ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔርን መታዘዝ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

በካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኝ ባሜንዳ ከተማ መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ በክልሉ ውስጥ ያሉትን በርካታ የድህነት እና የኢ-ፍትሃዊነት ዓይነቶች በማውገዝ፥ ካሜሮናውያን የሰላም እና የዕርቅ ሕይወት ለመፍጠር በሚያደርጉት ትግል ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እና ለቃሉ አደራ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን ምዕራባዊ ክፍል በምትገኝ ባሜንዳ ከተማ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ “የእያንዳንዱ ሰው ክብር የሚከበርበት እና መሠረታዊ መብቱ የተረጋገጠበት የሰላም እና የዕርቅ ሕይወት ሊኖረው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰሜን ምዕራብ ከተማ ባሜንዳ የተጓዙት ሐሙስ ሚያዝያ 8/2018 ዓ. ም. ሲሆን፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ  አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት ያለበት አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ- ሥርዓት ላይ ወደ 20,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተዋል።

የካሜሩን ሕዝብ የአገሪቱን ታሪክ ለመለወጥ፣ ሰላም እና እርቅ የሚነግስበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጥረት በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት ድጋፋቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የእያንዳንዱ ሰው ክብር የሚጠበቅበት፣ መሠረታዊ መብቶቹ የተረጋገጡበት የሰላም እና የእርቅ ሕይወት ተስፋን እንደሚጋሩ ተናግረው፥ “ነገር ግን በዚህች ውብ ምድር ውስጥ ሳያቋርጡ በሚደርሱ በርካታ ችግሮች ምክንያት ተስፋ ተደናቅፏል” ሲሉ አክለዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን-ባሜንዳ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን-ባሜንዳ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥   (@Vatican Media)

የበዓላት እና የአስደሳች እምነት ኃይል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የምዕመናኑን አስደሳች እና ሕያው የአምልኮ እና የጸሎት ሥርዓቶችን አድንቀው፥ “በእግዚአብሔር ላይ መተማመን ለእርሱ መገዛታችሁ፣ የማይናወጥ ተስፋችሁ ከእርሱ ፍቅር ጋር መዋሄዳችሁን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው” ሲሉ ገልጸው፥ “ልባችንን የሚሰብሩ ብዙ የሕይወት ሁኔታዎች በመኖራቸው ለሰላም እና ለፍትህ ያለን ተስፋ ብዙውን ጊዜ ይደናቀፋል” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በሃብት አስተዳደር ውስጥ የተቋማትን እና የመሠረተ ልማትን ዕድገት የሚያደናቅፍ፥ የምግብ ቀውስ እና ሙስናን ጨምሮ ሰፊ ድህነት በአገሪቱ ውስጥ መኖሩን ጠቁመው፥ በትምህርት እና በጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ላይ፣ በተለይም ወጣቶች እንዲሰደዱ የሚያደርጉ ሰፊ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

“ብዙውን ጊዜ በጥላቻ እና በዓመፅ ከሚቀሰቀሱ ውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ፥ በትርፍ ስም በአፍሪካ አህጉር ላይ እጃቸውን በመጫን የሚበዘብዙ ሰዎች ከውጭ የሚያደርሱት ጉዳት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባሜንዳ የመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባሜንዳ የመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት   (@Vatican Media)

የለውጥ ጊዜ አሁን ነው!

“ምዕመናን ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ፥ ዛሬ ነገ ሳይሉ የአገሪቱን እና የአህጉሪቱን ብዝሃነት እና ሃብት በማሰባሰብ ወደ ነበረበት የሚመልሱበት፣ በሰላም እና በእርቅ ላይ የተገነባ ማኅበረሰብን የሚመሠርቱበት ጊዜ ደርሷል” ሲሉ አሳስበዋል

እግዚአብሔር የመታደስ ኃይል ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቃለ ምዕዳናቸው፥ “ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ቢኖሩም የእግዚእብሔር ቃል አዳዲስ ዕድሎችን በመክፈት፣ ለውጥን እና ፈውስን በማምጣት አማኞችን ንቁ የለውጥ ተዋናዮች ያደርጋቸዋል” ብለዋል።

“እግዚአብሔር የመታደስ ኃይል ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ክፉን በመጋፈጥ መልካሙን የምንገነባ ደፋር ሰዎች ያደርገናል” ብለው፥ ሐዋርያት በምስክርነታቸው የህሊና ድምፅ፣ ትንቢት ተናጋሪዎች እና ክፋትን የሚያወግዙ ሆነዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከማንኛውም ሰብዓዊ ሥልጣን ይልቅ እግዚአብሔርን መታዘዝ አለብን” ሲሉ አጽንኦት በመስጠት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔርን የማይታዘዙት ከሆነ ውስጣዊ ነፃነታቸውን እንደገና በመፈተሽ ሰላምን እና ወንድማማችነትን እንዲያሳድጉ” በማለት አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በቃለ-ምዕዳናቸው ማጠቃለያም፥ “ለእግዚአብሔር የምንታዘዝ ከሆነ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል በድጋሚ ገልጸው፥ እምነትን ከቁሳዊ አካል ጋር በማዋሃድ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ዓላማዎች ከሚያራምዱ ጋር እንዳንቀላቀል አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ባሜንዳ ሲደርሱ ከሕዝቡ የተደረገላቸው አቀባበል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ባሜንዳ ሲደርሱ ከሕዝቡ የተደረገላቸው አቀባበል   (@Vatican Media)

 

17 Apr 2026, 16:53