ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የኢኳቶሪያል ጊኒ መሪዎች ስለ ፍትህና ልማት እንዲያስቡ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አራተኛ እና የመጨረሻ አገር ወደ ሆነች ኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ ሲደርሱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማላቦ ለሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማቶች ንግግር ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በዚህ የመጀመሪያ ይፋዊ ንግግራቸው የኢኳቶሪያል ጊኒ መሪዎች ማግለልን በመቃወም ለሰብዓዊ ክብር ትኩረት እንዲሰጡ፥ ልማትን ለግል ስልጣንና ትርፍ ከማድረግ ይልቅ ወደ ጋራ ጥቅም በመዞር ፍትህንና ልማትን እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ ይፋዊ ንግግር፣ በአገሪቱ ዋና ከተማ ማላቦ ውስጥ ከፖለቲካ ባለሥልጣናት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና የዲፕሎማሲ አባላት ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎ ​​አጭር የአቀባበል ንግግር በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አገሪቱን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1982 ዓ. ም. በጎበኟት ጊዜ የአገር ርዕሠ መስተዳድር “የሕዝብ ሕያው ምኞት፣ እውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰብዓዊ ክብር እና የእያንዳንዱን ሰው መብቶች ለማስተዋወቅ የሚሰበሰቡበት ማዕከል ነው” ማለታቸውን አስታውሰው፥ ይህ መልዕክት ወቅታዊ ሆኖ እንደሚቀጥል እና የሕዝብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎችን የፈተን መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ለቅዱስነታቸው የአቀባበል ንግግር  ሲያደርጉ
ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ለቅዱስነታቸው የአቀባበል ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

የእምነት ነጽነትን ማረጋገጥ

ቅዱስነታቸው በመቀጠል “ደስታ እና ተስፋ” በሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ ውስጥ፥ “የዘመናችን ሰዎች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘንና ጭንቀት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ደስታና ተስፋ ጭምር ናቸው” የሚለውን በመጥቀስ፥ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እምነትን በማረጋገጥ፥ ፈጣን ለውጥ እያሳዩ የሚገኙትን የአገሪቱን ሕዝቦች ለማጽናናት በማሰብ የሚደረግ ሐዋርይዊ ጉብኝት እንደሆነ አስረድተዋል።

የሂፖው ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ “በእግዚአብሔር ከተማ” እና “በምድራዊት ከተማ” መካከል ያለውን ልዩነት አስመልክቶ በተናገረው ላይ በማስተንተን እንድተናገሩት፥ “የእግዚአብሔር ከተማ ያልተገደበ ፍቅር የተገለጠበት” ሲሉ ገልጸውት፥ “ምድራዊት ከተማ ደግሞ በራስ የመተማመን ፍቅር እና ወደ ጥፋት የሚያመራ የሥልጣን እና የዓለም ክብር ምኞት” እንደሆነ ገልጸው፥ ባለሥልጣናቱ በየትኛው ከተማ ውስጥ ማገልገል እንደሚፈልጉ በመጠየቅ የእነዚህ አገልግሎቶች ልዩነት ከግል እና ከፖለቲካዊ መንገድ ጋር በማገናዘብ እንዲያስቡት ጋብዘዋል።

አዲስ የሰላም ከተማ

ኢኳቶሪያል ጊኒ “ሲውዳድ ዴ ላ ፓዝ” ወይም “የሰላም ከተማ” የተባለ አዲስ መዲናን ለመገንባት ማቀዷን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ስሙ ራሱ ሥነ-ምግባርራዊ የአስተንትኖ ሃሳብ በማቅረብ፥ የፖለቲካ ሕይወት በኢ-ፍትሃዊ ሃብት ፍለጋ እና በገናናነት ቅዠት መመራት እንደሌለበት፥ ይልቁንም ዘላቂነት ወዳለው ነገር እንዲያተኩር አሳስበዋል።

የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ሚና፥ “የሥነ-ምግባር መስፈርቶችን እና ትክክለኛ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን በማቅረብ አገራት የሕዝባቸውን እና የመንግሥታቸውን ሉዓላዊነት እንዲያከበሩ” ማሳሰብ እንደሆነ ተናግረው፥ እያንዳንዱን ትውልድ አዳዲስ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙት እና አዲስ ግንዛቤ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ማግለል ኢ-ፍትሃዊ ነው

ዘመናዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በማስመልከት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “ማግለል የማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት አዲስ ገጽታ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀው፥ በአናሳ እና በብዙሃኑ መካከል ያለው ​​ክፍተት እየሰፋ መምጣቱን በማስረዳት፥ “የመሬት፣ የምግብ፣ የመኖሪያ ቤት እና የሥራ ዕድል አለመኖር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አቅም ጋር ያለውን ልዩነት በመግለጽ፥ ይህም ሞባይል ስልኮችን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ወይም “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን” እንደሚያካትት አስረድተዋል።

የፖለቲካ መሪዎች ለሁሉ አቀፍ የሰው ልጅ ልማት እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን እንዲያስወግዱ ጥሪ በማቅረብ፣ ይህም በአንድነት እና በዓለም አቀፍ የዕቃዎች መዳረሻ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ዕድገቶች በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የሚያሳድሩትን ልዩ ተጽዕኖ ስጋት በማስታወስ፥ እነዚህ ተግዳሮቶች የፍጥረት ጥበቃን፣ የማኅበረሰቦች መብቶችን፣ የሠራተኛ ክብር እና የሕዝብ ጤና ጥበቃን ሊጋርዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ከፍተኛ ባለሥልጣናት የቅዱስነታቸው ንግግር በማዳመጥ ላይ
ከፍተኛ ባለሥልጣናት የቅዱስነታቸው ንግግር በማዳመጥ ላይ   (@Vatican Media)

ለሞት የሚዳርግ የኢኮኖሚ ሥርዓት መቃወም

ከአንድ ዓመት በፊት ያረፉት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በመድገም፥ መገለልን እና የኑሮ አለመመጣጠን የሚያበረታታ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ችላ ማለት እንደሚገባ አሳስበው፥ እንዲህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለሞት እንደሚዳርግ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ጦርነቶች ዓለም አቀፍ ሕግን ወይም የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን የሚያከብሩ ሳይሆን፥ ከዘይትና ከማዕድን ሃብቶች ብዝበዛ ጋር የተያያዙ ናቸው” ሲሉ አክለዋል።

ቴክኖሎጂን ለወታደራዊ ዓላማ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ያስጠነቀቁት ቅዱስነታቸው፥ “የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ በፖለቲካ ኃላፊነት ሳቢያ አቅጣጫን በመለወጥ በአሳዛኝ ሁኔታ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተዋል። ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማክበር እንደሚገባ አሳስበው፥ “የሞት ድርጊቶችን ለማጽደቅ የእግዚአብሔርን ስም መጠራት ተገቢ አይደለም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ነፃና ኃላፊነት የሚሰማው ሕሊና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው ማጠቃለያ የአገሪቱን ወጣቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ኢኳቶሪያል ጊኒ ነፃ እና ኃላፊነት የሚሰማው ሕሊና የመፍጠር አቅም ያላት ወጣት አገር እንደሆነች ገልጸው፥ መሪዎቿ በጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ሥርዓትን እንዲደግፉ በማረታታት፥ “ለወጣቶች ሚና እና መተማመን አዲስ ድፍረት የሚሰጥ የትምህርት ማዕቀፍ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፥ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎ ጋር በመሆን በክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

 

22 Apr 2026, 12:28