ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአፍሪቃ ብቸኛዋ ስፓኒሽ ተናጋሪ አገር በሆነችው ኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከሰላሳ አንድ ደቂቃ ላይ የደረሱ ሲሆን፥ በኢኳቶሪያል ጊኒ እስከ ሐሙስ ሚያዝያ 15 ድረስ የሚቆዩ ሲሆን፥ ይህም የ11 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጨረሻ ዙር እንደሆነ የጉዞአቸው መርሃ-ግብር አመልክቷል።
ቅዱስነታቸው በአንጎላ ሲያደርጉ የቆዩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ከመዲናዋ ሉዋንዳ አየር ማረፊያ የተነሱት በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከአሥራ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ እንደ ሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመካከለኛዋ የአፍሪካ አገር አንጎላ ውስጥ ሦስት ቀናትን ያሳለፉ ሲሆን፥ በእነዚህ ቀናት ሦስት ከተሞችን እነርሱም ሉዋንዳ፣ ሙክሲማ እና ሳዩሪሞን ጎብኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሲደርሱ በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት የሪፐብሊኩን ፕሬዝዳንት ከጉበኙ በኋላ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋርም ተገናኝተዋል።
ቀጥሎም በብሔራዊ ዩኒቨርሲቲው የሊዮ 14ኛ ካምፓስ ውስጥ ዓለም አቀፍ የባሕል ተወካዮችን ለማግኘት፣ በዣን ፒየር ኦሊ የአእምሮ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችን እና ታካሚዎችን ለመጎብኘት እንዲሁም ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በግል ለመሰብሰብ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ሚያዝያ 14/2018 ዓ. ም. ከማላቦ ወደ ሞንጎሞ በመጓዝ በጽንሰተ ማርያም ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤትን ይጎበኛሉ።
ከዚያም ጉዞአቸውን ወደ ባታ በማድረግ በአካባቢው የሚገኘውን እስር ቤት ከጎበኙ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 7/2021 ዓ. ም. በደረሰው ፍንዳታ በተጎዱ ሰዎች መታሰቢያ ላይ ለመጸለይ እና በከተማው ስታዲየም ከወጣቶች እና ከቤተሰቦች ጋር ከተገናኙ በኋላ በቀኑ መጨረሻ ወደ ማላቦ እንደሚመለሱ ታውቋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀን በሆነው ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. በማላቦ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ በአየር ማረፊያው በሚዘጋጅ የስንብት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሳተፋሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዚያው ቀን ወደ ሮም እንደሚመለሱ ይጠበቃል።
