መጭዎቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች ይፋ መሆናቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የሚያደርጓቸውን ሁለት ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ጨምሮ ሁለት ሐዋርያዊ ሹመቶችንም እንደሚሰጡ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በሚያዝያ ወር የሚያደርጉት የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአልጄሪያ፣ በካሜሩን፣ በአንጎላ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ሊያደርጉት ያቀዱት የአሥር ቀናት ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛው እንደሚሆን ታውቋል።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ከተመረጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ አህጉር የሚጓዙ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው ከዚህ ቀደም ኬንያን ቢያንስ ስድስት ጊዜ፣ ታንዛኒያን አምስት ጊዜ ያህል መጎብኘታቸው ይታወሳል። በየካቲት ወር 2017 ዓ. ም. ወደ ናይሮቢ ተጉዘው አዲስ የታነጸው ጸሎት ቤት ምረቃ ላይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴን መርተው እንደነበር ይታወሳል።
የቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም ጠቅላይ አለቃ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኙ የገዳሙ አባላትን ጎብኝተው እንደ ነበርም ይታወሳል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሚያዝያ 18/2018 ዓ. ም. ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ ለምስጢረ ክኅነት አሰጣጥ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ታውቋል። “የመልካም እረኛ እሑድ” ተብሎ በሚታወቀው በዚህ ዕለት ቅዱስነታቸው ከሮም ሀገረ ስብከት ለተውጣጡ ስምንት ሰዎች ምስጢረ ክኅነትን እንደሚሰጧቸው ታውቋል።
በግንቦት ወር መርሃ ግብር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ሚያዝያ 24/2018 ዓ. ም. ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ በቅዱስ ዮሐንስ ዘ ላቴራ ባዚሊካ ውስጥ የሚፈጸም የጵጵስና ማዕረግ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓትን ይመራሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓርብ ግንቦት 30/2018 ዓ. ም. በደቡብ ጣሊያን ወደሚገኝ የፖምፔ ቅዱስ መቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ በመሄድ የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ ሥልጣን የመጀመሪያ ዓመት በዓላቸውን ከረፋዱ በአራት ሰዓት ተኩል ላይ በሚያቀርቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ያከብራሉ። ኔፕልስም ጭምር በሚጎበኙበት በዚህ ጉዞ በቤተ መቅደሱ ውስ|ጥ የምስጋና ጸሎትን ይደግማሉ።
ቅዱስነታቸው ይህን ከፈጸሙ ከሦስት ሳምንታት በኋላ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት ግንቦት 16/2018 ዓ. ም. የሚከበረውን የጴንጤቆስጤ በዓል በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከረፋዱ በአራት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን መሥዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ።
በአይቤሪያ እና በሜዲትራኒያን ደሴት የሚያደርጉት ግብኝት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ስፔን በመጓዝ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 5/2018 ዓ. ም. ድረስ በካናሪ ደሴቶች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማጠናቀቃቸው በፊት አዲሱን እና ረጅሙን የሳግራዳ ፋሚሊያ ባዚሊካን ለመባረክ ባርሴሎናን ይጎበኛሉ።
ቅዱስነታቸው ከስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጣሊያን ሚላን ከተማ በስተደቡብ በምትገኘው ፓቪያ ውስጥ ሰኔ 13/2018 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በአገሩ አቆጣጠርን በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ የሚቀርበውን የማታ ጸሎት ይካፈላሉ። የሰሜን ጣሊያን ከተማ ፓቪያ ከቅዱስ አጎስጢኖስ ጋር ግንኙነት ያላት ሲሆን፥ ቅዱስ አጽሙ በዚያው በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ በክብር ተቀምጠው ይገኛሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ማለትም ሰኔ 22/2018 ዓ. ም. የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ክብረ በዓልን በማስመልከት በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. በደቡብ ጣሊያን ላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ። ይህች ደሴት ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወደ ጣሊያን እና አውሮፓ ለሚመጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ዋና የመግቢያ በር እንደሆነች ይታወቃል።
