶኪዮ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር “ሚዜሪዮር” እና “አድቬኒያትን” ጨምሮ በርካታ የዕርዳታ ተነሳሽነቶችን ማቋቋማቸውን አስታውሰዋል።

“ይህ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ ነው የሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ራዕይ ከአውሮፓ ወሰን አልፎ የሄደ  የአንድነት እና የውይይት ባሕል የሚቀጥል እና በድርጅታችሁ ማንነት ውስጥም ቀዳሚ ሆኖ ይቆያል” ብለዋል።

የኮሎኝ ሀገረ ስብከት እንዲሁም ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ የሚያደርጉ ኤጀንሲዎች (ROACO) መሥራች አባል በመሆን፥ በረሃብ፣ በጎርፍ እና በጦርነት አደጋዎች ለተጎዱ ክልሎች ዕርዳታ የሚሰጥ እንደሆነ ታውቋል።

በሀገረ ስብከቱ የሚደገፉ ሌሎች ተነሳሽነቶች፥ ለዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠትን እና አረጋውያን ካኅናትን መርዳት እንደሚያካትት ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጳጳስ ሆነው በፔሩ በነበሩ ጊዜ የኮሎኝ ሀገረ ስብከት በርካታ የፔሩ ሀገረ ስብከቶችን መደገፉን አስታውሰው፥ ከእነዚህም ውስጥ የኦክስጅን አምራች ማሽኖችን መግዛት ይገኙበታል።

“በልግስና አገልግሎታችሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ገጽታ ግልጽ እና ተጨባጭ ሆኖ በመታየት አንድነትን የሚያጠናክር፣ ብዙውን ጊዜ በመለያየት እና በጭንቀት በሚታወቀው ዓለም ውስጥ የሰላም ወንጌልን ይመሰክራል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የኮሎኝ ሀገረ ስብከት የበጎ አድራጎት ተልዕኮውን እንዲቀጥል በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ላሉ ክርስቲያኖች እና ከትውልድ አገራቸው ለመሸሽ ለተገደዱ ሰዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።

“በዚህ የበጎ አድራጎት ተልዕኮ እንድትጸኑ አበረታታችኋለሁ” በማለት፥ ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ቅርበት እንዲለማመዱት በማሳሰብ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

30 Apr 2026, 16:32