ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ወጣቶች በድፍረት እና በደስታ ስለ ኢየሱስ እንዲመሰክሩ አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ በባታ ስታዲየም ለተሰበሰቡት ወጣቶች እና ቤተሰቦች መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት እና በደስታ እንዲመሰክሩ በማሳሰብ ከወጣቶቹ በቀረቡት ምስክርነቶች ላይ በማስተንተን ምክራቸውን ለግሠዋል። በሕይወት ውስጥ ጥረት እና ዲሲፕሊን ስላለው ዋጋ፣ ሴቶችን በሥራ መስክ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች፣ ራስን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ከመስጠት ስለሚገኝ ደስታ እና የትዳር ጓደኛን የማግኘት እና ወላጅ የመሆን አስደሳች ተልዕኮን በማስመልከት መልዕክቶች አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ30,000 በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችል የባታ ስታዲየም በሙዚቃ ዝግጅቶች፣ በልዩ ልዩ ቀለማት፣ በፈገግታ እና በደስታ ተሞልቷል። ቅዱስነታቸው ወደ ስታዲየሙ ሲደርሱ በርካታ ወጣቶች፣ ቤተሰቦች፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች፣ ካህናት እና የባታ ከተማ ምዕመናን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ለተደረገላቸው አቀባበል ባሰሙት የምስጋና ንግግር፥ “ኢኳቶሪያል ጊኒ ወደ ተስፋ በምታደርገው ጉዞ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃኗ ነው” የሚለውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ጭብጥ በማስታወስ፥ “በባታ ያለው ደማቅ ብርሃን በዓይኖቻችሁ፣ በፊቶቻችሁ፣ በፈገግታችሁ እና በዝማሬያችሁ በኩል ያበራል” ብለው፥ እነዚህ በሙሉ ክርስቶስ የሕይወታችሁ ደስታ፣ ትርጉም፣ ተነሳሽነት እና ውበት መሆኑን ይመሰክራሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በባታ ስታዲየም ከወጣቶች ጋር በተገናኙበት ወቅት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በባታ ስታዲየም ከወጣቶች ጋር በተገናኙበት ወቅት   (@Vatican Media)

ጥረትን የሚያበረታታ ባሕል

ከባታ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ብጹዕ አቡነ ሚጌል አንጌል ንጌማ ከተደረገላቸው አቀባበል ቀጥሎ ንግግር ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለአስተንትኖ መልዕክታቸው መሪ የሆኑ ተከታታይ ምስክርነቶችን ካዳመጡ በኋላ፥ ወጣት አሌሲያ በሥራ መስክ ሴቶችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማስመልከት ለሰጠችው የመጀመሪያ ምስክርነት ምላሽ ሰጥተዋል።

“በዕለት ተዕለት ተግባር ለራሳችሁ ታማኝ መሆን፤ ለቤተሰብ እና ለኅብረተሰብ ጥቅም ሲባል የምትችሉትን አስተዋጽኦ ማበርከት፤ ወጣቶች ስኬትን በቀላል መንገድ ከመፈለግ ይልቅ በጥረት፣ በዲሲፕሊን እና ጠንክሮ በመሥራት ባሕል ማግኘት አለባቸው። ኢኳቶሪያል ጊኒ ለዚህ ሁሉ ዋጋ የምትሰጥ አገር ናት። ክርስቲያን መሆን ማለት በመስዋዕተ ቅዳሴ መሳተፍ ብቻ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

አቡነ ሚጌል አንጌል ንጌማ ለቀዱነታቸው ሰላምታ ሲያቀርቡ
አቡነ ሚጌል አንጌል ንጌማ ለቀዱነታቸው ሰላምታ ሲያቀርቡ   (@Vatican Media)

እግዚአብሔርን በመከተል መቶ እጥፍ ታገኛላችሁ!

የዘርዓ ክኅነት ተማሪ ፍራንችስኮስ ማርቲን የግል ጥሪውን በማስመልከት፥ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር በመስጠት የሚገኝ ደስታን ማየት ብቻ ሳይሆን ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠቱ በፊት የተጋፈጣቸውን ተግዳሮቶች በተረጋጋ መንፈስ በደስታ እንደተቀበላቸው ገልጿል።

ቅዱስነታቸው ይህን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሕይወት የደስታ ሕይወት ነው። ነገር ግን በየቀኑ በጸሎት፣ በቅዱሳት ምስጢራት እና እግዚአብሔር በመንገዳችን ላይ ከሚያስቀምጣቸው ወንድሞች እና እህቶች ጋር ሆነን በምናሳልፋቸው ጊዜ መታደስ አለበት። በልብ አንድነት እና ለተቸገሩ ሰዎች በምናበረክታቸው የበጎ አድራጎት ተዓምራት ያለማቋረጥ ይታደሳሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የክኅነትን እና የምንኩስና ሕይወትን እንዲሁም የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት አገልግሎትን በልዩ መንገድ እንድትከተሉት እየጠራችሁ መሆኑ ከተሰማችሁ የእርሱን ፈለግ ለመከተል አትፍሩ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባታ ስታዲየም ለተገኙት የማበረታቻ መልዕክት ሲያስተላልፉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባታ ስታዲየም ለተገኙት የማበረታቻ መልዕክት ሲያስተላልፉ   (@Vatican Media)

ቤተሰብ ለሰው ልጅ እና ለክርስቲያናዊ ዕድገት ለም መሬት ነው!

በምስክርነት ዝግጅት ላይ የተገኙት ቤተሰቦች፥ ፑሪፊካሲዮን እና ያይሜ አንቶኒዮ ወላጆቻቸው በእግዚአብሔር በመታመን በአንድነት ማደግ እንደቻሉ፣ ሕይወትን ከአደጋ በመጠበቅ እና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ የተሰጣቸውን የሕይወት ስጦታን በደስታ መቀበል መቻላቸውን ተናግረዋል።

ይህን ምስክርነት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “ባለትዳሮች እና ወላጆች መሆን አስደሳች ተልዕኮ ነው። በየቀኑ ለመኖር የተገባ ቃል ኪዳን ነው። በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ በሕይወት ተአምር ለራሳችሁ እና ለልጆቻችሁ ደስታን በመገንባት ከእግዚአብሔር ጋር በመተሳሰር እርስ በርሳችሁ ያለማቋረጥ ትገናኛላችሁ። ይህን ጥሪ በነፃነት የሚያድግ እውነተኛ የፍቅር ጉዞ አድርጋችሁ ለመቀበል ተዘጋጁ። እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይተዋችሁ ከማወቅ የተገኘውን የተስፋ ጉዞ እና ዘወትር የሌሎችን መልካም እና ደስታ የምትፈልጉበት የቅድስና ጉዞ አድርጋችሁ ለመቀበል ተዘጋጁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባለትዳሮችን ለጋብቻ ምስክርነታቸው ሲያመሰግኑ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባለትዳሮችን ለጋብቻ ምስክርነታቸው ሲያመሰግኑ   (@Vatican Media)

ለተወለደ እና ለሚያድግ ሕይወት ክብር መስጠት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፥ ወላጆቹ የተለያዩት የ13 ዓመት አዳግ ልጅ ለሰጠው ቅን እና ደፋር ምስክርነት ምስጋናቸውን በማቅረብ፥ “ምስክርነቱ ለሚወለድ እና ለሚያድግ ሕይወት የተሻለ ዓለምን ለመገንባት የሚያበረታታ ሊሆን ይገባል” ብለው፥ “በሕይወት የመኖር ዋጋዋን ለመቀነስ የሚፈልጉ መስዋዕትነቶች፣ ፍርዶች፣ ጭፍን ጥላቻዎች እና የተዛቡ አመለካከቶች ቢኖሩም ሕይወትን ለማዳበር፣ ለመኖር እና ለመመስከር ተጠርተናል” ብለዋል።

“ቪክቶር አንቶኒዮ፥ ሕይወትን በደስታ ለመቀበል ፍቅር፣ ቁርጠኝነት እና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጉ አስታውሶናል። እነዚህ በአዳጊ ልጅ የተነገሩ ቃላት፣ ቤተሰብን እና በውስጡ የተማርናቸውን እሴቶች የመጠበቅ እና የመንከባከብ አስፈላጊነት በቁም ነገር እንድናስብ ሊያደርጉን ይገባል” ብለዋል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ወጣቶች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት
የኢኳቶሪያል ጊኒ ወጣቶች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት   (@Vatican Media)

ኢየሱስ ለሰጠን ፍቅር ምስክሮች እንሁን!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲሰማው እና የተዘነጋ መስሎ እንዳይሰማው ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ “ለዚህ አገልግሎት የቆሙ ተቋማት ዓለምን በመለወጥ ረገድ እንዲሳተፉ፤ የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ የአፍሪካ እና የመላው ዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንን ወደ ተስፋ እንዲመራን በኅብረት ሆነን በጠንካራ ውሳኔ እና መልካም ቁርጠኝነት ማደግ አለብን” ብለዋል።

“ውድ ወጣቶች፣ ወላጆች እና በዚህ ቦታ የተገኛችሁት በሙሉ፥ በፍቅር እንነሳሳ! ኢየሱስ ለሰጠን እና ላስተማረን ፍቅር ምስክሮች እንሁን! በየቀኑ ፍቅር ውብ መሆኑን እናሳይ! በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ ትልቅ ደስታ የሚመጣው በተለይም የእኛ ድጋፍ እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች መድረስ እንዳለብን በማወቅ እና ለዚህ አገልግሎት ራሳችንን ከመስጠት መሆኑን እንመስክር! በቤታችን ውስጥ የሚንከባከበው እና በእምነት ላይ የተመሠረተ የበጎ አድራጎት ብርሃን ዓለምን በእውነት ሊለውጠው ይችላል” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ አርቲስቶች ባሕላዊ ውዝዋዜያቸውን ሲያቀርቡ
የኢኳቶሪያል ጊኒ አርቲስቶች ባሕላዊ ውዝዋዜያቸውን ሲያቀርቡ   (@Vatican Media)
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባታ ስታዲየም ከወጣቶች እና ቤተሰቦች ጋር በተገናኙበት ወቅት

 

 

23 Apr 2026, 13:57