ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይቅር ስንል እና አብረን ስንጸልይ ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነው” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንጎላ ሳውሪሞ ከተማ በሚገኝ የአቅመ ደካሞች መንከባከቢያ ማዕከል የሚኖሩ አረጋውያንን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የአንድ አገር ማንነት የሚገለጸው ለአቅመ ደካሞች በሚያደርገው እንክብካቤ ጭምር መሆኑን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአንጎላ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሦስተኛ ቀን የጀመሩት በሰሜናዊ ምሥራቅ በምትገኝ ሳውሪሞ ከተማ ሰኞ ሚያዝያ 12/2018 ዓ. ም. ጠዋት ባደረጉት በረራ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው ወደ ከተማይቱ ከደረሱ በኋላ በአንጎላ መንግሥት ወደሚተዳደር የአረጋውያን ማዕከል ተጉዘዋል።

በነዋሪዎቹ “ላር” ወይም “ቤት” በመባል የሚታወቀው ተቋሙ 62 አረጋውያንን እንደሚያስተናግድ እና ከእነዚህም ውስጥ 26ቱ ወንዶች እና 36ቱ ሴቶች እንደሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በማዕከሉ ውስጥ ለሚገኙት አረጋውያን ባደረጉት ንግግር፥ በተደረገላቸው በእምነት ለተሞላ አቀባበል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ እውነተኛ የቤተሰብ ድባብ ባለበት ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ያላቸውን ተስፋ አጋርተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ቤት በመጎብኘት ከሐዋርያው ጴጥሮስ አማች ጋር መሆን እና ብዙውን ጊዜ በቅፍርናሆም የማርያምን፣ የማርታን እና የአልዓዛርን ቤት መጎብኘት እንደሚወድ አስታውሰዋል።

በእንክብካቤ ማዕከሉም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአረጋውያን ጋር እንደሚኖር በተለይም እርስ በርስ ይቅር ሲባባሉ እና እርቅን ሲፈልጉ በመካከላቸው የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።

“እርስ በርሳችሁ ስትዋደዱ እና እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እርስ በርር ለመረዳዳት በሞከራችሁ ቁጥር ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችሁ ይኖራል” ብለው፥ “ሁላችሁም ወይም አንዳንዶቻችሁም በትህትና አብራችሁ በምትጸልዩበት ጊዜ እርሱ በመካከላችሁ አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ “ላር” የእንክብካቤ ቤት ያሉ ተነሳሽነቶችን በመደገፋቸው የአንጎላ ባለሥልጣናትን አመስግነዋል።

“ለደካሞች የሚደረግ እንክብካቤ የአንድ አገር ማኅበራዊ ሕይወት ጥራት የሚለካበት እጅግ አስፈላጊ ምልክት ነው” ብለው፥ “አረጋውያን ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የሰዎችን ጥበብ ጠብቀው የሚያቆዩ በመሆናቸው መደመጥን እንደሚፈልጉ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለአረጋውያኑ በመጸለይ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንክብካቤ በአደራ በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ቤተ ክርስቲያን ከሳውሪሞ የአረጋውያን ማዕከል ጋር ያላት የጠበቀ ግንኙነት

የእንክብካቤ ማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ጆርጂና ምዋንዱምባ፥ የአካባቢው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በማዕከሉ ውስጥ ከሚኖሩት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው፥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ከመስጠት በተጨማሪ ለተቋሙ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።

በማዕከሉ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አረጋውያን ለመዝናናት እና ለራሳቸው ምግብን ለማቅረብ ሲሉ ትናንሽ የአትክልት ሥፍራዎች እንዳላቸው ዱልሴ አራዩ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ምንም እንኳን አንዳንዶች የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ባይሆኑም ብዙውን ጊዜ በማዕከሉ ውስጥ አብረው በመሆን በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ምዋንዱምባ በአንጎላ ውስጥ ለአረጋውያን ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅር በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ የጥንቆላ ተግባር ሊወገድ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “በዚህም ቤተሰቦች በአጉል እምነት ስም አረጋውያን ወላጆቻቸውን ማግለልን ያቆማሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

21 Apr 2026, 16:49