ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በርካታ ድብቅ የበጎ ሥራ ምልክቶች መኖራቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በዋና ከተማ ማላቦ ውስጥ የሚገኘውን የዣን ፒየር ኦሊ የአእምሮ ሕክምና ሆስፒታልን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው የሆስፒታሉ ክርስቲያናዊ ተልዕኮን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ “ሆስፒታሉ ማንኛውም ሰው የሚታከምበት እና በአቅመ ደካማነቱ የሚከበርበት አዲስ ፍቅር የሚገለጥበት ቦታ ነው” ሲሉ ገለጸው፥ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሆስፒታል ሲጎበኙ የሚሰማቸውን ስሜት ያካፈሉት ቅዱስነታቸው፥ በአንድ በኩል ለታካሚዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ሐዘን ተናግረው፥ እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሸክም እና በግልጽ የሚታዩ ቁስሎች እንዳሉባቸው ገልጸው፥ በሌሎች ጊዜያት ማንም የማያያቸው ነገር ግን ራሳቸው ብቻ በልባቸው እና በሕይወታቸው ውስጥ የሚሸከሟቸው ቁስሎች እንዳሏቸው በመናገር ሆኖም የሰውን ሕይወት ለማገልገል የሚደረገውን ጥረት በማድነቅ እንደሚጽናኑ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በማላቦ ሆስፒታል መገኘት ለእኔ ምንም የተለየ ባይሆንም ነገር ግን የደስታን አሸናፊነት ያየሁበት እና ይህ ደስታ የሚመጣው በእግዚአብሔር ስም አንድ ላይ በመሰባሰብ እና ጤንነታቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች እንክብካቤን በማድረግ ነው” ብለዋል።

የዛሬው የፍቅር ምልክት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሆስፒታሉ ውስጥ በተሰጡት ምስክርነቶች እጅግ እንደተደሰቱ ተናግረው፥ ይህም የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ቤቺር ቤን ሃጅ አሊ ባቀረቡት ምስክርነት ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል። ዳይሬክተሩ፥ “በእውነት ታላቅ ማኅበረሰብ ድክመቶቹን የሚደብቅ ሳይሆን በፍቅር የሚይዝ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። “ይህ ፍቅር በክርስትና ላይ የተመሠረተ የአዲስ ፍቅር መርህ ስለሆነ እውነት ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣው በአካል ጉዳተኝነት በመገለል ችግር ለሚሰቃዩ ሰዎች ሙሉ ክብራቸውን ለመዋጀት እና ለመመለስ ነው” ብለው፥ “ሆኖም ይህን ለማድረግ የእኛ ትብብር በግልም ሆነ በማኅበር ደረጃ ያስፈልገዋል” ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች በሙሉ ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን በቃላትም ሆነ በድርጊት እንዲወዱ የሚጠራቸው ለዚህ እንደሆነ በመግለጽ፥ “እንደ ዣን ፒየር ኦሊ የሥነ-ልቦና ሆስፒታል ያለ ​​ተቋም በእግዚአብሔር ዕርዳታ እና በሁሉም ሰው ቁርጠኝነት የዚህ ፍቅር ማደግ ምልክት ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

እንደማንነታችን መውደድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሆስፒታሉ ውስጥ ካሉት ታካሚዎች መካከል አንዱ የተናገረውን በመጥቀስ፥ “ቅዱስነታቸው እኛን እንደማንነታችን ይወዱናል” በማለት ላቀረበው ምስክርነት አመስግነው፥ እግዚአብሔርም እያንዳንዱን ሰው የሚወደው በዚህ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። “እግዚአብሔር እኛን ሊፈውሰን እንጂ ሁልጊዜ እንድንታመም አይፈልግም ብለው፥ ወንጌል ይህንን ከአንድ ጊዜ በላይ እንደሚናገር ገልጸዋል።

“በተለይም ክርስቲያናዊ ተልዕኮ ያለው ሆስፒታል ማንኛውም ሰው እንደ ማንነቱ እና እንደ ደካማነቱ የሚከበርበት ቦታ ነው” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ቅዱስነትቸው፥ ይህ እይታ ካለ ሕሙማንን መርዳት ይቻላል” ብለው፥ ይህ መንፈሳዊ ስሜት ለዚህ ሥራ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሙሉ በሙሉ ሊያነብ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በታርሲሲዮ ለተጻፈው ግጥም ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፥ በየቀኑ ስንት የተደበቁ ግጥሞች እንደሚጻፉ፥ በቃላት ሳይሆን በርኅራሄ፣ በደግነት እና በእርስ በርስ ግንኙነት የሚገለጹ በርካታ ትናንሽ ምልክቶች እንዳሉ ተናግረው፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መሐሪ ልብ የሚያጽናናውን ይህን ግጥም ሙሉ በሙሉ ሊያነበው የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሆስፒታሉ ውስጥ ላሉት ታካሚዎች በሙሉ በተለይም በጠና ለታመሙት እና ብቻቸውን ለሆኑት ያላቸውን ቅርበት ከገለጹላቸው በኋላ በሆስፒታሉ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዣን ፒየር ኦሊ የአእምሮ ሕክምና ሆስፒታል ያደረጉት ጎብኝት
22 Apr 2026, 16:35