ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “‘ሌቦች’ ደስታችሁን እና ሰላማችሁን እንዲነጥቋችሁ አትፍቀዱ” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሚያዝያ 18 /2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት አድርሰዋል። ከሳምንታዊው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመሩበት ወቅት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ምእመናን በእግዚአብሔር እንዲታመኑ በማሳሰብ፥ “እኛን በማታለል ደስታችንን ለማጥፋት በሚጥሩ ‘ሌቦች’ እንዳትታለሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አርፍዳችኋል! መልካም ዕለተ ሰንበትን እመኝላችኋለሁ!  በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት የተነበበው የዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 10:1-10)፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ከእረኛ እና ከበጎች በረት መግቢያ ጋር ማነጻጸሩን ይነግረናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በእረኛው እና በሌባው መካከል ያለውን ንፅፅር ያሳያል። በእርግጥም ‘በበሩ በኩል ወደ በጎች በረት የማይገባ ነገር ግን በሌላ መንገድ የሚመጣ ሁሉ ሌባና ወንበዴ ነው’ ይላል (ዮሐ. 10:1)። ይህን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ሲፈልግ፥ ‘ሌባ ሊሰርቅ፣ ሊገድል እና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል። እኔ ግን የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ’ (ዮሐ. 10:10)። ልዩነቱ ግልጽ ነው፤ እረኛው ከበጎቹ ጋር ልዩ ትስስር ስላለው በበጎች በረት በር መግባት መውጣት ይችላል። ነገር ግን አንድ ሰው በሌላ በኩል አጥሩን ዘልሎ የሚገባ ከሆነ ይህ ሰው በጎችን ሊሰርቅ የፈለገ ሌባ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌው እየነገረን ያለው በወዳጃዊ ግንኙነት ነው፤ ከእኛ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም እርሱ የእኛን ማንነት ያውቃል፣ በስማችን ይጠራናል፣ ይመራናልም። ልክ እረኛው ለበጎቹ እንደሚያደርገው ሁሉ ስንጠፋ ይፈልግናል፤ ስንታመም ቁስላችንን ይጠግንልናል (ሕዝ 34:16)። ኢየሱስ ወደ እኛ የሚመጣው እንደ ሌባ ሕይወታችንን እና ነፃነታችንን ለመንጠቅ ሳይሆን በጽድቅ ጎዳናዎች ላይ ሊመራን ነው። ሕሊናችንን ለማጥመድ ወይም ሊያታልለን ሳይሆን ነገር ግን በጥበብ ብርሃኑ ሊያበራልን ነው። ምድራዊ ደስታችንን ሊያበላሽብን ሳይሆን ወደተሟላ እና ዘላቂ ወደ ሆነው ደስታ ሊያደርሰን ነው። በእርሱ የሚታመኑትን የሚያስፈራቸው ነገር የለም። ምክንያቱም እርሱ የሚመጣው ሕይወትን አተርፍርፎ ሊሰጣቸው ነው (ዮሐ. 10:10)።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በዚህ ላይ እንድናስብበት ተጋብዘናል። ወደ ልባችን እና ወደ ሕይወታችን ስለሚያስገባው በር እንድናስብ እና በተለይም እንድንጠነቀቅ ተጋብዘናል። ምክንያቱም ወደ ልባችን ውስጥ የሚገባው ደስታችንን ሊጨምር ወይም እንደ ሌባ ሊሰርቀን ይችላል። ‘ሌቦች’ በብዙ መንገድ ሊመጡ ይችላሉ።

ሰዎች መልካቸው ምንም ይምሰል ምን ነፃነታችንን የሚገፍፉ ወይም ክብራችንን የማይጠብቁ፣ ሕይወትን እና ሌሎች ሰዎችን በተረጋጋ መንፈስ እንዳናይ የሚከለክሉ እምነቶችን እና አድልዎችን የሚያስተምሩ፣ አሉታዊ ምርጫዎችን እንድናደርግ የሚገፋፉ የተሳሳቱ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ፤ ወይም ውስጣችን ባዶ እንዲሆን የሚያደርጉን እና ከአቅማችን በላይ እንድንኖር የሚገፋፉን ሊሆኑ ይችላሉ። የምድርን ሃብት የሚዘርፉ፣ የንጹሃን ደም የጠማው ጦርነትን በማካሄድ ወይም በማንኛውም መንገድ ክፋትን በማቀጣጠል የእያንዳንዳችን ሰላማዊ እና የተረጋጋ የወደፊት ዕድልን የሚሰርቁ ‘ሌቦች’ መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም።

ሕይወታችንን ማን እንዲመራው እንፈልጋለን? ወደ መንጋዎቻችን ሊገቡ የሞከሩ ‘ሌቦች’ የትኞቹ ናቸው? ተሳክቶላቸዋል ወይስ አባርረናቸዋል? ብለን መጠየቅ አለብን።

ቅዱስ ወንጌል ዛሬ በእግዚአብሔር እንድንታመን ይጋብዘናል። እግዚአብሔር ወደ እኛ የሚመጣው ሕይወትን አትረፍርፎ ሊሰጥን እንጂ ሊወስድብን አይደለም። እርሱ ቸር እረኛ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር ከእኛ ጋር እየተጓዘች  ስለ እኛ እና ስለ ዓለም ሁሉ ታማልደን።”

27 Apr 2026, 16:17