ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የቅዱስ ብሩክ ማኅበር መነኮሳትን ለመልካም አገልግሎታቸው አመሰገኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማኅበሩ ዓባላት ባደረጉት ንግግር፥ ወንድሞች እና እህቶች ለቤተ ክርስቲያን በምታበረክቷቸው ግዙፍ እና ድብቅ መልካም ተግባራት፣ በመሥዋዕታቸው፣ በማያቋርጥ ጸሎታቸው፣ በአገልግሎታቸው እና በሕይወት ምስክርነታቸው አመስግነው፥ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሦስት የቅዱስ ብሩክ ማኅበር መነኮሳት የማበረታቻ ንግግር ያደረጉት ሰኞ መጋቢት 21/2018 ዓ. ም. ሲሆን እነርሱም ከሮም ከተማ ወጣ ብሎ በሱቢያኮ የሚገኙት የቅድስት ስኮላስቲካ ገዳማውያት፣ በሴሴና የሚገኙት የቅድስት ማርያም ገዳማውያት፣ በባሪ የሚገኙት የቅድስት ስኮላስቲካ ገዳም መነኮሳት እና ከእነርሱም ጋር በቫቲካን ለተገኙት መነኩሴዎች ጭምር እንደሆነ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው ከመነኮሳቱ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ የቅዱስ ብሩክ የመንፈሳዊ ተነሳሽነት እሴቶች በሕይወታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ ስላሉት ዋጋ በአንድነት ለማሰላሰል ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታንም ገልጸዋል።
ቅዱስ ብሩክ ምእመናን የአንድን ሰው የሕይወት ተግባር ሳያቋርጡ እንዲጠብቁት ማሳሰቡን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ብሩክ ሕይወት ላይ የሚያስተነትኑ ሰዎች ጸሎት እና የእግዚአብሔርን ቃል በጽሞና ማንበብ በንቃት ለመኖር እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።
ይህንን በዚህ መንገድ የሚፈጽሙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ያላቸውን ለመረዳት፣ የራሳቸውን ድክመቶች እና ኃጢአቶች ለማወቅ እና የእግዚአብሔርን ጸጋዎች እና በረከቶችለ ለማክበር ያስችላቸዋል ብለው፥ በዚህ መንገድ የእርሱ ለመሆን ያለን ፍላጎት እንደሚጠነክር እና የመቀደሳችን ቃል ኪዳንም እንደሚረጋገጥ አስረድተዋል።
ቅዱስታቸው በማከልም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዘወትር በማሰላሰል፣ ለዕለት ተዕለት ሕይወት ምግባቸው እንዲሆን በማድረግ እና ይህን ተሞክሮአቸውን ለሌሎች ማጋራት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ወደ ቅድስና የሚወስድ መንገድ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅንዓት እና በተነስሽነት የተሞላው የቅድስና መንገድ አንዲት መነኩሴን ወደ ግል ጉዞ ሊመልሳት እንደማይችል ገልጸው፥ “የቅድስና መንገድ የጋራ ገጽታ ያለው በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጆች በሙሉ ባለው የፍቅር እና የወንድማማችነት አገልግሎት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ነው” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ለመነኮሳቱ ባደረጉት የማበረታቻ ንግግራቸው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመደማመጥ በጋራ በሚያድደርጉት ጉዞ ላይ ከአካባቢው ቤተ ክርስቲያን እና ከቅዱስ ብሩክ ማኅበር ጋር በመተባበር በተለይም በወንድማማችነት ጉባኤዎች፣ በጋራ ጸሎት እና በጋራ ውሳኔዎች ውስጥ እንዲሳተፉ አበረታተዋቸዋል።
ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚሆን ምሳሌ
የገዳም ሕይወት ራስን ብቻ በማሰብ እና በግለኝነት በሚታወቅ ዓለም ውስጥ ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ምሳሌ እንደሚሆን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “ከምንም ነገር በፊት ሚስዮናዊ መሆን የእርስ በርስ ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚገባ ያስታውሰናል” ብለዋል።
የምንኩስና ሕይወት የተደበቀ ተልዕኮ ልዩ ገጽታን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህም የእግዚአብሔር ቃል የምልጃ ጸሎት የሆነበትን እና እኛን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያገናኘን የጸሎት ገጽታን አወድሰዋል።
“ይህ በአደራ የተሰጣችሁ ሥራ ዋና እና መሠረታዊ ገጽታ ነው” ይሉት ቅዱስነታቸው፥ ከቤተ መቅደሱ ሳትወጣ እግዚአብሔርን ሌት ተቀን በጾም እና በጸሎት ያገለገለች የነቢይቱ ሐና ተነሳሽነት እንዲኖራቸው አደራ ብለዋል። “መበለት ሆና በዕድሜ እየገፋች በመምጣት የእግዚአብሔርን ቤት የራሷ አድርጋዋለች” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ጸሎት እና ባሕታዊነት እግዚአብሔርን እንድታውቅ አድርጓታል” ሲሉ አክለዋል።
የበጎ አድራጎት እና የክርስቶስ ፍቅር ቀዳሚነት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ከእውቀት ሁሉ በላይ በሆነውን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ቀጣይነት ያለው የገዳም ሕይወት ትምህርት አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተው፥ መነኮሳቱ ለሚያደርጉት ታላቅ ጥረት በሰጡት አድናቆትም፥ ለበጎ አድራጎት ቅድሚያን ሲሰጡ እያንዳንዱ ገዳም የበለጠ የእግዚአብሔር አገልግሎት ትምህርት ቤት እንደሚሆን በማስረዳት፥ የአገልግሎታቸውን አደራ በሙሉ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለቅዱስ ብሩክ፣ ለቅድስት ስኮላስቲካ እና ለበርካታ የቅዱስ ብሩክ ማኅበር ቅዱሳን ሰጥተዋል።
