ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ድልን መቀዳጀት ያለበት ፍቅር እንጂ ጦርነት መሆን የለበትም” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ከፍተኛ የአምልኮ ሥፍራዎች መካከል አንዱ ወደ ሆነውን እና “እማማ ሙክሲማ” በመባል ወደሚታወቀው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ እሁድ ሚያዝያ 11/2018 ዓ. ም. ንግደት በማድረግ እዚያው ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመቁጠሪያ ጸሎት አድርሰዋል።
ከዋና ከተማዋ ከሉዋንዳ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው “እማማ ሙክሲማ” መቅደስ በኪምቡንዱ ውስጥ ትርጉሙ፥ “የልብ እናት” ማለት ሲሆን፥ ቤተ መቅደሱ ለዘመናት ያህል ለአንጎላውያን የጸሎት ቦታ ሆኖ ቆይቷል። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ይህ ቤተ መቅደስ በቅኝ ግዛት አገዛዝ እና በረጅም የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ጨምሮ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት የአምልኮ ማዕከል ሆኖ የቆየ ሲሆን፥ ዛሬ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን መንፈሳዊ ጉዞ የሚያደርጉበት ሥፍራ ሆኖ ቀጥሏል።
ለጸሎት ጊዜው የቀረበ ምስጋና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለወጣቶች፣ ለእመቤታችን ማርያም ማኅበር አባላት እና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለተሰበሰቡ ሌሎች በርካታ ምእመናን ባደረጉት ንግግር፥ “ወደ እመቤታችን ማርያም ጸሎት የሚቀርብበት” የተባለውን ጊዜ ከአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር ለመካፈል በመቻላቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ምዕመናኑ ከእርሳቸው ጋር በኅብረት ባቀረቡት የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ጸሎቱ በቤተ ክርስቲያን ባሕል ላይ የተመሠረተ ተደራሽነት ያለው የጸሎት ዓይነት እንደሆነ አስረድተው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመጥቀስ፥ ይህ ጸሎት ጥንታዊ የክርስትናን ባሕል የሚጠብቅ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውጁ የሚያነሳሳ ጸሎት እንደሆነ ገልጸውታል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በሕዝቡ መካከል ያለውን ጠንካራ የእምነት ስሜት በመግልጽ፥ “ሕያው እና ለጋ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ ስለ ቤተ መቅደሱ ታሪካዊ ጠቀሜታ ሲናገሩ፥ “ትውልዶች በደስታም ሆነ በችግር ጊዜ የሚጸልዩበት ሥፍራ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ “እማማ ሙክሲማ ሁሉንም ሰው በደስታ የምትቀበል፣ ሁሉንም የምታዳምጥ እና ለሁሉም የምትጸልይ ናት” ሲሉ አስረድተዋል።
በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት የተደረገ ጉብኝት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ ቤተ መቅደሱ ጉብኝት ያደረጉት በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት መሆኑ ሲታወቅ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የጉዞአቸው መጨረሻ አድርገው የሚያምኑትን እንደሚያመለክት አፅንዖት ሰጥተው፥ በአሁኑ ጊዜ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምእመናን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተለይም በልጇ ሕይወት ውስጥ የተከሰቱትን ክስተቶች በማሰላሰል እና በማድነቅ ችሎታዋ እንደ ሞዴል አድርገው እንዲመለከቷት በማበረታታት፥ ክርስቲያኖች ይህን በማድረጋቸው ሁለንተናዊ እና ለሌሎች ትኩረት የሚሰጥ ፍቅር እንዲያሳድጉ ተጋብዘዋል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ ጸሎት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበው፥ በተለይም ለተቸገሩ ሰዎች እንክብካቤን በማድረግ እንደ ምግብ፣ የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት ዕድል እና ለአረጋውያን የተከበረ የኑሮ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው በማሳሰብ፥ እነዚህ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ሥራዎች አስፈላጊ የፍቅር መገለጫዎች እንደሆኑ ገልጸው፥ እናት ልጆቿን በሙሉ እንደምወዳቸው እና ይህ ምሳሌ ምእመናን ሌሎች ሰዎችን በተለይም ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎች ባላቸው ቁርጠኝነት መሪያቸው መሆን እንዳለበት አክለዋል።
የብርሃነ ትንሳኤው ምልክት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ምዕመናን ለማስተናገድ የታሰበ የአዲስ እና ትልቅ ቤተ መቅደስ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንን ፕሮጀክት የተስፋ ምልክት እና በተለይም ወጣቶች የበለጠ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ማኅበረሰብን እንዲገነቡ የሚረዳ ግብዣ እንደሆነ ገልጸዋል። የወንጌል እሴቶች የግል ሕይወትን እና ሰፋፊ ማኅበራዊ መዋቅሮችን ሊቀርጹ የሚችሉበት መንገድ እንደሆነ በማስረዳት፥ ለወጣቶች በቀጥታ ባቀረቡት ጥሪ፥ ከጦርነት፣ ከኢ-ፍትሃዊነት፣ ከድህነት እና ከሙስና የጸዳ ዓለምን እንዲገነቡ አሳስበዋል
በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ “ድልን መቀዳጀት ያለበት ጦርነት ሳይሆን ፍቅር ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ምዕመናን ራሳቸውን ለእመቤታችን ማርያም አደራ እንዲሰጡ እና የእግዚአብሔርን በረከት በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እንዲሸከሙት ጥሪ አቅርበው፥ እንዲሁም ለሌሎች ተስፋናን አንድነትን በማምጣት ቤተ መቅደሱን “የሕይወት መልዕክተኛ” እንዲያደርጉት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
