ር.ሊ.ጳ ሊዮ ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም ሰው እንድታገኝና ሰላምን እንድታስፋፉ ምዕመናን እገዛ ያደርጋሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በዕለቱ የተነበበው የእግዚአብሔር ቃል
እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ እንድትመላለሱ እለምናችኋለሁ፤ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት (ኤፌ 4፡1. 4-5)።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አርፈዳችሁ!
በላቲን ቋንቋ "Lumen gentium (የአሕዛብ ብርሃን) በተሰኘው የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ህግጋት ሰነድ ውስጥ እንደቀረበው ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለንን የማሰላሰል መንገዳችንን እንቀጥል። ዛሬ ስለ ምዕመናን የሚናገረውን አራተኛውን ምዕራፍ እንመለከታለን። የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ መናገር ይወዱ የነበረውን ሁላችንም እናስታውስ፡- “ምዕመናን፣ በቀላል አነጋገር፣ በቁጥር አብላጫዎቹ የእግዚአብሔር ሕዝብ ናቸው። አናሳዎቹ - የተሾሙ አገልጋዮች - በአገልግሎታቸው ላይ ናቸው” (ሐዋርያዊ ምክር Evangelii gaudium፣ 102)።
ይህ የሰነዱ ክፍል፣ በዘመናት ውስጥ እንደ ቀሳውስት ወይም የተቀደሰ ሕይወት አካል ያልሆኑ ሰዎች ተብለው ከተገለጹ በኋላ፣ የምዕመናኑን ተፈጥሮ እና ተልእኮ በአዎንታዊ መልኩ ለማብራራት ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት፣ የክርስትናን ሁኔታ ታላቅነት የሚገልጽ በጣም የሚያምር ክፍል እንደገና ለማብራራት እፈልጋለሁ፡- “ስለዚህ፣ የተመረጡት የእግዚአብሔር ሕዝብ አንድ ናቸው፤ ‘አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት’ (ኤፌ 4፡5)፤ በክርስቶስ ከተወለዱበት ልደት ጀምሮ እንደ አባላት የጋራ ክብርን የሚጋሩ፣ ተመሳሳይ የልጅነት ጸጋ እና ተመሳሳይ የፍጽምና ጥሪ ያላቸው፤ የጋራ አንድ መዳን፣ አንድ ተስፋ እና አንድ ያልተከፋፈለ ፍቅር ያላቸው” (ኤልጂ፣ 32) ሲል ይገልጻቸዋል።
ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ ሰዎች ሁሉ እኩልነት
ከአገልግሎት ወይም ከሕይወት ሁኔታ ልዩነት በፊት፣ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ምስጢረ ጥምቀት የተጠመቁትን ሁሉ እኩልነት ያረጋግጣል። ሃይማኖታዊ ህግጋቱ (ዶግማ) ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ ምዕራፍ አስቀድሞ ያረጋገጠውን እንድንረሳ አይፈልግም፣ ማለትም የመሲሐዊው ሕዝብ ሁኔታ የእግዚአብሔር ልጆች ክብር እና ነፃነት ነው።
በተፈጥሮ ስጦታው በጨመረ ቁጥር፣ ቁርጠኝነትም ይጨምራል። በዚህ ምክንያት፣ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከክብር ጋር፣ በቤተክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ የምእመናንን ተልእኮ ያጎላል። ነገር ግን ይህ ተልዕኮ በምን ላይ የተመሠረተ ነው? በምን ላይ ነው አካታች የምያደርገው? ጉባኤው የሰጠው የምዕመናን መግለጫ ራሱ እንዲህ ይነግረናል፡- “ምዕመናን የሚለው ቃል እዚህ ላይ ሁሉም ምዕመናን ማለት እንደሆነ ተረድቷል… [በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል የሆኑ እና በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የተዋቀሩ]፤ በራሳቸው መንገድ በክርስቶስ የክህነት፣ የትንቢት እና የንጉሣዊ ተግባራት ተካፋዮች ሆነዋል፤ በቤተክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ ያሉትን የክርስቲያን ሕዝቦች ሁሉ ተልዕኮ በራሳቸው ድርሻ ያከናውናሉ” (LG፣ 31)።
የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅርጽ የሌለው መጠነ ቁስ አይደለም
ስለዚህ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ፈጽሞ ቅርጽ የሌለው መጠነ ቁስ አካል አይደለም፣ ነገር ግን የክርስቶስ አካል ወይም ቅዱስ አውጉስጢኖስ እንዳለው በላቲን ቋንቋ " Christus totus" (መላው ክርስቶስ)፤ በክርስቶስ ክህነት ውስጥ በሚሳተፉ ሁለት ዓይነት ተሳትፎዎች መካከል ባለው ፍሬያማ ግንኙነት በሕይወት ባለው አካል የተዋቀረ ማህበረሰብ ነው፣ የምዕመናን የጋራ ክህነት እና የአገልጋይ ክህነት (LG፣ 10) ውስጥ ማለት ነው። በምስጢረ ጥምቀት ምክንያት፣ ምዕመናን በክርስቶስ ክህነት ውስጥ ይሳተፋሉ። በእርግጥም፣ “ልዑሉና ዘላለማዊው ካህን ክርስቶስ ኢየሱስ፣ በምእመናኑ በኩል ምስክርነቱንና አገልግሎቱን ለመቀጠል ስለሚፈልግ፣ በዚህ መንፈስ ሕያው ያደርጋቸዋል እንዲሁም ወደ መልካምና ፍጹም ሥራ ሁሉ የበለጠ ያበረታታቸዋል” (LG፣ 34)።
ምእመናን የክርስቶስን ጥሪ እንደገና ያስተጋባሉ
በዚህ ረገድ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እና በላቲን ቋንቋ " Christifideles laici" (ክርስቲያን ምዕመናን) የተሰኘውን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸውን (እ.አ.አ ታህሳስ 30/1988 ዓ.ም) እንዴት ማስታወስ አንችልም? በዚህ ውስጥ፣ “ጉባኤው፣ ባለጸጋው መሠረተ ትምህርት፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ የእረኝነት እንክብካቤ ያለው፣ ስለ ምእመናን ተፈጥሮ፣ ክብር፣ መንፈሳዊነት፣ ተልዕኮ እና ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ጽፏል። እናም የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አባቶች፣ የክርስቶስን ጥሪ እንደገና በማስተጋባት፣ ምእመናንን፣ ሴቶችንም ወንዶችንም በወይን እርሻው ውስጥ እንዲሠሩ ጠርተዋል” (ቁጥር 2) ይለናል። በዚህ መንገድ፣ የተከበሩት የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የምእመናኑን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደገና አስጀምሯል፣ ምክር ቤቱም በኋላ ላይ ስለምንነጋገርበት የተወሰነ ሰነድ ሰጥውታል።
ቤተክርስቲያኗ ልጆቿ ወንጌልን በሚናገሩበትና በሚመሰክሩበት ቦታ ሁሉ ትገኛለች
ሰፊው የሐዋርያቱ መስክ በቤተክርስቲያን ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ወደ ዓለምም ይዘልቃል። በእርግጥም፣ ቤተክርስቲያኗ ልጆቿ ወንጌልን በሚናገሩበትና በሚመሰክሩበት ቦታ ሁሉ ትገኛለች፤ በሥራ ቦታ፣ በሲቪል ማህበረሰብ እና በሁሉም የሰው ልጅ ግንኙነቶች፣ በምርጫዎቻቸው፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሚፈጸመውን ፍትህና ሰላም የሚተነብይውን የክርስትና ሕይወት ውበት የሚያሳዩበት ቦታ ሁሉ። ዓለም “በክርስቶስ መንፈስ መሞላት እና ዓላማውን በፍትህ፣ በበጎ አድራጎትና በሰላም የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ መፈጸም” አለበት (LG፣ 36)። ይህ የሚቻለው በምዕመናን አስተዋጾ፣ አገልግሎት እና ምስክርነት ብቻ ነው!
የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ እኛ የተናገሩት “ወጣት” ቤተክርስቲያን እንድትሆን የቀረበ ግብዣ ነው፥ በታሪክ ውስጥ የተቀረጸች፣ ሁልጊዜም ለተልዕኮ ክፍት የሆነች ቤተክርስቲያን፣ ሁላችንም ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት፣ የወንጌል ሐዋርያት፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስክሮች፣ የክርስቶስን ደስታ ተሸካሚዎች እንድንሆን የተጠራች ወጣት ቤተ ክርስቲያን!
ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ለማክበር እየተዘጋጀን ያለነው ፋሲካ እንደ ማርያም መግደላዊት፣ እንደ ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ከሙታን የተነሣው የኢየሱስ ምስክር የመሆንን ጸጋ በውስጣችን ያድስልን!
