ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ "ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንጎላ ቤተ ክርስቲያን ጋር ዘወትር አብሮ ይጓዛል" ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንጎላ መዲና ሉዋናዳ አቅራቢያ በኪላምባ የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለምዕመናኑ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ከሞት የተነሳው እና ሕያው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከአንጎላውያን ጋር እንደሆነ ተናግረው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ መከራዎችን ባሳለፈው የአንጎላ ሕዝብ መካከል እንደሚገኝ ምዕመምናኑ የሚያምኑ ከሆነ የተባረከ እና ሰላማዊ ሕይወት ሊኖራቸው እንደሚችል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ታማኝ እንድትሆኑ፣ በሐዋርያዊ እረኞቻችሁ ላይ እምነት እንዲኖራችሁ፣ በተለየ መንገድ ራሱን በቃሉ እና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በሚገልጽ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ትኩረት አድርጉ” ሲሉ አሳስበው፥ በመካከላቸው ተገኝተው እግዚአብሔርን ለስጦታው እንዲሁም በደስታ ለተሞላ አቀባበላቸው በምስጋና ልብ መስዋዕተ ቅዳሴውን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

አንጎላ ብትቆስልም ውብ አገር ናት

በላቲን ሥርዓት መሠረት በብርሃነ ትንሳኤው ሦስተኛ እሁድ ከቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ወደ ኤማውስ ይጓዙ የነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርትን አስታውሰው፥ እምነታቸውን የጣሉበት እና የተከተሉት ኢየሱስ በመሞቱ ምክንያት ልባቸው በማዘኑ ተስፋ የቆረጡ ቢሆንም ኢየሱስ ከጎናቸው ሆኖ እንደሚጓዝ በተገነዘቡ ጊዜ ሁሉ ነገር መለወጡን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኪላምባ መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ጊዜ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኪላምባ መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ጊዜ   (@Vatican Media)

ቅዱስነታቸው በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ በማስተንተን እንደተነገሩት፥ አንጎላ ከዚህ ቀደም ባጋጠማት ልዩ ልዩ ችግሮች የቆሰለች ብትሆንም፥ ተስፋን፣ ሰላምን እና ወንድማማችነትን የምትራብ እና የምትጠማት አገር ናት” ሲሉ አስረድተዋል።

ተስፋ የቆረጡ ሁለት ደቀ መዛሙርት በኢየሱስ ላይ የደረሰውን በማስመልከት ያደረጉትን ውይይት በመጥቀስ፥ አንጎላ ረጅም የእርስ በርስ ጦርነት የተካሄደባት፣ በውስጧ ጠላትነት እና መለያየት የተፈጠረባት፣ በጦርነት በወደሙ በርካታ ንብረቶች እና ባደረሰው ድህነት ከፍተኛ ስቃይ ያየች አገር መሆኗን አስታውሰዋል።

አንድ ሰው ይህ ሁሉ ሲገጥመው እና ለረጅም ጊዜ በመከራ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ከአደጋው የሚወጣበትን መንገድ ካላወቀ እንደ ኤማውስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ዕድል ሊያጋጥመው እንደሚችል አስረድተዋል።

ተስፋ የቆረጡ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት በወዳጅነት የቀረባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የአንጎላ ሕዝብ ታሪኩን ከስቃይ ባሻገር እንዲመለከተው፥ ወደፊት ለመጓዝ በሚያደርገው ጥረት ብቻውን እንዳልሆነ እና በእግዚአብሔር ፍቅር ተሳስሮ በኅብረት የሚኖርበት የወደፊት ጊዜ እንደሚጠብው መእመናኑን አስታውሰዋል።

እግዚአብሔር ጸጋውን እየሰጠን ከጎናችን ይጓዛል

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! የጌታ ወንጌል ዛሬም ለእኛ የሚነግረን ይህ ነው” ሲሉ በአፅንዖት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ነው! ከሞት ተነስቷል! በመከራ እና በስቃይ መንገድ አብሮን ይጓዛል” በማለት አስረድተው፥ “የእርሱን ሥራ የምናይበት ዓይን እና ጉዞን እንደገና በመጀመር ሕይወትን የምንገነባበት ጸጋ ይሰጠናል” ብለዋል።

“ከፊት ለፊታችን የተዘረጋው መንገድ ይህ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “እናንተ ውድ አንጎላውያን ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የኅብረት ጉዞአችሁን እንደገና ለመጀመር በአንድ በኩል እግዚአብሔር አብሮአችሁ እንደሚጓዝ እና እንደሚራራላችሁ እርግጠኞች መሆን፥ በሌላ በኩል ከእናንተ የሚፈልገውን ቁርጠኝነት እንድታሳዩት” በማለት አሳስበው፥ “ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ወዳጅነት የምንለማመደው ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ነው” ሲሉ  አስረድተዋል።

ለሁለቱ ደቀ መዛሙርት እንዳደረገው ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚንገናኘው ልባችን በውስጣችን እንዲቃጠል በሚያደርግ ጸሎት እና ቃሉን በመስማት እንደሆነ ተናግረው፥ ከሁሉም በላይ በመስዋዕተ ቅዳሴ መሆኑን አስረድተዋል።

“ለባሕላዊ ሃይማኖቶች ዘወትር ትኩረት መስጠት አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የባሕላችሁ መሠረት ቢሆኑም በመንፈሳዊ ጉዞ ላይ የማይጠቅሙ እና እምነትን ግራ የሚያጋቡ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ለምታስተምራችሁ ነገር ታማኞች ሁኑ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በሐዋርያዊ እረኞቻችሁ ላይ እምነት ይኑራችሁ፤ በቃሉ እና በቅዱስ ቁርባን በኩል በልዩ መንገድ ራሱን የሚገልጸውን ኢየሱስ ክርስቶስን በትኩረት ተመልከቱት፤ እነዚህ ሁለቱ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንደሚጓዝ ያሳዩናል” ብለው፥ በዚህ እኛም የከበበንን ሞት አሸንፈን ከሞት እንደተነሡት ሰዎች እንኖራለን” ብለዋል።

ቁስሎችን መፈወስ እና ተስፋን እንደገና ማቀጣጠል

ይህም “ብቸኞች አለመሆናችንን፣ ቁስሎችን እንድንፈውሳቸው እና ተስፋችንን እንደገና እንድናቀጣጥል ሊያደርገን ይገባል” ሲሉ አሳስበው፥ “የአገራችሁ ታሪክ፣ እስከ ዛሬ ልትቋቋሟቸው አስቸጋሪ የሆኑት የጦርነት እና የአመጽ ውጤቶች፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ የድህነት ዓይነቶች በሙሉ ከሕዝቦች ጋር የምትጓዝ እና የልጆቿን ጩኸት የምትሰማ ቤተ ክርስቲያን ከጎናችሁ እንድትሆን የሚያሳስብ” ነው ብለው፥ በቃሉ ብርሃን እና በቅዱስ ቁርባን የምትመግብ ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ተስፋ እንደገና የምታድስ እንደሆነች አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለአንጎላ ምዕመናን ቃለ-ምዕዳን በማሰማት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለአንጎላ ምዕመናን ቃለ-ምዕዳን በማሰማት ላይ   (AFP or licensors)

“ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁለቱ የኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ዳቦን ቆርሶ እንደሰጣቸው ሁሉ፥ ራሳቸውን ለሌሎች አገልግሎት አሳልፈው የሚሰጡ እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋታል” ብለው፥ “አንጎላ በልባቸው ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት ለአገልግሎት ለመስጠት እና እርስ በርስ ለመጋራት ፍላጎት ያላቸውን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ሚስዮናውያን፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን ያስፈልጓታል” ብለዋል።

የወደፊት ተስፋን መገንባት ይቻላል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቃለ-ምዕዳናቸው፥ “ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አማካይነት እኛም እውነታን የሚቀይር የሕይወት እንጀራ መሆን እንችላለን” ብለው፥ ቅዱስ ቁርባን እኛ አንድ አካል እና አንድ መንፈስ መሆናችንን እንደሚያስታውሰን ሁሉ፥ የድሮ መለያየት ሙሉ በሙሉ የሚወገድበት፣ ጥላቻ እና ዓመፅ የሚጠፋበት፣ የሙስና ቁስል በአዲስ የፍትህ እና የመጋራት ባሕል የሚፈወስበት አገርን መገንባት እንችላለን” ብለዋል።

“በዚህ መንገድ ብቻ ተስፋን ላጡት በርካታ ወጣቶች የወደፊት ሕይወት እውን ይሆናል” ሲሉ በጥብቅ ተናግረው፥ የአገሪቱ ምእመናን የወደፊት ሕይወታቸውን በተስፋ እንዲመለከቱት እና እንዲገነቡት በማበረታታት፥ ይህን ለማድረግ መፍራት እንደሌለባቸው በማሳሰብ፥ “ከእናንተ ጋር የሚጓዝ እና ራሱን እንደ እንጀራ የሚቆርስ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤው ምስክሮች እና የአዲሱ ሰብዓዊነት እና ማኅበረሰብ ዋና ተዋንያን እንድትሆኑ ያበረታታችኋል” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

የአንጎላ ካቶሊካዊ ምዕመናን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አባታዊ ቅርበት እና ጸሎት መተማመን እንደሚችሉ በማረጋገጥ፥ ምዕመናኑንም ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃ አደራ በመስጠት፥ እርሳቸውም በምዕመናኑ እንደሚተማመኑ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉ የአንጎላ ምዕመናን ሰላምታ ሲሰጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉ የአንጎላ ምዕመናን ሰላምታ ሲሰጡ   (ANSA)
20 Apr 2026, 12:16