ፈልግ

የቼርኖቤል የኒውክሌር አደጋ 40ኛ ዓመት መታሰቢያ የቼርኖቤል የኒውክሌር አደጋ 40ኛ ዓመት መታሰቢያ  (AFP or licensors)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኒውክሌር ኃይል በሰላማዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቼርኖቤል የኒውክሌር አደጋ 40ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር፥ እያንዳንዱን የኒውክሌር ኃይል በማስተዋል እና ኃላፊነት በተሞላ መንገድ በመጠቀም ለሕይወት እና ለሰላም አገልግሎት እንዲውል ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ዘንድ ጸሎት ለማድረስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ ሚያዝያ 18 /2018 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ የኒውክሌር ኃይል ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው ይህን ጥሪ ያቀረቡት፥ “የሰው ልጅን ሕሊና የሚያሳይ” በማለት በገለጹት የቼርኖቤል የኒውክሌር አደጋ 40ኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን ላይ እንደሆነ ታውቋል።

“የአደጋው ሰለባዎችን እና በመዘዙ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ የሚሰቃዩትን በሙሉ ለእግዚአብሔር ምሕረት እናቀርባቸዋለን” ብለዋል።

ከዩክሬን መዲና ኪየቭ በስተሰሜን 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው እና የሶቪየት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ በሆነው የቼርኖቤል የኑክሌር ኃይል ማመንጫ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 26/1986 ዓ. ም. በመፈንዳቱ 31 ሰዎችን ወዲያው ሲገድል ከዚያን ጊዜ ወዲህ በነበሩ በርካታ ዓመታት ውስጥ በጨረር መመረዝ ምክንያት ሌሎች 15,000 ሰዎችን ለሞቶት መዳረጉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባቀረቡት ጥሪ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡትን ኃይለኛ ቴክኖሎጂዎች የመጠቀም አደጋን አስጠንቅቀው፥ በኒውክሌር ኃይል ዙሪያ ማስተዋል እና ኃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ሁሉም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ዘወትር በማስተዋል እና በኃላፊነት እንደሚከናወኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “በዚህም የአቶሚክ ኃይል ለሕይወት እና ለሰላም ጥቅም ሊውል ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

 

27 Apr 2026, 16:13