ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “በዓለማችን የደረሰውን ረሃብ ለሌሎች በማሳወቅ ሁላችን እንተባበር” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አምስተኛ ቀን በካሜሩኗ ዱዋላ ውስጥ ከ120,000 ምዕመናን ጋር ሆነው መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የያውንዴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቀደሰ ጥረታቸውን እንዲያዳብሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካሜሩን ሰሜናዊ ምዕራብ ከተማ ባሜንዳ ውስጥ ዓርብ ሚያዝያ 9/2018 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር ሙስናን አውግዘው ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፥ የካሜሩን ሌላኛው አሳሳቢ ችግር ረሃብ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው ዱዋላ ከተማ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የተራቡትን እና ሸክም የከበዳቸውን ሰዎች በርኅራሄ ዓይን እንድንመለከታቸው በማበረታታት፥ “ምን ማድረግ ትችላላችሁ” ሲል እያንዳንዳችንን መጠየቁን ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ መስዋዕተ ቅዳሴው ሥፍራ ሲያመሩ
ቅዱስነታቸው ወደ መስዋዕተ ቅዳሴው ሥፍራ ሲያመሩ   (@Vatican Media)

"ለሁሉም የሚበቃ ምግብ አለ"

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ባለፈው የካቲት ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፥ ከካሜሩን ሕዝብ 40 በመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር እና 3.3 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ እንደሆነ ተናግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ፥አምስት ሺህ ሰዎችን የመመገብ ተአምር በተጻፈበት የቀኑ የወንጌል ንባብ ላይ በማሰላሰል፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ችግሩን እንዴት እንደሚፈቱ እንደጠየቃቸው በማስታወስ፥ ይህን ጥያቄ ዛሬ ለእያንዳንዳችን የሚያቀርብ ጥያቄ እንደሆነ ተናግረው፥ በመጨረሻም ሕዝቡ የሚመገበውን ማግኘት የሚችለው በማካፈል ምልክት እንደሆነ እና ይህም “ለሁሉም ሰው ቢሰጥ የሚበቃ ምግብ አለ” የሚለውን የሚያሳስብ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለመስዋዕተ ቅዳሴው ለተሰበሰቡት ወደ 120,000 ለሚደርሱ ምዕመናን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ማንም ሰው ሊራብ አይገባም” ሲሉ ተናግረው፥ “ምግብ በሚነጥቅ እጅ ሳይሆን በሚሰጥ እጅ ከተወሰደ ለሁሉም የሚበቃ አለ” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ
ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)

የተቀደሰ ጥረት

ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በኋላ የማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲን ለመጎብኘት ወደ ካሜሩን መዲና ያውንዴ ከመመለሳቸው በፊት ወደ አንድ የካቶሊክ ሆስፒታል የግል ጉብኝት በማድረግ፥ ግለኝነት እና ግብዝነት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለወዳጅነት፣ ለትብብር እና ውስጣዊ አስተንትኖ ልዩ ቦታ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ አንደኛው አካል፥ ነፃ የሆነ ኅሊናን መፍጠር እና የተቀደሰ ጥረት ማድረግ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ወጣቶች የተቀደሰ ጥረታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተው፥ በተጨማሪም በንግግራቸው በተደጋጋሚ እንደገለጹት፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” በተመለከተ የተነሳውን ርዕሥ ተመልከተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “ቴክኖሎጂ አእምሯችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀረጸ እና እየገባ ነው” ብለው፥ ይህ ለውጥ ግለሰቦች በሰው ሠራሽ ዘመን ውስጥ በሥራ መስክ ያለውን ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ቢስነት፣ አድልዎች እና የሥልጣን ዓይነቶችን እንዲረዱ የሚረዳ በመሆኑ ሥነ-ሰው ጥናትን የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከዩኒቨርሲቲው ዲን ጋር ሲገናኙ
ቅዱስነታቸው ከዩኒቨርሲቲው ዲን ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ከገዳማውያት የበላይ አለቆች ጋር መገናኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወዳረፉበት የሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ከተመለሱ በኋላ በካሜሩን ውስጥ ከሚገኙ ከ250 በላይ የገዳማውያት እና ገዳማውያት ተቋማት እና ማኅበራት ዘጠኝ ተወካዮች ጋር ተገናኝተዋል።

እንደ ቅድስት መንበር መግለጫ መሠረት፥ የገዳማውያን እና ገዳማውያት የበላይ አለቆቹ በአገሪቱ ውስጥ የሚያበረክቱት የበጎ አድራጎት ጥረት፥ በተለይም ከወጣቶች፣ ከተፈናቃዮች፣ የዓመፅ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ጋር የሚያደርጉትን ሥራ በማስመልከት ለቅዱስነታቸው ገለጻ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቦታው ለተገኙት ባደረጉት ንግግር፥ የምንኩስና ሕይወት ሥር ነቀል ድፍረትን እንደሚጠይቅ እና ይህም በዓለም ላይ ያሉትን እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት እና ተስፋ ለሚያስፈልጋቸው የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማድረስ ያግዛል” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዷነታቸው ከገዳማውያን እና ገዳማውያት የበላይ አለቆቹ ጋር
ቅዷነታቸው ከገዳማውያን እና ገዳማውያት የበላይ አለቆቹ ጋር   (@Vatican Media)

 

18 Apr 2026, 16:24