ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማላቦ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማላቦ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ወቅት   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ “የአፍሪካ ጉብኝቴ ሕይወቴን እና አገልግሎቴን የሚያበለጽግ ነው” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአፍሪካ አኅጉር ሲያደረጉት የቆየውን የ11 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. በኢኳቶሪያን ጊኒ መዲና ማላቦ ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ አጠናቅቀዋል። “የአፍሪካ ጉብኝቴ ሕይወቴን እና አገልግሎቴን የሚያበለጽግ ነው” በማለት በማላቦ ስታዲየም ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ኢኳቶሪያል ጊኒን እና መላው አፍሪካን ተሰናብተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ሚያዝያ 15 በማላቦ ባደረጉት አጭር የስንብት ንግግር  በኢኳቶሪያል ጊኒ እና በሌሎች ሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያጠናቀቁ ሲሆን፥ በዚህም የ11 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተፈጽሟል።

ቅዱስነታቸው በማላቦ ስታዲየም ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ፍጻሜ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ወደ ቅድስት መንበራቸው የመመለሻ ጊዜ መድረሱን ገልጸው፥ ጉብኝታቸውን ለማካሄድ ላገኙት ዕድል እግዚአብሔርን አመስግነዋል።

ወንጌል ለ170 ዓመታት ሲሰበክ የቆየባት እና “በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ የሚጓዙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች” ያሏቸውን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ቀሳውስት እና ሰፊውን ምዕመናን በማመስገን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የኢኳቶሪያል ጊኒ ብርሃን እንደ ሆነ እንዲሁም ምዕመናኑ የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን እንደሆኑ ገልጸዋል።

ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የአገሪቱ ባለስልጣናት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአፍሪካ ያሳለፉትን ጊዜ በማስታወስ፥ በጉብኝታቸው ወቅት ባዩዋቸው ምስክርነቶች እና ልምዶች እጅግ በርካታ የእምነት፣ የተስፋ እና የልግስና ሃብትን ይዘው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

“ይህ ከፍተኛ ሃብት፥ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪ እንደመሆኔ መጠን ሕይወቴን እና ሐዋርያዊ አገልግሎቴን በእጅጉ የሚያበለጽጉ ታሪኮችን፣ ፊቶችን እና ምስክርነቶችን ያካትታል” ብለዋል።

አኅጉሪቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወት ያላትን ሚና ሲያስረዱ፥ “እንደ ክርስትና የመጀመሪያ ምዕተ ዓመታት ሁሉ ለምዕመናን ቅድስና እና ሚስዮናዊ ባህሪ አስተዋጽኦ እንድታደርግ ተጠርታለች” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የኢኳቶሪያል ጊኒ እና መላውን የአፍሪካ ሕዝብ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በመስጠት፥ በአኅጉሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እና አገራት በሙሉ እንክብካቤዋን በመማጸን ንግግራቸውን  ደምድመዋል።

 

24 Apr 2026, 11:31