ፈልግ

በኮሎምቢያ ደቡብ ምዕራብ ክልል የተፈጸመ የአማጽያን ጥቃት ሰለባዎች በኮሎምቢያ ደቡብ ምዕራብ ክልል የተፈጸመ የአማጽያን ጥቃት ሰለባዎች  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በደቡብ ምዕራብ ኮሎምቢያ የሚገኙ የጥቃት ሰለባዎችን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኮሎምቢያ ደቡብ ምዕራብ ክልል የዓመፅ ጥቃቶች እየተባባሱ ባሉበት ወቅት ሁሉም ሰው ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት እንዲቃወም በማሳሰብ፥ በርካታ የጥቃቱ ሰለባዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ረቡዕ ሚያዝያ 21/2018 ዓ. ም. ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ታዳሚዎች መካከል የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመናንን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር፥ በደቡብ ምዕራብ ኮሎምቢያ እየጨመረ የመጣውን ዓመፅ አስታውሰዋል።

የአማፂያን ቡድኖች ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ቢያንስ 26 ጥቃቶችን በሲቪሎች እና በወታደራዊ ማዕከላት ላይ በመፈጸም በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለም ዕመናኑ ሰላምታ ባቀርቡበት ወቅት፥ በኮሎምቢያ ያለውን ሁኔታ በሐዘን በማስታወስ፥ ጥቃቱ በሰው ሕይወት ላይ ባደረሰው ከባድ የሞት አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ የአመጹ ሰለባዎችንም በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

“ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ያለኝን ቅርበት በጸሎት እገልጻለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ሁሉም ሰው ማንኛውንም ዓይነት ዓመፅ አቁሞ በቆራጥነት የሰላምን መንገድ እንዲመርጥ አበረታታለሁ” ብለዋል።

ከግንቦት ምርጫ በፊት እየተባባሰ የመጣው ዓመፅ

በኮሎምቢያ ዓመፅ እየተስፋፋ የመጣው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 31 ቀን ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት እንደ ሆነ ታውቋል።

የኮሎምቢያ መንግሥት ባለስልጣናት ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጓቸው፥ የኮሎምቢያ አብዮታዊ ጦር ኃይሎች (FARC-EMC) አማፂ ቡድን ሲሆን፥ ይህም የአገሪቱ መንግሥት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. የሰላም ስምምነት ካደረገ በኋላ የፈረሰ አማፂ ቡድን እንደሆነ ታውቋል።

ቡድኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሚያዝያ 24 ጀምሮ ቢያንስ 26 ጥቃቶችን እንደፈጸመ ሲነገር በጥቃቶችም በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉ ተነግሯል።

ያለፈው ቅዳሜ በካሊ እና ፖፓያን ከተሞች መካከል በሚገኝ አውራ ጎዳና ላይ በተከሰተው ከፍተኛ ፍንዳታ 21 ሰዎችን መግደሉ ታውቋል።

ተንታኞች፥ “አማጺ ቡድኑ (FARC-EMC) በግንቦት መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለሚመረጥ ማንኛውም ሰው አቅሙን ለማሳየት እና ተዓማኒነቱን ለማረጋገጥ እየሞከረ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል።

አማጺ ቡድኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. የሰላም ስምምነቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባልሆነው ኔስተር ቬራ በተለምዶ ኢቫን ሞርዲስኮ ተብሎ በሚጠራ ሰው የሚመራ መሆኑ ታውቋል።

አማፂያኑ በካውካ እና ቫሌ ዴል ካውካ ግዛቶች ውስጥ ጠንካራ መሠረት ያለው ሲሆን፥ የዕፅ ዝውውሮችን እና ሕገወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎችን ለመቆጣጠር እየተዋጉ እንደሚገኝ ታውቋል።

ቡድኑ እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ2023 ዓ. ም. መጨረሻ ላይ ከኮሎምቢያ መንግሥት ጋር የሰላም ድርድር የጀመረ ቢሆንም ነገር ግን አንድ ወገን በሚያዝያ ወር 2024 ዓ. ም. ውይይቱን ትቶ በመውጣት መንግሥት ላይ የሚያደርገውን ትግል ማደሱ ታውቋል።

“አማጺ ቡድኑ (FARC-EMC) የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማስፈራራት ድሮኖችን እና የመኪና ቦምቦችን በመጠቀም እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ገቢ ለማሰባሰብ አፈና እያካሄደ እና ግብር በመጣል ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

29 Apr 2026, 16:55