ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ቀረበ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መኖሪያ በነበረው የቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኝ ጸሎት ቤት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊጂ ትራቫሊኖ እንደ ነበሩ ታውቋል።

“ዛሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለተኛው ፎቅ ላይ ለሥራ፣ ለስብሰባ እንዲሁም በትንሿ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ ለጸሎት የሚዘጋጁበት ጊዜ አይደለም” ሲሉ ተናግረው፥ እርሳቸው ይህንን ቤት እንደወደዱት ሁሉ እኛም እርሳቸውን እንደምንወዳቸው እርግጠኛ ነኝ ብለው፥ የዕረፍታቸው አንደኛ ዓመት በሚታሰብበት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከእኛ ጋር እንደቀረቡ ይሰማናል” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ አሰርቢ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ይህንን በቃለ-ምዕዳናቸው የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊጂ ትራቫሊኖ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት  ውስጥ በንባብ ያሰሙትን መልዕክት መሠረት በማድረግ ነው።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ

ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ አሰርቢ በቃለ-ምዕዳናቸው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አካላዊ ሕመም ቢኖርባቸውም የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ዕድገቶችን አምጥተዋል” ብለዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ሥልጣን ዓመታት ውስጥ አካላዊ ውስንነት ቢኖርባቸውም ተልዕኮአቸውን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለመውሰድ ያደረጉትን ድፍረት ማስታወስ እፈልጋለሁ” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ አሰርቢ ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእያንዳንዱ ሐዋርያዊ ጉዞአቸው በፊት እና በኋላ እንዲሁም በሕይወታቸው መጨረሻ በክብር ወደተቀበላቸው ወደ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሃሳባችንን እናዙር” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊጂ ትራቫሊኖ ተናግረዋል።

የሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ እስከ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2018 ዓ. ም. ምሽት ድረስ ይቀጥላል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ጀምሮ የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚቀርብ እና ከዚያም በካርዲናሎች መማክርት ጽሕፈት ቤተ ተጠሪ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ የሚመራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ

 

21 Apr 2026, 16:39