ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚገኘውን የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት ጎበኙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያን ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ በምሥራቅ ሞንጎሞ ከተማ የሚገኘውን እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም የተቋቋመውን የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት ረቡዕ ሚያዝያ 14/2018 ዓ. ም. ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ትምህርት ቤቱን የጎበኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያረፉበት የመጀመሪያ ዓመት ከተዘከረ ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም በሚገኘው ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ለቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በላኩት መልዕክት፥ “ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የብዙዎችን ልብ የነኩ፣ የእግዚአብሔር ደቀ መዝሙር ሆነው የቆዩ፣ ለጥምቀታቸው እና ለጵጵስና አገልግሎታቸው እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ የነበሩ” በማለት ጠርተዋቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እረኛ ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰው፣ የለውጥ ምልክት እያደገ በመጣበት ዘመን ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ እና ደፋር ምስክር እንደነበሩ አስረድተዋል።
አክለውም በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት አብሮአቸው የነበሩት ጋዜጠኞች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለቤተ ክርስቲያን እና ለዓለም በስጦታነት ያበረከተውን እግዚአብሔር እንዲያመሰግኑት ጠይቀዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት፥ ቴክኖሎጂን እና ሙያን በተለይም ለወጣቶች ለማስተዋወቅ የሚሠራ የትምህርት ተቋም እንደ ሆነ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው ከተቋሙ ጉብኝት ቀደም ብሎ በከተማው በሚገኘው የጽንሰተ ማርያም ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ማቅረባቸው እና እንዲሁም ከታራሚዎች እና ከወጣቶች ጋር ተገናኝተው እንደ ነበር ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. በኢኳቶሪያል ጊኒ የመጨረሻውን መስዋዕተ ቅዳሴ ካቀረቡ በኋላ የ11 ቀናት የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ሮም እንደሚመለሱ ታውቋል።
