ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ሊዮ "ኢየሱስ ጦርነት የሚያካሂዱትን ሰዎች ጸሎት በፍጹም አይሰማም" ማለታቸው ተገለጸ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም የሆሳህና በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባባት የሆሳህና በዓል በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተከበረበት ወቅት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ጦርነትን የሚደግፉ እና ጦርነት የሚያካሂዱትን ሰዎች ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነውን ኢየሱስ የሰላም ንጉሥ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ጌታ ሕማማቱን ለምቀበል በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት የሆሳህና በዓል እሑድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን ቅዳሴ አሳርገዋል። 

በስብከታቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዓመፅ በዙሪያው እየታየ ቢሆንም እንኳን ኢየሱስ የሰላም ንጉሥ መሆኑን መግለጻቸው የተዘገበ ሲሆን ኢየሱስ የመስቀል መንገዱን ስያከናውን ከእርሱ ጋር እንሄዳለን እና ለሰው ልጅ ሲል የተሸከመውን ሕማማቱን እናሰላስላለን፣ ይህም የፍቅር ስጦታ ነው ብለዋል። ይህንን ሐሳባቸውን ቅዱስነታቸው ሲያጠናክሩ የሚከተለውን ብለዋል . . .

"ኢየሱስ በመስቀል መንገድ ላይ ሲጓዝ፣ እኛም ከእርሱ ኋላ ሆነን እንከተለዋለን፣ ፈለጉንም እንከተላለን። ከእርሱ ጋር ስንሄድ፣ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር፣ የተሰበረውን ልቡን እና ሕይወቱን እንደ ፍቅር ስጦታ እናስባለን። ጦርነት በዙሪያው እየተንገዳገደ ቢሆንም እንኳ ራሱን የሰላም ንጉሥ አድርጎ የሚገልጸውን ኢየሱስን እንመለከተዋለን። ሌሎች ደግሞ ዓመፅን እያነሳሱ በሚገኝበት ሰዓት እርሱ በትሕትና ይቆማል። ሌሎች ሰይፍና ዱላ ሲያነሱም እንኳ የሰውን ልጅ ለማቀፍ ራሱን ያቀርባል። ጨለማ ምድርን ሊሸፍን ቢቃረብም፣ የዓለም ብርሃን እርሱ ይሆናል።   ሞት በእርሱ ላይ ለመፍረድ ዕቅዶች ሲወጡም እንኳ ሕይወትን ለማምጣት እርሱ መጣ የሰላም ንጉሥ። ኢየሱስ ዓለምን ወደ አብ ክንድ ለማምጣት፣ ከእግዚአብሔርና ከባልንጀራችን የሚለየንን ማንኛውንም እንቅፋት ለማፍረስ ይፈልጋል፣ ምክንያቱም “ሰላማችን ነው” (ኤፌ 2፡14)።

“ሌሎች ዓመፅን ሲያነሳሱ፣ ኢየሱስ ግን በትሕትና ጸንቶ ይኖራል፣ ሌሎች ሰይፍና ዱላ ሲያነሱ፣ የሰውን ልጅ ለመቀበል ራሱን ያቀርባል” ያሉት ቅዱስነታቸው አክለውም ኢየሱስ ጨለማና ሞት ሊውጠን ሲል እንኳን ሕይወትንና ብርሃንን ለዓለም ለማምጣት መጣ ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል ...

"የሰላም ንጉሥ። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በፈረስ ላይ ሳይሆን በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሆን በመሲሑ መምጣት ደስታን የሚጠይቀውን ጥንታዊ ትንቢት ፈጽሟል፡- “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ! እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። ሠረገላውንም ከኤፍሬም፥ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆና"  (ዘካ 9፡9-10)።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ኢየሱስ ዓለምን ወደ አብ ክንድ ለማምጣት እና ከእግዚአብሔር እና ከባልንጀሮቻችን ጋር መገናኘት የሚከለክለንን ማንኛውንም እንቅፋት ለማፍረስ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰላም ንጉሥ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ በመጠቀም፣ የኢየሱስ በፍቅሩ ውስጥ ያሉትን ድርጊቶች አጉልተው ገልጸዋል፤ ይህም ሰላም ለማምጣት ያለውን ፍላጎት ያሳያል፣ ያሉት ቅዱስነታቸው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው እና ጆሮውን ሲቆርጥ፣ ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩን ሰይፉን እንዳያነሳ አዘዘው፣ በሰይፍ የሚኖሩት በሰይፍ እንደሚሞቱ ኢየሱስ ገልጾ እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው አስታውሷል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል .. .

"የሰላም ንጉሥ። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሊከላከልለት ሰይፉን ሲመዝዝ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ሲመታ፣ ኢየሱስ ወዲያውኑ አስቆመው፡- “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና” (ማቴ 26፡52)። የሰላም ንጉሥ። በሥቃያችን ተሸክሞ ስለ ኃጢአታችን ሲወጋ፣ ኢየሱስ “ወደ መታረድ እንደሚነዳ በግ፣ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ አፉን አልከፈተም” (ኢሳ 53፡7)። ራሱን አላስታጠቀም፣ ወይም ራሱን አልተከላከለም፣ ወይም ማንኛውንም ጦርነት አልተዋጋም። ሁልጊዜ ዓመፅን የሚጠላውን የእግዚአብሔርን ገር ፊት ገለጠ። ራሱን ከማዳን ይልቅ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በእያንዳንዱ ጊዜና ቦታ የተሰቀለውን መስቀል ሁሉ ተቀብሎ በመስቀል ላይ እንዲቸነከር ፈቀደ። ወንድሞችና እህቶች፣ ይህ አምላካችን ነው፡- የሰላም ንጉሥ ኢየሱስ ነው፤ ጦርነትን የሚቃወም ማንም ጦርነትን ለማጽደቅ ሊጠቀምበት አይችልም። ጦርነትን የሚዋጉ ​​ሰዎች ጸሎት አይሰማም፣ ነገር ግን “ብዙ ጸሎት ብታቀርቡም አልሰማም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋልና” (ኢሳ 1፡15) በማለት ይቃወማል።

በተሰቀለበትና በተገደለ ጊዜ፣ ኢየሱስ ራሱን አላስታጠቀም ወይም አልተከላከለም፣ ነገር ግን እንደ በግ ወደ እርድ እንዲወሰድ ፈቀደ ያሉት ቅዱስነታቸው “ሁልጊዜ ዓመፅን የሚጠላውን የእግዚአብሔርን ገር ፊት ገለጠ” ብለዋል። በዛሬው ዓለማችን ውስጥ ሰዎች “በዓመፅ የተጨቆኑትንና የጦርነት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ በሚያሠቃይ ጩኸት የተነሳ” ወደ እግዚአብሔር ሲጮሁ እግዚአብሔር የሐዘን ጩኸታቸውን ያዳምጣል፣ መልስ ይስጣል ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ስለ እኛ በተሰቀለው ላይ ትኩረታችንን ስናደርግ፣ የተሰቀለውን ሰብአዊነት እናያለን። በቁስሎቹ ውስጥ፣ ዛሬ የብዙ ሴቶችንና የወንዶችን ሥቃይ እናያለን። ወደ አብ በመጨረሻው ጩኸቱ፣ የተጨቆኑትን፣ ተስፋ የሌላቸውን፣ የታመሙትንና ብቻቸውን ያሉትን ሰዎች ለቅሶ እንሰማለን። ከሁሉም በላይ፣ በዓመፅ የተጨቆኑትንና የጦርነት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ የሚያሠቃይ ጩኸት እንሰማለን።

“የሰላም ንጉሥ ክርስቶስ፣ ከመስቀሉ እንደገና ይጮኻል፡- እግዚአብሔር ፍቅር ነው! ምሕረት ያደርጋል! የጦር መሣሪያችሁን አስቀምጡ! እናንተ ወንድማማቾችና እህተማማቾች ናችሁ!” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከተናገሩ በኋላ ስብከታቸው አጠናቀዋል።

29 Mar 2026, 14:53